ኅዳር 14, 2024
ዩናይትድ ስቴትስ
ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት አቅራቢያ ሰደድ እሳት ተነሳ
ኅዳር 9, 2024 በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት በስተ ሰሜን ምዕራብ ሁለት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ሰደድ እሳት ተነስቷል። ይህ ሰደድ እሳት በፍጥነት የሚዛመት ባይሆንም እስከ አሁን 2,000 ሄክታር የሚሆን ቦታ አቃጥሏል። የአካባቢው ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከሆነ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እስኪጥል ድረስ እሳቱ ሊቀጥል ይችላል።
በአሁኑ ወቅት ዎርዊክን፣ የራማፖ የግንባታ ፕሮጀክትን እና በተክሲዶ ፓርክ የሚገኘውን የብሮድካስት ስቱዲዮ ጨምሮ በአካባቢው ባሉ የቤቴል ሕንፃዎች ላይ የተጋረጠ አደጋ የለም። ሆኖም ወንድሞቻችን ሁኔታውን በንቃት እየተከታተሉ ሲሆን የቤቴል ቤተሰብንና ንብረቶችን ከአደጋ ለመጠበቅ የጥንቃቄ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው። (ምሳሌ 22:3) የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ሆኖ የሚያገለግለው ወንድም ሉክ ሳላዲኖ እንዲህ ብሏል፦ “ሰደድ እሳቱ ሲነሳ ወዲያውኑ በዎርዊክ ሁኔታውን 24 ሰዓት የሚከታተል የወንድሞች ቡድን አደራጀን። የአደጋ ጊዜ ቡድኖች አዋቅረን በሕንፃው አቅራቢያ ያሉ የደረቁ ተክሎች እንዲወገዱና የሕንፃዎቹን ጣሪያዎች የሚሸፍኑት ተክሎች በውኃ እንዲርሱ እንዲሁም ሌሎች የአደጋ መከላከል ሥራዎች እንዲከናወኑ አድርገናል። የዎርዊክ ቤቴል ቤተሰብ አባላትም የአደጋ ጊዜ ቦርሳቸውን እንዲያዘጋጁና አስፈላጊ ከሆነ አካባቢውን ለመልቀቅ ዝግጁ እንዲሆኑ ማበረታቻ ሰጥተናል። ደግነቱ፣ እስከ አሁን ድረስ አካባቢውን ለመልቀቅ የሚያስገድድ ሁኔታ አልተፈጠረም።”
ወንድሞች በዎርዊክ ግቢ ውስጥ ያሉ ተክሎችና ዛፎች በእሳት እንዳይያያዙ በውኃ ሲያርሷቸው። ውስጠኛው ፎቶግራፍ፦ አንዲት ሄሊኮፕተር እሳቱ ላይ ውኃ ለመርጨት በአቅራቢያው ካለው ብሉ ሌክ የተባለ ሐይቅ ውኃ ስትወስድ
በአካባቢው ያሉ የእሳት እና የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች እሳቱን ለመቆጣጠር በትጋት እየሠሩ ይገኛሉ። በተለያዩ የቤቴል የሥራ ክፍሎች ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶችም ለእነዚህ ሠራተኞች ያላቸውን አድናቆት ለመግለጽ ምግብ፣ የሚጠጣ ውኃ እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ የተቀናጀ ጥረት እያደረጉ ነው። ወንድም ሳላዲኖ እንዲህ ብሏል፦ “እነዚህ ሠራተኞች ለእኛና በአቅራቢያችን ላሉት ሰዎች ሲሉ በዚህ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ በትጋት እያከናወኑ ላሉት ሥራ አመስጋኞች ነን።”
ይሖዋ በሰደድ እሳቱ የተነሳ አደጋ ለተጋረጠባቸው ሁሉ “ጥበብንና የማመዛዘን ችሎታን” እንዲሰጣቸው መጸለያችንን እንቀጥላለን።—ምሳሌ 3:21

