አማርኛ
ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በሩሲያ ምልክት ቋንቋ ወጣ
https://cms-imgp.jw-cdn.org/img/p/702023102/univ/art/702023102_univ_sqr_xl.jpg

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ማርክ ሳንደርሰን አዲስ ዓለም ትርጉም በሩሲያ ምልክት ቋንቋ መውጣቱን አበሰረ። አስፋፊዎች ከተለያዩ ቦታዎች ሆነው ፕሮግራሙን ተከታትለዋል፦ (ከላይ በስተ ግራ አንስቶ ዙሪያውን) ዩክሬን፤ ላትቪያ፤ አስታና፣ ካዛክስታን እና አልማቲ፣ ካዛክስታን

ግንቦት 31, 2023
ዓለም አቀፋዊ ዜና

ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በሩሲያ ምልክት ቋንቋ ወጣ

ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በሩሲያ ምልክት ቋንቋ ወጣ

ግንቦት 27, 2023 በሩሲያ ምልክት ቋንቋ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ወጣ፤ የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ማርክ ሳንደርሰን አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሩሲያ ምልክት ቋንቋ መውጣቱን አበሰረ። በዕለቱ በተካሄደው ልዩ ፕሮግራም ላይ በድምሩ 148 ሰዎች በአካል ተገኝተዋል። በ15 አገራት ያሉ ሌሎች 5,000 ሰዎች ደግሞ ፕሮግራሙን በቀጥታ ስርጭት ተከታትለዋል፣ ወይም የተቀዳውን ተመልክተዋል። አዲሱ መጽሐፍ ቅዱስ አሁን jw.org ላይም ሆነ JW Library Sign Language አፕሊኬሽን ላይ ይገኛል።

መስማት የተሳነው አንድ ወንድም እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፦ “በምልክት ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ ስመለከት፣ ኢየሱስ በሰዎች ሥቃይ አንጀቱ ሲላወስ በአካል የማይ ያህል ሆኖ ይሰማኛል። ልቤ በጣም ይነካል!”

በሩሲያ ምልክት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ከመውጣቱ በፊት፣ መስማት የተሳናቸው ብዙ አስፋፊዎች የሚጠቀሙት በሩሲያኛ የተዘጋጀውን የታተመ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። ይሁንና የሩሲያ ምልክት ቋንቋ በጣም ገላጭ በመሆኑ አንዳንዶቹ አስፋፊዎች በታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙትን በርካታ አገላለጾች መረዳት ይከብዳቸው ነበር።

ለምሳሌ ያህል፣ በ1 ነገሥት ምዕራፍ 17 ላይ የሰራፕታዋ መበለት እሷና ልጇ ያለቻቸውን ምግብ በልተው እንደሚሞቱ ለነቢዩ ኤልያስ ነግራው ነበር። አንዳንድ መስማት የተሳናቸው አስፋፊዎች ይህን ታሪክ የሚረዱት የመበለቷ ምግብ የተመረዘ እንደሆነ አድርገው ነበር። በሩሲያ ምልክት ቋንቋ በተዘጋጀው ትርጉም ላይ ግን ከዚያ ምግብ ውጭ ያላቸውን ነገር ሁሉ እንደጨረሱ በግልጽ ተቀምጧል።

በተለያዩ አገራት የሚገኙና የተለያየ ባሕል ያላቸው ሰዎች የሩሲያ ምልክት ቋንቋን ይጠቀማሉ። በመሆኑም ተርጓሚዎቹ፣ ቋንቋው በየአካባቢው ያለውን ልዩነት ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈልጓቸዋል። ከተርጓሚዎቹ አንዱ እንዲህ ሲል አስረድቷል፦ “‘ኃጢአት’ ለማለት የምንጠቀምበት አንድ ምልክት፣ በሌላ አካባቢ ‘አምላክ’ የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል። በአንድ አካባቢ ‘ደቀ መዝሙር’ ለማለት የሚጠቀሙበት ምልክት ደግሞ በሌላ አካባቢ ‘መጨረሻ’ ወይም ‘ድሃ’ ማለት ሊሆን ይችላል። ከዚህ አንጻር የትርጉም ቡድኑ፣ በብዙኃኑ ዘንድ የሚታወቁ ምልክቶችን ለመጠቀም ጥረት አድርጓል።”

በሩሲያ ምልክት ቋንቋ ውድ ስጦታ ካገኙት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር አብረን እንደሰታለን፤ የዚህ ገጸ በረከት ምንጭ የሆነውን ይሖዋንም ማመስገን እንፈልጋለን።—ምሳሌ 10:22