በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ነቅታችሁ ጠብቁ!

ፖለቲካ ይህን ያህል ከፋፋይ የሆነው ለምንድን ነው?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ፖለቲካ ይህን ያህል ከፋፋይ የሆነው ለምንድን ነው?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 በዓለም ዙሪያ በተለያዩ አገሮች ውስጥ የፖለቲካ ቅራኔ የሚፈጥረው ክፍፍል እየተስተዋለ ነው። አንድ የምርምር ማዕከል በ2022 ይህን ጉዳይ የሚመለከት የዳሰሳ ጥናት አድርጎ ነበር፤ “የዳሰሳ ጥናት በተደረገባቸው 19 አገራት ውስጥ 65 በመቶ የሚሆኑት አዋቂዎች እንደተናገሩት በአገራቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በሚደግፉ ሰዎች መካከል ጠንካራ እንዲያውም በጣም ጠንካራ የሐሳብ ልዩነት አለ።”

 አንተ በምትኖርበት አካባቢስ ሁኔታው እንዴት ነው? የፖለቲካ ክፍፍል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መጥቷል? ለመሆኑ ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? መፍትሔስ ይኖረው ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ተመልከት።

ከፋፋይ ባሕርያት

 መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ያለንበትን ጊዜ የሚጠራው ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ብሎ ነው፤ በዚህ ዘመን ብዙ ሰዎች ለአንድነት ፀር የሆኑ ባሕርያት እንደሚኖሯቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ይጠቁማል።

  •   “በመጨረሻዎቹ ቀናት ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን [ይመጣል።] ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ . . . ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ” ይሆናሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-3

 ብዙ ሰዎች በቅንነት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም መንግሥታት ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተዳደር አልሆነላቸውም። ተቃራኒ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ችግሮችን ለመፍታት በጋራ መሥራት እየከበዳቸው እንዲያውም የማይቻል እየሆነባቸው ነው። ይህ አዝማሚያ መጽሐፍ ቅዱስ ከረጅም ጊዜ በፊት የገለጸውን ሐቅ እውነተኝነት የሚያሳይ ነው።

  •   “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።”—መክብብ 8:9

 ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይህን ችግር ለዘለቄታው የሚፈታ መንግሥት እንዳለ ያበስረናል፤ የዚህ መንግሥት መሪ ማኅበረሰቡን ቀስፈው የያዙትን ችግሮች ማስወገድ የሚችል ነው።

ግድ የሚሰጠው ብቁ መሪ

 መጽሐፍ ቅዱስ፣ በሌላ በየትኛውም መሪ ላይ የማናገኛቸው ብቃቶች ያሉት መሪ እንዳለ ይነግረናል፤ ይህ መሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ የሰውን ዘር አንድ ለማድረግና ሰላም ለማስፈን ኃይሉ፣ ሥልጣኑም ሆነ ፍላጎቱ አለው።

  •   “በእሱ ዘመን ጻድቅ ይለመልማል፤ . . . ሰላም ይበዛል።”—መዝሙር 72:7

  •   “ብሔራትም ሁሉ ያገለግሉታል።”—መዝሙር 72:11

 ኢየሱስ ከማንም የተሻለ መሪ ነው የምንለው ለሰዎች ግድ ስለሚሰጠውና ለተቸገሩት ስለሚራራ ነው፤ በተለይም በግፍ ለተጨቆኑት።

  •   “እርዳታ ለማግኘት የሚጮኸውን ድሃ፣ እንዲሁም ችግረኛውንና ረዳት የሌለውን ሁሉ ይታደጋልና። ለችግረኛውና ለድሃው ያዝናል፤ የድሆችንም ሕይወት ያድናል። ከጭቆናና ከግፍ ይታደጋቸዋል።”—መዝሙር 72:12-14

 ኢየሱስ ስለሚመራው የሰማይ መስተዳድር ማለትም ስለ አምላክ መንግሥት ተማር። ይህ መንግሥት አንተን የሚጠቅሙ ምን ነገሮች እንደሚያደርግ እንዲሁም ይህንን መንግሥት መደገፍ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለምን አትመለከትም?