አማርኛ
የስሪ ላንካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት 11 ዓመት ከፈጀ የፍርድ ሂደት በኋላ ለይሖዋ ምሥክሮች ፈረደ
https://cms-imgp.jw-cdn.org/img/p/702025113/univ/art/702025113_univ_sqr_xl.jpg

ሐምሌ 18, 2025
ስሪ ላንካ

በስተ ግራ፦ የስሪ ላንካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕንፃ። በስተ ቀኝ (ከግራ ወደ ቀኝ)፦ እህት ማልካንቲ፣ እህት ሱኒታ ካልያኒ ደ ሲልቫ፣ እህት ኒሩጃ እና እህት ቲሱሪ አማ ሊያናጅ፤ ግንቦት 2025

የስሪ ላንካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት 11 ዓመት ከፈጀ የፍርድ ሂደት በኋላ ለይሖዋ ምሥክሮች ፈረደ

የስሪ ላንካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት 11 ዓመት ከፈጀ የፍርድ ሂደት በኋላ ለይሖዋ ምሥክሮች ፈረደ

ግንቦት 21, 2025 የስሪ ላንካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አንድ ወሳኝ ብይን አስተላልፏል፤ ይህ ብይን ከሃይማኖታዊ ነፃነት ጋር በተያያዘ ለአገሪቱ ትልቅ እመርታ ነው። አራት እህቶቻችንን የሚመለከተው የክስ እና የፍርድ ሂደት 11 ዓመታትን ፈጅቷል፤ ፍርድ ቤቱ ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ ፖሊሶች የፈጸሙት ተግባር እምነትን ሰላማዊ በሆነ መንገድ የመናገር መብትን የሚጥስ እንደሆነ አረጋግጧል። ከተለያዩ ምክንያቶች አንጻር ሲታይ ይህ አዎንታዊ ብይን በስሪ ላንካ ላሉ የይሖዋ ሕዝቦች ወሳኝ የሆነ ድል ነው። በአንድ በኩል የይሖዋ ምሥክሮች እምነታቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለሌሎች የመናገር ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳላቸው ያረጋግጣል። ከዚህም ባለፈ በመላው ደቡባዊ እስያ ሃይማኖታዊ ነፃነትን ለማስከበር በሚደረጉ ጥረቶች ተጠቃሽ ሊሆን የሚችል ብይን ነው።

ጉዳዩ የተፈጸመው ጥቅምት 2014 በደቡባዊ ስሪ ላንካ፣ ኪራማ በተባለች መንደር ውስጥ ነው። አራት እህቶች እየሰበኩ ሳለ ነገሩ ያስቆጣቸው ሰዎች በድንገት ሆ ብለው በመውጣት እህቶችን ለማወክ ሞከሩ። ፖሊሶች አካባቢው ላይ ሲደርሱ ሁከተኞቹን ከመበተን ይልቅ ምንም ወንጀል ያልሠሩትን አራት እህቶች በቁጥጥር ሥር አዋሏቸው። ፖሊሶቹ ክስ ሳይመሠርቱ እህቶችን እስር ቤት አሳደሯቸው፤ አደገኛ ወንጀለኞች ባሉባቸው ክፍሎች ውስጥ ተለያይተው እንዲታሰሩ አደረጉ። ያም ቢሆን እህቶቻችን በይሖዋ በመታመን ሳይረበሹ ያንን ከባድ ምሽት አሳለፉ። በቀጣዩ ቀን ከእስር ተለቀቁ።

ከአንድ ወር በኋላ ማለትም ኅዳር 2014 የአካባቢው ዳኛ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ፋይሉ እንዲዘጋ ወሰኑ። ይሁንና አራቱ እህቶች ሰብዓዊ መብታቸው ስለ መጣሱ ሐቃቸው እንዲረጋገጥ ስለፈለጉ ለሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና ለስሪ ላንካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታቸውን አስገቡ። በመጨረሻ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ግንቦት 2025 ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን ፓሊሶቹ በዕለቱ የፈጸሙት ተግባር የእህቶችን መብት የሚጥስ እንደሆነ አረጋግጧል፤ የአካባቢው የፖሊስ ኃላፊና የክልሉ መንግሥት ለሁሉም እህቶች የገንዘብ ካሳ እንዲከፍሉም ፍርድ ቤቱ በይኗል። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ካስተላለፈው ውሳኔ በኋላ እህት ማልካንቲ እንዲህ ብላለች፦ “ይህ ሕጋዊ ድል የእኛ የአራታችን ብቻ አይደለም። በስሪ ላንካ ላሉ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በሙሉ ትልቅ ድል ነው፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የማምለክ መብታቸው እንዲጸና አድርጓል። አምላክ በኢሳይያስ 54:17 ላይ የሰጠው ‘አንቺን ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ ይከሽፋል’ የሚለው ዋስትና አሁን ይበልጥ እውን ሆኖልኛል።”

“ሙሉ በሙሉ ለአምላክ በማደር . . . በጸጥታና በተረጋጋ ሁኔታ መኖራችንን [የመቀጠል]” መብታችንን የሚያጸናው ይህ ሕጋዊ ድል ለስሪ ላንካ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ብቻ ሳይሆን ለእኛም ትልቅ ደስታ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 2:2