በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ኦሌግ ዳኒሎቭ

መጋቢት 31, 2021
ሩሲያ

ወንድም ኦሌግ ዳኒሎቭ በችኮላ ከተካሄደ ችሎት በኋላ የሦስት ዓመት እስራት ተፈረደበት

ወንድም ኦሌግ ዳኒሎቭ በችኮላ ከተካሄደ ችሎት በኋላ የሦስት ዓመት እስራት ተፈረደበት

የፍርድ ውሳኔ

በክራስኖዳር ክልል የሚገኘው የአብንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት የወንድም ኦሌግ ዳኒሎቭን ጉዳይ ተመልክቶ መጋቢት 30, 2021 ውሳኔ አሳልፏል። ወንድም ኦሌግ ሦስት ዓመት እንዲታሰር ተፈርዶበታል። ወንድም ኦሌግ ከፍርድ ቤት በቀጥታ ወደ ማረሚያ ቤት ተወስዷል።

አጭር መግለጫ

ኦሌግ ዳኒሎቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1974 (ኡሶልየ ሲቢርስከየ፣ ሳይቤሪያ)

  • ግለ ታሪክ፦ አያቶቹ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሰሙት በ1958 ነው፤ የመሠከሩላቸው ወደ ሳይቤሪያ የተጋዙ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ወላጆቹ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። በ1991 ተጠመቀ

  • በ1995 ከናታሊያ ጋር ትዳር መሠረተ። ሁለት ወንዶች ልጆች አሏቸው። በቤተሰብ ሆነው ወደተለያዩ ቦታዎች መጓዝ እንዲሁም ተፈጥሮን ማየት ይወዳሉ

የክሱ ሂደት

ፖሊሶች የወንድም ዳኒሎቭን ቤት መጀመሪያ የፈተሹት ሚያዝያ 29, 2020 ነው። ሕግ አስከባሪ ባለሥልጣናት የተከለከሉ ጽሑፎችን ቤቱ ውስጥ ባያገኙም የቤተሰቡን አባላት ስልኮች እንዲሁም ሌሎች የግል ንብረቶች ወረሱ። ለክስ የሚያበቃ ማስረጃ ባይገኝም ኅዳር 2020 ባለሥልጣናቱ በወንድም ኦሌግ ዳኒሎቭ ላይ የወንጀል ምርመራ ማካሄድ ጀመሩ። ወንድም ዳኒሎቭ ከተጠረጠረባቸው “ወንጀሎች” መካከል ሃይማኖታዊ ትምህርት ማስተማር፣ መስበክ እንዲሁም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት ይገኙበታል።

ታኅሣሥ 2, 2020 ከንጋቱ 12:00 ላይ የደኅንነት ኃይሎች የኦሌግን ቤት ለሁለተኛ ጊዜ በመውረር ቤቱን አብጠርጥረው ፈተሹት። ከዚያም ለምርመራ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰደ።

ፍርድ ቤቱ የኦሌግን ጉዳይ በፍጥነት ለመመልከት ሲል የመጀመሪያው ቀጠሮ መጋቢት 23, 2021 እንዲሆን ወሰነ። ጉዳዩን የያዘው መርማሪ ኮሚሳሮቭ የሚባል ሲሆን በ63 ዓመቱ ወንድም አሌክሳንደር ኢቨሺን ላይ የወንጀል ምርመራ ያካሄደውም እሱ ነው። ፍርድ ቤቱ የካቲት 2021 የወንድም ኢቨሺንን ጉዳይ በችኮላ ከተመለከተ በኋላ የሰባት ዓመት ተኩል እስራት ፈርዶበታል፤ ይህም እስከ ዛሬ ሩሲያ ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከተበየኑት ከባድ ፍርዶች አንዱ ነው።

በኦሌግ ላይ የደረሰው ስደት በእሱና በቤተሰቡ ላይ ውጥረት የፈጠረ ቢሆንም አምላካችን ይሖዋ የሚያከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳዩትን ፍቅር ፈጽሞ እንደማይረሳ እንተማመናለን።—ዕብራውያን 6:10