አማርኛ
በሩሲያ ታስረው የነበሩ ሦስት ወንድሞች ተፈቱ
https://cms-imgp.jw-cdn.org/img/p/702025061/univ/art/702025061_univ_sqr_xl.jpg

ሚያዝያ 17, 2025
ሩሲያ

ወንድሞች ከእስር ከተለቀቁ በኋላ፦ ቭላድሚር ሜልኒክ ከባለቤቱና ከሴት ልጆቹ ጋር (በስተ ግራ)፣ ቭላድሚር ፒስካሬቭ (መሃል)፣ አርተር ፑቲንሴቭ ከባለቤቱ ጋር (በስተ ቀኝ)

በሩሲያ ታስረው የነበሩ ሦስት ወንድሞች ተፈቱ

በሩሲያ ታስረው የነበሩ ሦስት ወንድሞች ተፈቱ

ሚያዝያ 9, 2025 ወንድም ቭላድሚር ሜልኒክ፣ ወንድም ቭላድሚር ፒስካሬቭ እና ወንድም አርተር ፑቲንሴቭ ከእስር ተለቅቀዋል። እነዚህ ወንድሞች ጥቅምት 13, 2023 ጥፋተኛ ተብለው የስድስት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው እንደነበር ይታወሳል። ከታኅሣሥ 2020 አንስቶ በቁጥጥር ሥር የቆዩበትን ጊዜ ታሳቢ በማድረግ አሁን የእስራት ፍርዳቸው እንደተጠናቀቀ ተቆጥሮላቸዋል።

ቭላድሚር ሜልኒክ የተወሰደበት እስር ቤት ክሱ ከታየበት ቦታ 1,400 ኪሎ ሜትር ገደማ ይርቃል፤ በዚህም የተነሳ ቤተሰቡ እሱን መጠየቅ ከባድ ሆኖባቸው ነበር። በተጨማሪም እስር ቤት ሳለ፣ ከማንም ጋር እንዳይገናኝ ብቻውን አንድ ክፍል ውስጥ የታሰረበት ጊዜ ነበረ። የቭላድሚር ሚስት ኢሪና፣ ባለቤቷ እንዲጸና የረዳውን ነገር ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ቭላድሚር፣ ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ጠንካራ እምነት አለው፤ ያጋጠሙትን ብዙ ችግሮች በጽናት ለማለፍ የረዳው ይህ ነው። አዘውትሮ መጸለዩ ትኩረቱ ምንጊዜም በተስፋው ላይ እንዲሆን እንዲሁም ተዘናግቶ አቋሙን እንዳያላላ ረድቶታል።”

ቭላድሚር ፒስካሬቭ ከእስር ከተለቀቀ በኋላ ባለቤቱን ታትያናን ሲያነጋግር፤ ታትያና የጉልበት ሥራ ተፈርዶባት ማረሚያ ቤት ነች

ሦስቱም ወንድሞች ለአራት ዓመት ተኩል ገደማ ከቤተሰባቸው ለመለየት ተገድደዋል። ቭላድሚር ፒስካሬቭ ግን ከዚህ በኋላም ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከሚስቱ ተለይቶ መኖሩ የግድ ነው። መጋቢት 1, 2024 የሁለት ዓመት የጉልበት ሥራ የተፈረደባት ባለቤቱ ታትያና አሁንም ማረሚያ ቤት ነች። ታትያና ያሳለፉት ነገር የቀየራቸው እንዴት እንደሆነ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥ ስናልፍ ለይሖዋ፣ አንዳችን ለሌላው እንዲሁም ለጎረቤቶቻችን ያለን ፍቅር ጨመረ እንጂ ፈጽሞ አልቀነሰም። ይህን ሊቀይር የሚችል አንድም ነገር የለም።”

አርተር ፑቲንሴቭ ክርስቲያናዊ ባሕርያት ማሳየቱ በእስር ቤት ባሳለፈው ጊዜ ያጋጠሙትን የተለያዩ ተፈታታኝ ሁኔታዎች በስኬት ለማለፍ አስችሎታል። ባለቤቱ ልዩድሚላ እንዲህ ብላለች፦ “አብረውት የታሰሩት ሰዎች ችግር ሲፈጥሩበት ምላሽ የሚሰጠው ለእነሱ ምግቡን በማጋራት፣ በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት በማሳየትና ተግባብቶ ለመኖር የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ነው። ሰላም ፈጣሪ ሰው ነው።” ይህ በእንዲህ እንዳለ አርተር እና ልዩድሚላ በመንፈሳዊ ቤተሰባቸው አማካኝነት የይሖዋን ድጋፍ ማየት ችለዋል። ልዩድሚላ እንዲህ ስትል ታስታውሳለች፦ “ይሖዋ ችግር ገጥሞን መቼም ብቻችንን ትቶን አያውቅም። ካሳለፍነው ነገር እንደተማርነው ምንም ዓይነት ሕይወት የሚያመሰቃቅል ነገር ቢገጥመን ይሖዋ ከምንችለው በላይ እንዲሆንብን አይፈቅድም። ዋናው ነገር እኛ በእሱ ሙሉ በሙሉ መታመናችን ነው።”

ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ለእነዚህ ወንድሞችና እህቶች ላደረገው ድጋፍና እንክብካቤ እናመሰግነዋለን። ፈተናቸው አሁንም ባያበቃም ይሖዋ “ለተጨቆኑ ሁሉ በጽድቅና በፍትሕ እርምጃ [እንደሚወስድ]” እንተማመናለን።—መዝሙር 103:6