በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ኒኮላይ አሊዬቭ እና ባለቤቱ አልዬስያ

መጋቢት 25, 2021
ሩሲያ

ወንድም ኒኮላይ አሊዬቭ በእምነቱ ምክንያት የደረሰበትን ስደት በድፍረት ተቋቁሟል

ወንድም ኒኮላይ አሊዬቭ በእምነቱ ምክንያት የደረሰበትን ስደት በድፍረት ተቋቁሟል

የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን

የካምሰሞልስክ ና አሙሪ ማዕከላዊ አውራጃ ፍርድ ቤት በወንድም ኒኮላይ አሊዬቭ ላይ የቀረበውን ክስ ተመልክቶ በቅርቡ ውሳኔውን ያሳውቃል። *

አጭር መግለጫ

ኒኮላይ አሊዬቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1978 (ካምሰሞልስክ ና አሙሪ)

  • ግለ ታሪክ፦ ልጅ እያለ ሕይወት እና ጽንፈ ዓለም እንዴት እንደተገኘ ያሳስበው ነበር። በመሆኑም መልስ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር ጀመረ። የኢየሱስን ትምህርቶችና ሰላም ፈጣሪ በመሆን ረገድ የተወውን ምሳሌ ከተማረ በኋላ በትግል ስፖርቶች መካፈል አቆመ። በ1993 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ

    በ2016 ከአልዬስያ ጋር ትዳር መሠረተ። ባልና ሚስቱ ወደተለያዩ ቦታዎች መጓዝን፣ ተራራ መውጣትን እና በረዶ ላይ መንሸራተትን ጨምሮ ብዙ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎችን ይወዳሉ

የክሱ ሂደት

ግንቦት 22, 2020 ማለዳ ላይ የካምሰሞልስክ ና አሙሪ ከተማ ሕግ አስከባሪ ባለሥልጣናት የኒኮላይ እና የአልዬስያን ቤት ሰብረው ገቡ። ፖሊሶቹ ሲገቡ ኒኪላይን መሬት ላይ የጣሉት ሲሆን ቤታቸውን ለአምስት ሰዓት ያህል ፈተሹ፤ ከዚያም ባልና ሚስቱን በቁጥጥር ሥር አዋሏቸው። በምርመራው ወቅት ፖሊሶቹ ለኒኮላይ ብዙኃኑ የሚከተለውን ዓይነት ሃይማኖት እንዲይዝ ሐሳብ አቅርበውለት ነበር። አልዬስያን ደግሞ ካልተባበረች ባሏ ላይ “የሆነ ነገር እንደሚደርስበት” በመግለጽ አስፈራሯት። ይህ ሁሉ ዛቻ ቢደርስባቸውም ምሽት ላይ ተለቀው ወደ ቤታቸው ተመለሱ።

ኒኮላይ በዚህ መከራ ወቅት ይሖዋ እሱን በደገፈባቸው በርካታ መንገዶች ላይ ማሰላሰሉ ብርታት ሰጥቶታል። እንዲህ ብሏል፦ “ፈተና ሲያጋጥማችሁ፣ ሁኔታውን በራሳችሁ ልትወጡት እንደማትችሉ ትገነዘባላችሁ። ይሖዋ ጸሎት የሚመልስበትንና መመሪያ የሚሰጥበትን መንገድ ይበልጥ ማየት ችያለሁ። ጳውሎስ ‘ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝና’ በማለት የተናገረው ሐሳብ ትክክለኛ እንደሆነ ይበልጥ እርግጠኛ ሆኛለሁ።”—2 ቆሮንቶስ 12:10

ኒኮላይ እና አልዬስያ ይበልጥ ደፋሮች ለመሆን እና ለመረጋጋት የሚረዷቸውን እርምጃዎች መውሰዳቸውን ቀጥለዋል። ኢሳይያስ 41:10⁠ን አትመው ፍሪጃቸው ላይ ለጥፈውታል። ኒኮላይ እንዲህ ብሏል፦ “ነገሮች በጣም ተፈታታኝ ሲሆኑብኝ ይህን ጥቅስ አነበዋለሁ፤ ይህም ቀለል እንዲለኝ ያደርገኛል። በጥቅሱ ላይ የሚገኘው ሐሳብ እንዳልፈራ ያበረታታኛል። በተለይ ደግሞ ይሖዋ ከጎኔ እንደሆነና አጠገቤ ያለ ያህል በቀኝ እጁ እቅፍ እንዳደረገኝ የሚገልጸው ሐሳብ በጣም ያበረታታኛል።” ይሖዋ ምንጊዜም ታማኞቹን ማበረታታቱን እንደሚቀጥል እንተማመናለን።

^ አን.3 ፍርድ ቤቱ ብይን የሚያስተላልፍበትን ቀን አስቀድሞ የማያሳውቅበት ጊዜ አለ።