በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት አናስታሲያ ጉዜቫ ከባለቤቷ ከኮንስታንቲን ጋር

ሚያዝያ 2, 2021
ሩሲያ

እህት አናስታሲያ ጉዜቫ በእምነቷ ምክንያት እስራት ሊፈረድባት ይችላል

እህት አናስታሲያ ጉዜቫ በእምነቷ ምክንያት እስራት ሊፈረድባት ይችላል

የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን

በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት በእህት አናስታሲያ ጉዜቫ ላይ የቀረበውን ክስ ተመልክቶ በቅርቡ ውሳኔውን ያሳውቃል። *

አጭር መግለጫ

አናስታሲያ ጉዜቫ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1979 (ቢሮቢድዣን)

  • ግለ ታሪክ፦ እሷንና ሁለት ወንድሞቿን ያለአባት ያሳደገቻቸው እናታቸው ናት። ልጅ እያለች ማንበብ፣ ስፖርት እንዲሁም ዳንስ ትወድ ነበር። አሥር ዓመት ሲሆናት አያቷ ቤት መጽሐፍ ቅዱስ አገኘች። ይህም ስለ አምላክ ለማወቅ እንድትነሳሳ አደረጋት። ከጊዜ በኋላ እሷና እናቷ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጠኑ። ሁለቱም በ1995 ተጠመቁ። በ2001 ከኮንስታንቲን ጋር ትዳር መሠረተች

የክሱ ሂደት

ግንቦት 2018 የሩሲያ ባለሥልጣናት የኮንስታንቲንን እና የአናስታሲያን አፓርታማ ፈተሹ። ኮንስታንቲን ሐምሌ 2019 አናስታሲያ ደግሞ የካቲት 2020 “በጽንፈኝነት” ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው። በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል በሚገኙ 23 የይሖዋ ምሥክሮች ላይ 19 ክሶች ተመሥርተዋል።

በኮንስታንቲን እና በአናስታሲያ ላይ የሚደረገው የወንጀል ምርመራ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ላይ ከባድ ጫና አሳድሯል። “ጽንፈኛ” ተብለው ስለተፈረጁ ሁለቱም ከሚሠሩበት የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተሰናብተዋል። የካቲት 2021 ኮንስታንቲን የሁለት ዓመት ተኩል የገደብ እስራት ተፈርዶበታል።

አናስታሲያ ለመጽናት የረዳት ምን እንደሆነ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ስደት እንደሚያጋጥማችሁ መጠበቃችሁና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስትሆኑ ምን እንደምታደርጉ ማሰባችሁ ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ ኢየሱስ በምድር ላይ ስላሳለፈው የመጨረሻ ቀን ስናነብ ኢየሱስ በሚያዝበት ወቅት ምን እንደሚያደርግ አስቀድሞ አስቦ እንደነበር እናስተውላለን፤ . . . መቼ እንደሚናገር፣ መቼ ዝም እንደሚልና ምን እንደሚናገር አስቀድሞ አስቦ መሆን አለበት።”

አናስታሲያ በሮም 8:38, 39 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በአሁኑ ወቅት ለእሷ ልዩ ትርጉም እንዳለው ገልጻለች። እንዲህ ብላለች፦ “ለደስታ ምክንያት የሚሆነን ነገር በዚህ ጥቅስ ላይ ተገልጿል። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ሁለት አካላት ይወዱኛል፤ ደግሞም ማንም ከእነሱ ፍቅር ሊለየኝ አይችልም። ይህን ማወቄ እንድጸና እና ደፋር እንድሆን ያነሳሳኛል።”

^ አን.3 ፍርድ ቤቱ ብይን የሚያስተላልፍበትን ቀን አስቀድሞ የማያሳውቅበት ጊዜ አለ።