በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተሻለ ጊዜ ይመጣል ብለን ተስፋ ማድረግ እንችላለን?

የተሻለ ጊዜ ይመጣል ብለን ተስፋ ማድረግ እንችላለን?

 ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ይሰማሃል? ዛሬ የሰው ልጆች በከባድ ችግሮች እየተጠቁ ቢሆንም ብዙ ሰዎች ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ያደርጋሉ። በእርግጥ ወደፊት ሁኔታዎች እንደሚሻሻሉ ለማሰብ የሚያበቃ ምክንያት አለን? አዎ! መጽሐፍ ቅዱስ፣ ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ አስተማማኝ ተስፋ ይሰጠናል።

 መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ ምንድን ነው?

 የሰው ልጆች ብዙ ተፈታታኝ ችግሮች እንዳሉባቸው መጽሐፍ ቅዱስም ይገልጻል። ሆኖም የሰው ልጆች ለዘላለም በእነዚህ ችግሮች እየተሠቃዩ እንደማይቀጥሉ ተስፋ ይሰጣል። እስቲ የተወሰኑ ምሳሌዎችን እንመልከት።

 •   ችግር፦ መኖሪያ ቤት ማጣት

   መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ፦ “ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ።”—ኢሳይያስ 65:21

   ይህ ተስፋ ሲፈጸም፦ ሰዎች የራሳቸው ቤት ይኖራቸዋል።

 •   ችግር፦ ሥራ ማጣት እና ድህነት

   መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ፦ “የመረጥኳቸው አገልጋዮቼም በእጃቸው ሥራ የተሟላ እርካታ ያገኛሉ።”—ኢሳይያስ 65:22

   ይህ ተስፋ ሲፈጸም፦ ሁሉም ሰው አርኪና አስደሳች ሥራ ይኖረዋል።

 •   ችግር፦ ፍትሕ ማጣት

   መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ፦ “መኳንንትም ፍትሕ ለማስፈን ይገዛሉ።”—ኢሳይያስ 32:1

   ይህ ተስፋ ሲፈጸም፦ ያን ጊዜ ማንም ሰው በዘሩ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ባለው ቦታ ወይም በኑሮ ደረጃው የተነሳ መድልዎ አይደርስበትም። ሁሉም ሰው ፍትሕ ያገኛል።

 •   ችግር፦ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና ረሃብ

   መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ፦ “በምድር ላይ እህል ይትረፈረፋል፤ በተራሮችም አናት ላይ በብዛት ይኖራል።”—መዝሙር 72:16

   ይህ ተስፋ ሲፈጸም፦ ሁሉም ሰው ለጤና ተስማሚ የሆነ ምግብ በበቂ መጠን ያገኛል። ጾሙን የሚያድር ወይም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚጠቃ ሰው አይኖርም።

 •   ችግር፦ ወንጀል እና ዓመፅ

   መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ፦ “እያንዳንዱም ከወይኑና ከበለስ ዛፉ ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም።”—ሚክያስ 4:4

   ይህ ተስፋ ሲፈጸም፦ ሁሉም ሰው ተረጋግቶና ያለስጋት ይኖራል፤ ምክንያቱም ያን ጊዜ ክፉ ሰዎች አይኖሩም፤ በምድር ላይ የሚኖሩት “ጻድቃን” ብቻ ናቸው።—መዝሙር 37:10, 29

 •   ችግር፦ ጦርነት

   መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ፦ “አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ ሰይፍ አያነሳም፤ ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይማሩም።”—ኢሳይያስ 2:4

   ይህ ተስፋ ሲፈጸም፦ በመላው ምድር ላይ ሰላም ይሰፍናል። (መዝሙር 72:7) ማንም ሰው በጦርነት የተነሳ ወዳጅ ዘመዱን አይነጠቅም፤ በጦርነት ምክንያት የሚሰደድ ሰውም አይኖርም።

 •   ችግር፦ ሕመም እና በሽታ

   መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ፦ “በዚያም የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’ አይልም።”—ኢሳይያስ 33:24

   ይህ ተስፋ ሲፈጸም፦ በአካል ጉዳት የሚጠቃ ወይም የሚታመም ሰው አይኖርም። (ኢሳይያስ 35:5, 6) ሌላው ቀርቶ ‘ሞት እንኳ እንደማይኖር’ መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይሰጣል።—ራእይ 21:4

 •   ችግር፦ በምድራችን ላይ የሚደርስ ጉዳት

   መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ፦ “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ሐሴት ያደርጋል፤ በረሃማው ቦታም ደስ ይለዋል፤ እንደ ሳሮን አበባም ያብባል።”—ኢሳይያስ 35:1

   ይህ ተስፋ ሲፈጸም፦ መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች፤ አምላክ መጀመሪያ እንዳሰበው ለሰው ልጆች ምቹ መኖሪያ ትሆናለች።—ዘፍጥረት 2:15፤ ኢሳይያስ 45:18

 መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠን ተስፋ ከእውነታ የራቀ እንደሆነ ይሰማሃል?

 እንደዚህ ቢሰማህ አያስገርምም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚናገረውን ሐሳብ ይበልጥ እንድትመረምር እናበረታታሃለን። ለምን? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጣቸው ተስፋዎች ሰዎች እንደሚሰጧቸው ተስፋዎች ወይም እንደሚናገሯቸው ትንበያዎች አይደሉም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ተስፋዎች የሰጠው አምላክ ራሱ ነው። ይህ ትልቅ ለውጥ ያመጣል የምንለው ለምንድን ነው?

 •   አምላክ ለቃሉ ታማኝ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ‘ሊዋሽ እንደማይችል’ ይናገራል። (ቲቶ 1:2) በተጨማሪም ስለ ወደፊቱ ጊዜ የመናገር ችሎታ ያለው አምላክ ብቻ ነው። (ኢሳይያስ 46:10) አምላክ የተናገረው ነገር ሁሉ ምንጊዜም እንደሚፈጸም የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ። ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የመጣ መሆኑን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።

 •   አምላክ ችግሮቻችንን ሁሉ የማስወገድ ችሎታ አለው። አምላክ “ደስ ያሰኘውን ነገር ሁሉ” ማድረግ እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (መዝሙር 135:5, 6) ይህም ሲባል፣ አምላክ የሰጣቸውን ተስፋዎች እንዳይፈጽም ሊያግደው የሚችል ምንም ነገር የለም ማለት ነው። ከዚህም ሌላ አምላክ ስለሚወደን እኛን የመርዳት ፍላጎትም አለው።—ዮሐንስ 3:16

 ‘አምላክ እኛን ለመርዳት ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ ካለው፣ ታዲያ አሁንም በብዙ ችግሮች የምንሠቃየው ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅ ከፈለግህ አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።

 ይህ ተስፋ እውን የሚሆነው እንዴት ነው?

 አምላክ፣ የሰጣቸው ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ መንግሥት አቋቁሟል፤ ይህ መንግሥት በሰማይ የሚገኝ መስተዳድር ነው። ኢየሱስ ክርስቶስን የዚህ መንግሥት ገዢ አድርጎ ሾሞታል፤ ምድርንና በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችን የማስተዳደር ሥልጣንም ሰጥቶታል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የታመሙትን ፈውሷል፤ የተራቡትን መግቧል፤ የተፈጥሮ ኃይሎችን መቆጣጠር ችሏል፤ ሌላው ቀርቶ የሞቱትን አስነስቷል። (ማርቆስ 4:39፤ 6:41-44፤ ሉቃስ 4:40፤ ዮሐንስ 11:43, 44) በዚህ መንገድ፣ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ሲያስተዳድር ምን እንደሚያደርግ አሳይቷል።

 የአምላክ መንግሥት አንተን የሚጠቅሙ ምን ነገሮች እንደሚያደርግ ለማወቅ የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።

 ይህ ተስፋ የሚፈጸመው መቼ ነው?

 በቅርቡ ፍጻሜውን ያገኛል! ይህን በምን እናውቃለን? መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ መንግሥት ምድርን የሚያስተዳድርበት ጊዜ ሲቃረብ በዓለም ላይ የሚከሰቱ ነገሮችን አስቀድሞ ተናግሯል። (ሉቃስ 21:10, 11) አሁን በዓለም ላይ የሚታየው ሁኔታ፣ እነዚህ ነገሮች እየተፈጸሙ እንዳሉ የሚያሳይ ነው።

 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “የአምላክ መንግሥት ምድርን የሚገዛው መቼ ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

 መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ ዛሬ አንተን የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ተስፋ ሲገልጸው “ለነፍሳችን እንደ መልሕቅ” ነው ብሏል። (ዕብራውያን 6:19) በማዕበል በሚናወጥ ባሕር ላይ አንድን መርከብ አጽንቶ የሚያቆመው መልሕቅ ነው፤ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ ተስፋም ዛሬ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በጽናት እንድንቋቋም ይረዳናል። ተስፋችን እንድንረጋጋና ደስተኛ እንድንሆን እንዲሁም አጥርተን እንድናስብ ይረዳናል፤ ሌላው ቀርቶ ለጤንነታችን እንኳ ይጠቅመናል።—1 ተሰሎንቄ 5:8