በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከላይ ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም ዬቭጌኒ ድዬሽኮ እና ወንድም ሩስላን ኮሮልዮቭ፤ ከታች ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም ቫለሪ ሻሌቭ ከባለቤቱ ከስቬትላና ጋር እና ወንድም ቪክቶር ማልኮቭ ከባለቤቱ ከቭዬራ ጋር። አራተኛው ተከሳሽ የነበረው ወንድም ቪክቶር ማልኮቭ የፍርድ ሂደቱ ከማብቃቱ በፊት በሞት አንቀላፍቷል

መጋቢት 24, 2021
ሩሲያ

በስሞለንስክ የሚኖሩ አራት ወንድሞች በእምነታቸው የተነሳ ለከባድ ስደትና እስራት ተዳርገዋል

በስሞለንስክ የሚኖሩ አራት ወንድሞች በእምነታቸው የተነሳ ለከባድ ስደትና እስራት ተዳርገዋል

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ሦስት ወንድሞችን “በጽንፈኝነት” ወንጀል ፈረደባቸው

ሚያዝያ 23, 2021 የስሞለንስክ ኢንደስትሪያል አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም ዬቭጌኒ ድዬሽኮ፣ ወንድም ሩስላን ኮሮልዮቭ እና ወንድም ቫለሪ ሻሌቭ በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል የሚል ውሳኔ አሳለፈ። ወንድም ሩስላን ኮሮልዮቭ እና ወንድም ቫለሪ ሻሌቭ እያንዳንዳቸው የስድስት ዓመት ተኩል የገደብ እስራት ተፈርዶባቸዋል። ወንድም ዬቭጌኒ ድዬሽኮ ደግሞ የስድስት ዓመት የገደብ እስራት ተፈርዶበታል። እርግጥ አሁን ወህኒ አይወርዱም።

የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን

የስሞለንስክ ኢንደስትሪያል አውራጃ ፍርድ ቤት በወንድም ዬቭጌኒ ድዬሽኮ፣ በወንድም ሩስላን ኮሮልዮቭ እና በወንድም ቫለሪ ሻሌቭ ላይ የቀረበውን ክስ ተመልክቶ በቅርቡ ውሳኔውን ያሳውቃል። * አቃቤ ሕጉ፣ ወንድም ዬቭጌኒ እና ወንድም ሩስላን የዘጠኝ ዓመት፣ ወንድም ቫለሪ ደግሞ የስምንት ዓመት እስራት እንዲፈረድባቸው ጠይቋል። በዚህ ክስ ውስጥ ተካትቶ የነበረው ወንድም ቪክቶር ማልኮቭ የፍርድ ሂደቱ ከመጠናቀቁ በፊት በሞት አንቀላፍቷል።

አጭር መግለጫ

ዬቭጌኒ ድዬሽኮ

 • የትውልድ ዘመን፦ 1989 (ሶቺ)

 • ግለ ታሪክ፦ የእሽት ሕክምና ይሰጥ ነበር፤ በተጨማሪም ሾፌርና የኤሌክትሪክ ባለሙያ ሆኖ ሠርቷል። ወላጆቹ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ለመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች የነበረው ጥልቅ አክብሮት በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ እንዳይሆን አድርጎታል። በ2012 ተጠመቀ። ከ2012 እስከ 2014 ባለው ጊዜ ውስጥ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ግዴታውን ለመወጣት በአንድ የአረጋውያን ሆስፒታል ውስጥ ሠርቷል

ሩስላን ኮሮልዮቭ

 • የትውልድ ዘመን፦ 1982 (ስሞለንስክ)

 • ግለ ታሪክ፦ በልጅነቱ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን መጠገን የሚቻልበትን መንገድ ማወቅ ያስደስተው ነበር። ከጊዜ በኋላ ሜካኒክ ሆነ። በሩሲያ ጦር ሠራዊት ውስጥ አገልግሏል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምር የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አጽናናው። በ2004 ተጠመቀ

ቪክቶር ማልኮቭ

 • የትውልድ ዘመን፦ 1959 (ስሞለንስክ)

 • ግለ ታሪክ፦ በሜካኒክነትና በአናጺነት ሠርቷል፤ እንዲሁም ጣሪያ ሠሪ ነበር። በ1992 ከቭዬራ ጋር ትዳር መሠረተ። ወጣት እያለ እግር ኳስ መጫወት ይወድ ነበር። የማየት ችግር ያለበትን ወንድሙን ይንከባከብ ነበር

  ዓመፀኛ ሰው ነበር፤ በዚህም ምክንያት ለሰባት ዓመት ታስሯል። ትዳሩ በፍቺ ሊፈርስ ተቃርቦ ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ካጠና በኋላ ሰላማዊ ሰው፣ ሕግ አክባሪ ዜጋ እንዲሁም ጥሩ ባል ሆነ። በ2008 ተጠመቀ። ሚያዝያ 25, 2020 በሞት አንቀላፋ

ቫለሪ ሻሌቭ

 • የትውልድ ዘመን፦ 1977 (ያርትስዬቮ)

 • ግለ ታሪክ፦ በወጣትነቱ የእንግሊዝኛ ቋንቋ አጥንቷል። ከጦር ሠራዊት ትምህርት ቤት ተመርቋል። በጦር ሠራዊቱ ውስጥ በሒሳብ ባለሙያነት ለመሥራት ወደ ሩሲያ ሩቅ ምሥራቃዊ ክፍል ተዛውሮ ነበር። ከጦር ሠራዊቱ ከወጣ በኋላ የሒሳብ አማካሪ ሆኖ ሠርቷል። ኮሌጅ ሲማር ያውቃት ከነበረችው ከስቬትላና ጋር በ1999 ትዳር መሠረተ፤ ከዚያም የአራት ዓመት ልጇን እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ማሳደግ ጀመረ። እግር ኳስ መጫወትና ሩጫ ያዘወትራል

  እናቱ መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ከጀመረች በኋላ የተማረችውን ነገር ነገረችው። የእናቱ አዲስ እምነት ስህተት መሆኑን ሊያሳምናት ጥረት አድርጎ ነበር፤ ውሎ አድሮ ግን እውነትን እንደያዘች ተገነዘበ። በ2002 ተጠመቀ

የክሱ ሂደት

በስሞለንስክ በወንድሞቻችን ላይ ስደት መድረስ የጀመረው በ2017 ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሩሲያ የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ ከማገዱ በፊት ነው። ታኅሣሥ 18, 2016 መሣሪያ የታጠቁ 15 ፖሊሶች ስሞለንስክ ውስጥ በአንድ የስብሰባ አዳራሽ የሚካሄድን የጉባኤ ስብሰባ አቋርጠው ገቡ። በስብሰባው ላይ 60 ያህል ወንድሞችና እህቶች ተገኝተው ነበር። በዚህ ወቅት ፖሊሶቹ የሩሲያ መንግሥት በጽንፈኝነት የፈረጃቸውን ጽሑፎች አዳራሹ ውስጥ ደበቁ፤ ከዚያም እነዚህን ጽሑፎች በአዳራሹ ውስጥ እንዳገኙ ገለጹ።

በ2018 እና በ2019 ባለሥልጣናቱ የወንድሞችን ቤቶች ይፈትሹ፣ ወንድሞችን በቁጥጥር ሥር ያውሏቸው እንዲሁም ያስሯቸው ነበር። ሚያዝያ 25, 2019 የተለያዩ ቤቶችን የፈተሹ ሲሆን ወንድም ሩስላን ኮሮልዮቭን፣ ወንድም ቫለሪ ሻሌቭን እና ወንድም ቪክቶር ማልኮቭን በቁጥጥር ሥር አዋሏቸው። በዚህ ጊዜ ቪክቶር ፖሊሶቹን እንዲህ አላቸው፦ “ጠበኛ በመሆኔ ለሰባት ዓመት ታስሬ ነበር፤ ከዚያም የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። አሁን ደግሞ ምሥራቹን በመስበኬ ልታስሩኝ ትፈልጋላችሁ?”

ወንድም ዬቭጌኒ ድዬሽኮ ሌሎቹ ወንድሞች ከተያዙ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ተደረገ። ዬቭጌኒ “ይህ ሊደርስብኝ እንደሚችል አስቀድሜ አስቤ ስለነበር ሁኔታውን መቀበል አልከበደኝም” ብሏል። ይሖዋ ለኢያሱ የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ እሱንም አበረታትቶታል፦ “ደፋርና ብርቱ ሁን . . . አምላክህ ይሖዋ በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር ስለሆነ አትሸበር፤ አትፍራ።” (ኢያሱ 1:9) ዬቭጌኒ “ይህ ጥቅስ ደፋር እንድንሆን የሚያበረታታን ከመሆኑም ሌላ የይሖዋ ድጋፍ እንደማይለየን ማረጋገጫ ይሰጠናል” ብሏል።

ሩስላን ማረፊያ ቤት በነበረበት ጊዜ ኢየሱስ በማቴዎስ 6:34 ላይ በተናገረው ሐሳብ ላይ ያሰላስል እንደነበር ገልጿል። ሩስላን ምን ሊያጋጥመው እንደሚችል በማሰብ ከመስጋት ይልቅ ምን ያደርግ እንደነበር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ደብዳቤ በመጻፍ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ እንዲሁም አብረውኝ ለታሰሩ ሰዎች ስለ እውነት በመመሥከር ተጠምጄ ነበር። በጭንቀት ለመዋጥ የሚሆን ጊዜ አልነበረኝም።”

መጋቢት 2020 የፌዴራል ደህንነት ቢሮ መርማሪ የሆነው ብዬዝሩኮቭ በአራቱ ወንድሞች ላይ የተጣለው ገደብ እንዲቀነስ አደረገ፤ በመሆኑም ከቁም እስር ተለቀቁ። ወደ አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በማረፊያ ቤትና በቁም እስር አሳልፈዋል። ይህ ለውጥ የመጣው እነዚህ ታማኝ ወንድሞቻችን ታስረው በነበሩበት ወቅት አዎንታዊና ተባባሪ ስለነበሩ ነው። መርማሪው እነዚህ ወንድሞች ተጨማሪ ነፃነት እንዲያገኙ ያደረገው፣ የምርመራውን ሂደት እንደማያስተጓጉሉ ወይም ከዚህ በኋላ ለጥያቄ ቢጠሩ እንደማያስቸግሩ ስለተማመነ ነው።

የሚያሳዝነው፣ ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ቪክቶር በሞት አንቀላፋ። ብዙዎች፣ ቪክቶር በማረፊያ ቤት በነበረበት ወቅት መጥፎ ሁኔታ ውስጥ መቆየቱ እንዲሁም በወንጀል መከሰሱ ያስከተለበት ውጥረት በጤንነቱ ላይ ከባድ ጉዳት እንዳስከተለ ይሰማቸዋል።

ሩስላን፣ ቫለሪ እና ዬቭጌኒ የወንድም ቪክቶርንና እንደ እሱ በታማኝነት እስከ መጨረሻው የጸኑ በርካታ ክርስቲያኖችን ምሳሌ ለመከተል ቆርጠዋል። እነዚህ ወንድሞች መንፈሳዊነታቸውን መጠበቃቸው፣ የደረሰባቸውን ስደት ከመቋቋም ባለፈ በደስታ ለመጽናት አስችሏቸዋል።

ቫለሪ እንዲህ ብሏል፦ “ከታሰርኩ በኋላ ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ ችያለሁ። የአሁኑን ያህል ወደ ይሖዋ እንደቀረብኩ ተሰምቶኝ አያውቅም። መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሬ አነብባለሁ። እስር ቤት ደስ የሚል ቦታ እንዳልሆነ አይካድም፤ ሆኖም የይሖዋ እርዳታ የሌላቸው ሰዎች እንኳ ሁኔታውን ተቋቁመው ያልፋሉ። እኛ ደግሞ የይሖዋ እርዳታ ስላለን መጽናት እንደምንችል ምንም ጥያቄ የለውም።”

ዬቭጌኒ ደግሞ ይሖዋ እንደሚረዳን ይበልጥ እርግጠኛ መሆኑን ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “በተለይም በጣም ከባድ ፈተና በሚገጥመን ወቅት አባታችን እንደሚረዳን እርግጠኛ ሆኛለሁ። ስለዚህ ‘ወደፊት ምን ዓይነት ፈተና ያጋጥመኝ ይሆን?’ ብዬ አልሰጋም።”

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ምንም ይሁን ምን ዬቭጌኒ “እነዚህን ፈተናዎች በጽናት ለመወጣትና ታማኝነቴን ለመጠበቅ አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ቆርጫለሁ” ብሏል።

እነዚህ ወንድሞችና ቤተሰቦቻቸው በይሖዋ እርዳታ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ደስታቸውን ሳያጡ እንደሚጸኑ እንተማመናለን።—2 ተሰሎንቄ 3:5

^ አን.5 ፍርድ ቤቱ ብይን የሚያስተላልፍበትን ቀን አስቀድሞ የማያሳውቅበት ጊዜ አለ።