የይሖዋ ምሥክሮች በፊሽኪል የሚገነቡትን አዲስ ድጋፍ ሰጪ ማዕከል መግቢያ የሚያሳይ ሥዕላዊ መግለጫ

ታኅሣሥ 21, 2023
ዓለም አቀፋዊ ዜና

በኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የፊሽኪል ከተማ የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ ድጋፍ ሰጪ ማዕከል እንዲገነቡ ፈቃድ ሰጠ

በኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የፊሽኪል ከተማ የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ ድጋፍ ሰጪ ማዕከል እንዲገነቡ ፈቃድ ሰጠ

ጥቅምት 27, 2023 በፊሽኪል፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ የቤቴል ይዞታ የሆነ ቦታ ላይ አዲስ ግንባታ እንዲካሄድ የከተማው የሕንፃ ንድፍ ቦርድ ፈቃድ ሰጠ። በመሆኑም በፊሽኪል የድጋፍ ሰጪ ማዕከሉን ግንባታ አሁኑኑ መጀመር እንችላለን ማለት ነው።

በፊሽኪል ያለው ቤቴል በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ካለው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት በስተ ሰሜን 64 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። በፊሽኪል የሚያገለግሉት ወንድሞችና እህቶች ከኮምፒውተርና ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ያከናውናሉ።

አዲሱ ግንባታ የሚካሄደው አሁን ካሉት የቤቴል ሕንፃዎች ማዶ በሚገኘው 23 ሄክታር ስፋት ያለው መሬት ላይ ነው። ድጋፍ ሰጪ ማዕከሉ 4,366 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን ባለአንድ ፎቅ የቢሮ ሕንፃ፣ 1,393 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን የጥገና ክፍሉ የሚገኝበትን ሕንፃ እንዲሁም 1,393 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን የተለያዩ መዝናኛዎች የሚኖሩበትን ሕንፃ ያካትታል። ከሕንፃው ውጭም የመዝናኛ አካባቢዎች እንዲገነቡ ታስቧል። የሕንፃዎቹ ንድፍ አካባቢው ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።

በፊሽኪል የሚገነባውን አዲስ ድጋፍ ሰጪ ማዕከል የሚያሳይ ሥዕላዊ መግለጫ፤ ሥዕላዊ መግለጫው (1) ባለአንድ ፎቅ የቢሮ ሕንፃውን፣ (2) የተለያዩ መዝናኛዎች የሚገኙበትን ሕንፃ፣ (3) የጥገና ክፍሉ የሚኖርበትን ሕንፃ እንዲሁም (4) ከሕንፃው ውጭ ያለውን የመዝናኛ ቦታ ያሳያል

አብዛኛው ሥራ በወንድሞች ሳይሆን በተለያዩ የሕንፃ ተቋራጮች የሚከናወን ቢሆንም ሥራውን የሚከታተሉ በቤቴል የሚያገለግሉ የተወሰኑ ወንድሞች ይኖራሉ። ግንባታው ጥቅምት 2025 ላይ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

በአሁኑ ጊዜ በፊሽኪል የሚኖርና በቢሮ ድጋፍ ዘርፍ የሚሠራ ጄሰን ኬል የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “እስካሁን ድረስ በፊሽኪል ቤቴል የመኖሪያ ክፍሎች ብቻ እንጂ ነዋሪዎቹ አብረው ጊዜ ማሳለፍ የሚችሉበት የጋራ ቦታ አልነበረም። አዲሶቹ ሕንፃዎች ግን ብዙዎቻችን እርስ በርስ መገናኘትና አብረን መሥራት የምንችልባቸው ቦታዎች ይኖሯቸዋል። ይህ አዲስ ድጋፍ ሰጪ ማዕከል ተገንብቶ የሚጠናቀቅበትን ጊዜ በጉጉት እንጠብቃለን!”

አሁን በፊሽኪል፣ ኒው ዮርክ ያሉት የቤቴል የመኖሪያ ቤቶች

በፊሽኪል ቤቴል የሚያገለግሉትን ወንድሞችና እህቶች አንድነት ይበልጥ የሚያጠናክር አዲስ የግንባታ ፕሮጀክት መታቀዱን በመስማታችን በጣም ተደስተናል። ይሖዋ ይህን አስደሳች ፕሮጀክት አብዝቶ እንዲባርከው እንጸልያለን።—መዝሙር 127:1