አማርኛ
ግንቦት 2025 ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በሁለት ቋንቋዎች ወጣ
https://cms-imgp.jw-cdn.org/img/p/702025062/univ/art/702025062_univ_sqr_xl.jpg

ሰኔ 2, 2025
ዓለም አቀፋዊ ዜና

ግንቦት 2025 ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በሁለት ቋንቋዎች ወጣ

ግንቦት 2025 ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በሁለት ቋንቋዎች ወጣ

ኪሲ

ግንቦት 25, 2025 የላይቤሪያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ዊንስተን ቤስትማን በኪሲ ቋንቋ ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ መውጣቱን አስታወቀ። ይህ ማስታወቂያ የተነገረው በጌኬዱ፣ ጊኒ በተካሄደው ልዩ ፕሮግራም ላይ ለተገኙ 1,029 የሚያህሉ ታዳሚዎች ነው። በተጨማሪም በፎያ፣ ላይቤሪያ እና በኮይንዱ፣ ሴራ ሊዮን ያሉ 2,467 ሰዎች ፕሮግራሙን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተከታትለዋል። በስብሰባው ላይ ለተገኙ በሙሉ የታተመው ቅጂ ተሰጥቷቸዋል። እንዲሁም መጽሐፉ jw.org እና JW Library አፕሊኬሽን ላይ ወዲያውኑ ለተጠቃሚዎች ተለቋል። በተጨማሪም የኪሲ አዲስ ዓለም ትርጉም የድምፅ ቅጂ ደረጃ በደረጃ እንደሚወጣ ተገልጿል።

ጊኒ፣ ላይቤሪያ እና ሴራ ሊዮን በሚዋሰኑበት ኪሲላንድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩ አንድ ሚሊዮን ገደማ ሰዎች የኪሲ ቋንቋን ይናገራሉ። ከ1200 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች በላይቤሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ በኪሲ ቋንቋ በሚመሩ 29 ጉባኤዎችና አንድ ቡድን ውስጥ ያገለግላሉ። እነዚህ የኪሲ ቋንቋ ተናጋሪ ወንድሞች እና እህቶች ይሖዋ የሚለው የአምላክ የግል ስም የሚገኝበትን ሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል።

የሰለሞን ደሴቶች ፒጅን

ግንቦት 25, 2025 የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ዊንደር ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሰለሞን ደሴቶች ፒጅን መውጣቱን አበሰረ። ማስታወቂያው የተነገረው የሰለሞን ደሴቶች ዋና ከተማ በሆነችው በሆኒያራ በተካሄደ ልዩ ፕሮግራም ላይ ነው። በአጠቃላይ 2,317 ሰዎች በፕሮግራሙ ላይ በአካል ተገኝተዋል። በማሊያታ ደሴት በሚገኙ ሁለት ቦታዎች የተሰበሰቡ ሌሎች 1,695 ተሰብሳቢዎች ደግሞ ፕሮግራሙን በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ተከታትለዋል። በሰለሞን ደሴቶች ፒጅን የተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም የታተመ ቅጂ ለሁሉም ተሰብሳቢዎች ታድሏል። በተጨማሪም መጽሐፉ jw.org እና JW Library አፕሊኬሽን ላይ ወጥቷል።

ምሥራቹ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰለሞን ደሴቶች የተሰበከው በ1953 ነው። በዛሬው ጊዜ በዚህች አገር ወደ 757,000 የሚጠጉ ሰዎች የሚኖሩ ሲሆን ከ70 የሚበልጡ የአገሬው ቋንቋዎች ይነገራሉ። የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ እንግሊዝኛ ቢሆንም በስፋት የሚነገረው ቋንቋ የሰለሞን ደሴቶች ፒጅን ነው። በአሁኑ ጊዜ በመላው አገሪቱ የሰለሞን ደሴቶች ፒጅን የሚናገሩ 2,100 ገደማ የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች ያሉ ሲሆን እነዚህ ወንድሞችና እህቶች በ38 ጉባኤዎች ውስጥ እያገለገሉ ነው።