በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ድንገተኛ የጤና እክል ሲያጋጥም

ድንገተኛ የጤና እክል ሲያጋጥም

 ያልተጠበቀ የጤና እክል አጋጥሞሃል? ከሆነ የጤና ችግር የሚያስከትለው አእምሯዊ፣ ስሜታዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ይገባሃል። ታዲያ ሁኔታውን ለመቋቋም ምን ሊረዳህ ይችላል? አንድ የቤተሰብህ አባል ወይም ጓደኛህ የጤና እክል ካጋጠመው እሱን መርዳት የምትችለውስ እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የሕክምና መጽሐፍ ባይሆንም ያጋጠመህን አስቸጋሪ ሁኔታ በተሻለ መንገድ ለመቋቋም የሚረዱ ጠቃሚ መመሪያዎችን ይዟል።

የጤና እክልን ለመቋቋም የሚረዱ ምክሮች

 •   የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርግ

   መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም።”—ማቴዎስ 9:12

   ምን ማለት ነው? አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሕክምና ባለሙያዎችን እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርግ።

   እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ በተቻለ መጠን ጥሩ ሕክምና ለማግኘት ሞክር። አንዳንድ ጊዜ የተለያዩ ሐኪሞችን ማማከር ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 14:15) ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር በግልጽ ተነጋገር፤ የሚናገሩትን ነገር ለመረዳት ጥረት አድርግ፤ እንዲሁም ስላጋጠመህ የጤና ችግር በትክክል መረዳታቸውን አረጋግጥ። (ምሳሌ 15:22) ስለ በሽታህና ስላሉህ የሕክምና አማራጮች ለማወቅ ሞክር። ስለ ሕመሙና ስለ ሕክምናው በደንብ መረዳትህ ሁኔታውን ለመቋቋም የሚያስችል ስሜታዊ ጥንካሬ እንዲኖርህና ጤንነትህን አስመልክቶ ጥሩ ውሳኔዎችን እንድታደርግ ይረዳሃል።

 •   ለጤና የሚጠቅሙ ልማዶችን አዳብር

   መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጥቂቱ ይጠቅማል።”—1 ጢሞቴዎስ 4:8

   ምን ማለት ነው? አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደማድረግ ያሉ ልማዶችን ማዳበርህ ለጤንነትህ ይጠቅምሃል።

   እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ አዘውትረህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርግ፤ ጤናማ የአመጋገብ ልማድ ይኑርህ፤ እንዲሁም በቂ እንቅልፍ ተኛ። ያጋጠመህ የጤና እክል የሚያሳድርብህ ጫና ቢኖርም ለጤና የሚጠቅሙ ልማዶችን ለማዳበር ጥረት ማድረግህ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ። እርግጥ የምታደርጋቸው ነገሮች የጤና ሁኔታህን ግምት ውስጥ ያስገቡ መሆን ይኖርባቸዋል፤ እንዲሁም ከምትወስደው ሕክምና ጋር መጋጨት የለባቸውም።

 •   የሌሎችን እርዳታ ጠይቅ

   መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።”—ምሳሌ 17:17

   ምን ማለት ነው? ጓደኞችህ ያጋጠመህን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቋቋም ሊረዱህ ይችላሉ።

   እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ለምታምነው ጓደኛህ ስሜትህን አውጥተህ ንገረው። እንዲህ ማድረግህ የጤና ችግሩ የፈጠረብህን አእምሯዊና ስሜታዊ ጫና ለማቅለል ይረዳሃል። ጓደኞችህና ቤተሰቦችህ በሌሎች መንገዶችም ሊረዱህ እንደሚፈልጉ ጥያቄ የለውም፤ ሆኖም ምን ዓይነት እርዳታ እንደሚያስፈልግህ ላያውቁ ይችላሉ። ስለዚህ ምን እንዲያደርጉልህ እንደምትፈልግ በግልጽ ንገራቸው። ከእነሱ በምትጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ሁን፤ እንዲሁም ለተደረገልህ ነገር ምንጊዜም አመስጋኝ ሁን። በሌላ በኩል ደግሞ ወዳጆችህ በአሳቢነት ተነሳስተው የሚያደርጉት ነገር ተጨማሪ ውጥረት እንዳይፈጥርብህ አንዳንድ ገደቦችን ማበጀት ሊኖርብህ ይችላል፤ ለምሳሌ ሰዎች መቼና ለስንት ሰዓት ሊጠይቁህ እንደሚችሉ መወሰን ትችላለህ።

 •   አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ

   መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኃኒት ነው፤ የተደቆሰ መንፈስ ግን ኃይል ያሟጥጣል።”—ምሳሌ 17:22

   ምን ማለት ነው? አዎንታዊ መሆንህና ተስፋ አለመቁረጥህ እንድትረጋጋና ያጋጠመህን አስጨናቂ የጤና እክል እንድትቋቋም ይረዳሃል።

   እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ካጋጠመህ ሁኔታ ጋር ለመላመድ ጥረት በምታደርግበት ጊዜ ከቁጥጥርህ ውጭ በሆኑ ነገሮች ላይ ሳይሆን ማድረግ በምትችላቸው ነገሮች ላይ አተኩር። ራስህን ከሌሎች ጋር ወይም ከመታመምህ በፊት ከነበርክበት ሁኔታ ጋር አታወዳድር። (ገላትያ 6:4) ምክንያታዊ የሆኑና ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦች አውጣ፤ እንዲህ ማድረግህ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖርህ ይረዳሃል። (ምሳሌ 24:10) ሁኔታህ በፈቀደ መጠን ሌሎችን ለመርዳት ጥረት አድርግ። መስጠት የሚያስገኘው ደስታ አሉታዊ ስሜቶችን ለማሸነፍ ይረዳሃል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35

አምላክ ያለብህን የጤና እክል ለመቋቋም ሊረዳህ ይችላል?

 ይሖዋ አምላክ a አንድ ሰው ያለበትን የጤና እክል እንዲቋቋም ሊረዳው እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እርግጥ ተአምራዊ ፈውስ እናገኛለን ብለን አንጠብቅም፤ ሆኖም አምላክ ለአገልጋዮቹ የሚከተሉትን ነገሮች በመስጠት ይረዳቸዋል፦

 ሰላም። ይሖዋ “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ [የሆነውን] የአምላክ ሰላም” ሊሰጠን ይችላል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ይህ ሰላም ወይም ውስጣዊ የመረጋጋት ስሜት በጭንቀት እንዳንዋጥ ይረዳናል። አምላክ ወደ እሱ በመጸለይ ጭንቀታቸውን ለሚነግሩት ሰዎች እንዲህ ያለውን ሰላም ይሰጣቸዋል።—1 ጴጥሮስ 5:7

 ጥበብ። ይሖዋ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳ ጥበብ ይሰጠናል። (ያዕቆብ 1:5) አንድ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ዘመን የማይሽራቸው ምክሮች በመማርና በሥራ ላይ በማዋል እንዲህ ያለውን ጥበብ ማግኘት ይችላል።

 አስደሳች የወደፊት ተስፋ። ይሖዋ ወደፊት “ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’” የማይልበት ጊዜ እንደሚመጣ ቃል ገብቶልናል። (ኢሳይያስ 33:24) ይህ ተስፋ ከባድ የጤና እክል ያለባቸው ብዙ ሰዎች አዎንታዊ አመለካከት ይዘው እንዲቀጥሉ ረድቷቸዋል።—ኤርምያስ 29:11, 12

a መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።—መዝሙር 83:18