አማርኛ
ሰኔ 2025 የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በአራት ቋንቋዎች ወጡ
https://cms-imgp.jw-cdn.org/img/p/702025078/univ/art/702025078_univ_sqr_xl.jpg

ሐምሌ 11, 2025
ዓለም አቀፋዊ ዜና

ሰኔ 2025 የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በአራት ቋንቋዎች ወጡ

ሰኔ 2025 የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በአራት ቋንቋዎች ወጡ

የአንጎላ ምልክት ቋንቋ

የአንጎላ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ቴይለር ቦርንሻይን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በአንጎላ ምልክት ቋንቋ መውጣቱን ሰኔ 13, 2025 አብስሯል። ይህ ዜና የተበሰረው ሉዋንዳ በተባለችው የአንጎላ ከተማ በተካሄደው የ2025 “ንጹሕ አምልኮ” የክልል ስብሰባ ላይ ሲሆን 1,540 ተሰብሳቢዎች ነበሩ። ይህ ትርጉም jw.org ድረ ገጽ ላይ እንዲሁም JW Library እና JW Library Sign Language አፕሊኬሽኖች ላይ ወዲያውኑ ተለቅቋል።

በአንጎላ ምልክት ቋንቋ ሙሉው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ሲወጣ ይህ የመጀመሪያው ነው። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይዘት ያላቸው ነገሮችን በዚህ ቋንቋ ማዘጋጀት የጀመሩት በ2013 ነው። በአሁኑ ወቅት በመላው አንጎላ በምልክት ቋንቋ በሚካሄዱ 37 ጉባኤዎችና 11 ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ 1,100 ገደማ ወንድሞችና እህቶች አሉ።

የቬኔዙዌላ ምልክት ቋንቋ

የቬኔዙዌላ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ኤድጋርዶ ሎፔዝ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቬኔዙዌላ ምልክት ቋንቋ መውጣቱን ሰኔ 14, 2025 አብስሯል። ይህ ዜና የተበሰረው ላ ቪክቶሪያ ውስጥ በሚገኘው የቬኔዙዌላ ቅርንጫፍ ቢሮ በተካሄደ ልዩ ስብሰባ ላይ ሲሆን በአካል የተገኙ 309 ተሰብሳቢዎች ነበሩ። ተጨማሪ 1,215 ሰዎች በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ፕሮግራሙን በቀጥታ ተከታትለዋል። ሌሎች 918 ሰዎች ደግሞ የተቀዳውን ፕሮግራም በዚያው ሳምንት በሌላ ቀን ተመልክተዋል። ይህ ትርጉም jw.org ድረ ገጽ ላይ እንዲሁም JW Library እና JW Library Sign Language አፕሊኬሽኖች ላይ ወዲያውኑ ተለቅቋል።

በአሁኑ ወቅት ከ100,000 በላይ ሰዎች የቬኔዙዌላ ምልክት ቋንቋን ይጠቀማሉ። በመላ አገሪቱ በምልክት ቋንቋ በሚካሄዱ 33 ጉባኤዎችና 34 ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ ከ1,300 በላይ ወንድሞችና እህቶች አሉ።

ኪቱባ

የኮንጎ (ኪንሻሳ) ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም እምቤቴ ፋንሷ ሰኔ 20, 2025 እንዳበሰረው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም እንዲሁም የዘፍጥረት እና የዘፀአት መጻሕፍት በኪቱባ ቋንቋ ወጥተዋል። ማስታወቂያው የተነገረው በ2025ቱ “ንጹሕ አምልኮ” የክልል ስብሰባ ላይ ለታደሙ 1,276 ተሰብሳቢዎች ሲሆን ስብሰባው የተካሄደው የኮንጎ ሪፑብሊክ ከተማ በሆነችው በፖይንተ ንዋ በሚገኝ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ውስጥ ነው። የዚህ ትርጉም ኤሌክትሮኒክ ቅጂዎች jw.org እና JW Library አፕሊኬሽን ላይ ወዲያውኑ ተለቅቀዋል። በተጨማሪም የተወሰኑ የታተሙ ቅጂዎች በክልል ስብሰባው ላይ በአካል ለተገኙ ተሰብሳቢዎች ታድለዋል። ጉባኤዎች በጊዜ ሂደት የታተሙ ቅጂዎች ይደርሷቸዋል።

አንጎላ፣ ኮንጎ ሪፑብሊክ እና ጋቦን ውስጥ ከ12 ሚሊዮን በላይ ኪቱባ ተናጋሪዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል በ35 የኪቱባ ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉት ከ2,500 በላይ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይገኙበታል።

የኮሎምቢያ ምልክት ቋንቋ

የኮሎምቢያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም አንድሬስ ሜሂያ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በኮሎምቢያ ምልክት ቋንቋ መውጣቱን ሰኔ 21, 2025 አብስሯል። ይህ ዜና የተበሰረው ኮታ በተባለችው የኮሎምቢያ ከተማ በሚገኝ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ውስጥ በተካሄደ ልዩ ፕሮግራም ላይ ነው። በአካል የተገኙ ታዳሚዎች ብዛት 1,980 ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በመላ አገሪቱ ከ47 የተለያዩ ቦታዎች ሆነው በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ፕሮግራሙን በቀጥታ ተከታትለዋል። ይህ ትርጉም jw.org ድረ ገጽ ላይ እንዲሁም JW Library እና JW Library Sign Language አፕሊኬሽኖች ላይ ወዲያውኑ ተለቅቋል።

ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ በኮሎምቢያ ምልክት ቋንቋ ተተርጉሞ ሲወጣ ይህ የመጀመሪያው ነው። በአሁኑ ወቅት ከ500,000 በላይ ሰዎች የኮሎምቢያ ምልክት ቋንቋን እንደሚጠቀሙ ይገመታል። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይዘት ያላቸው ነገሮችን በዚህ ቋንቋ ማዘጋጀት ከጀመሩ 25 ዓመታት አስቆጥረዋል። በመላ አገሪቱ በሚገኙ 35 የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎችና 11 ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ ከ1,400 በላይ ወንድሞችና እህቶች ሙሉውን አዲስ ዓለም ትርጉም በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል፤ ለአገልግሎት፣ ለግል ጥናትና ለጉባኤ ስብሰባዎች ሊጠቀሙበትም ጓጉተዋል።