በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት አይሪና ሎክቪትስካያ

መጋቢት 29, 2021
ሩሲያ

እህት አይሪና ሎክቪትስካያ የወንጀል ክስ ቢመሠረትባትም በአቋሟ ጸንታለች

እህት አይሪና ሎክቪትስካያ የወንጀል ክስ ቢመሠረትባትም በአቋሟ ጸንታለች

የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን

በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት በእህት አይሪና ሎክቪትስካያ ላይ የቀረበውን ክስ ተመልክቶ በቅርቡ ውሳኔውን ያሳውቃል። * አቃቤ ሕጉ በእህት አይሪና ላይ እንዲተላለፍ የሚፈልገውን ብይን ገና አላሳወቀም።

አጭር መግለጫ

አይሪና ሎክቪትስካያ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1962 (ኢዝቭዬስትኮቮዬ)

  • ግለ ታሪክ፦ አባቷ የሞተው የስድስት ዓመት ልጅ እያለች ነው። ልጅ እያለች ዳንስ፣ ቲያትር፣ ሹራብ ሥራ፣ ቅርጫት ኳስ እና መረብ ኳስ ትወድ ነበር

    በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የትንሣኤ ተስፋ ማረካት። በ1993 ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። በተጠመቀች በሰባት ወሯ ባለቤቷ ሞተ፤ በወቅቱ የሰባት ዓመት ልጅ የነበረውን አርተርን ያሳደገችው ብቻዋን ነው

የክሱ ሂደት

የካቲት 6, 2020 የሩሲያ ባለሥልጣናት፣ በጽንፈኝነት እንቅስቃሴ ተካፍለዋል በማለት ክስ ከመሠረቱባቸው በቢሮቢድዣን ከተማ የሚገኙ ስድስት እህቶች መካከል እህት አይሪና ሎክቪትስካያ አንዷ ናት። በዚያ አካባቢ በሚገኙ 22 የይሖዋ ምሥክሮች ላይ 19 ክሶች ተመሥርተዋል፤ ከእነሱ መካከል የአይሪና ልጅ አርተር እና ባለቤቱ አና ይገኙበታል።

የአይሪና ጉዳይ የታየው በዝግ ችሎት ነው፤ ጋዜጠኞችንና ቤተሰቧን ጨምሮ ማንም በፍርድ ቤቱ እንዲገኝ አልተፈቀደም። አይሪና ችሎቱ ለሕዝብ ክፍት እንዲሆን እና ጉዳይዋ ወደ አቃቤ ሕጉ እንዲመለስ ያቀረበችው ጥያቄም ተቀባይነት አላገኘም።

የምርመራውና የፍርዱ ሂደት በአይሪና አካላዊና ስሜታዊ ጤንነት ላይ ጫና አሳድሯል። ሆኖም ቋሚ መንፈሳዊ ልማድ ያላት መሆኑ እንድትጸና ረድቷታል። እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ጥሩ ልማዶች እንዳዳብር ረድቶኛል። መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ብቻ ሳልወሰን በጥልቀት አጠናዋለሁ።” በጭንቀት ከመዋጧ የተነሳ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ሲከብዳት የይሖዋን እርዳታ ጠየቀች። እንዲህ ብላለች፦ “አጥብቄ መጸለይ ጀመርኩ፤ እንዲሁም ወደ ቀድሞው ልማዴ የመመለስ ግብ አወጣሁ። ይሖዋ ከራሴ ይበልጥ ስለ ሌሎች እንዳስብ አስተምሮኛል።”

አይሪና ከእሷ ይበልጥ ድጋፍና ማበረታቻ በሚያስፈልጋቸው ሰዎች ላይ ትኩረት ታደርጋለች። ከእነዚህም መካከል ለምሥራቹ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች እንዲሁም ክርስቲያን ወንድሞቿና እህቶቿ ይገኙበታል። እንዲህ ብላለች፦ “ስለ ሌሎች የማስብ ከሆነ ለራሴ ለማዘን ወይም ከልክ በላይ ለመጨነቅ ጊዜ አይኖረኝም።”

ጉባኤው በተለይም ሽማግሌዎቹ አይሪናን አበረታተዋታል። ስለ እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “እነሱ ራሳቸው ስደት እየደረሰባቸው ቢሆንም እኔን አጽናንተውኛል፤ ምንጊዜም የሚያስፈልገኝን ማበረታቻ ይሰጡኛል። በተጨማሪም ስፈልጋቸው ሁልጊዜ ይደርሱልኛል፤ ለዚህም በጣም አመስጋኝ ነኝ።”

አይሪና ይህን ፈተና በጽናት ለመቋቋም ጥረት በምታደርግበት ወቅት ይሖዋ የሚያስፈልጋትን ነገር ሁሉ እንደሚያሟላላት ትተማመናለች፤ እኛም የእሷን ስሜት እንጋራለን። እንዲህ ብላለች፦ “ስደት ስለደረሰባቸው ሰዎች ሳነብ፣ እኔ በእነሱ ቦታ ብሆን ምን እንደማደርግ ሁልጊዜ አስብ ነበር። በይሖዋ እታመን ይሆን? አሁን መልሱን አግኝቻለሁ። በይሖዋ እርዳታ በእሱ መታመን እንደምችል ተመልክቻለሁ። እንደ ሌሎች ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ሁሉ እኔም ጸንቼ እቆማለሁ፤ ይሖዋ ደግሞ በቀኝ እጁ ይይዘኛል።”—ኢሳይያስ 41:10

^ አን.3 ፍርድ ቤቱ ብይን የሚያስተላልፍበትን ቀን አስቀድሞ የማያሳውቅበት ጊዜ አለ።