ነቅታችሁ ጠብቁ!
ሳይንቲስቶች የመዓት ቀን ሰዓት እንዲጠጋ ወሰኑ—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ጥር 24, 2023 ሳይንቲስቶች፣ የመዓት ቀን ሰዓት a ለእኩለ ሌሊት ቀረብ እንዲል ወስነዋል፤ በዚህ ሰዓት ላይ እኩለ ሌሊት የሚያመለክተው የዓለም ፍጻሜን ነው።
“በሰው ዘር ላይ ለሚመጣው የጥፋት ስጋት ተምሳሌት የሆነው ‘የመዓት ቀን ሰዓት’ እስከ ዛሬ ሆኖ በማያውቅ መጠን ወደ እኩለ ሌሊት እንዲጠጋ ተደርጓል፤ ማክሰኞ ዕለት የተላለፈው ይህ ውሳኔ በዩክሬን ጦርነት፣ በኑክሌር ስጋቶችና በአየር ንብረት ቀውስ ምክንያት የተደረገ ነው።”—AFP የዜና ምንጭ
“ሳይንቲስቶች ማክሰኞ ዕለት እንዳስታወቁት ‘የመዓት ቀን ሰዓት’ ለእኩለ ሌሊት 90 ሴኮንዶች ብቻ እንዲቀረው ወስነዋል፤ የሰው ዘር ለአርማጌዶን የዚህን ያህል ቀርቦ አያውቅም።”—ABC ዜና
“ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ ሳይንቲስቶች ቡድን እንዳስጠነቀቀው የሰው ልጅ ሕልውና የአሁኑን ያህል ስጋት ላይ ወድቆ አያውቅም።”—ዘ ጋርዲያን
እውነት፣ የሰው ልጅም ሆነ ምድራችን ወደ ፍጻሜያቸው እየገሰገሱ ይሆን? የነገውን ጊዜ የምንፈራበት ምክንያት አለ? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ወደፊት ምን ይመጣ ይሆን?
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ምድር . . . ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች”፤ “በእሷም ላይ” ሰዎች “ለዘላለም ይኖራሉ።” (መክብብ 1:4፤ መዝሙር 37:29) በመሆኑም ምድር በሰው ልጆች ምክንያት አትጠፋም፤ ሰው የማይኖርባት ባድማ ስፍራም አትሆንም።
ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ላይም ስለ ፍጻሜ ተጠቅሷል። ለአብነት ያህል፣ ‘ዓለም እንደሚያልፍ’ ይናገራል።—1 ዮሐንስ 2:17
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዓለም ፍጻሜ የሚናገረውን ሐሳብ ትርጉም መረዳት ትፈልጋለህ? “በዓለም ላይ ጥፋት እየመጣ ነው? አፖካሊፕስ ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።
ከፊታችን የሚጠብቁን የዓለም ክስተቶች የሚፈጸሙበትን ጊዜ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ለማወቅ “የዓለም መጨረሻ የሚመጣው መቼ ነው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።
በተስፋ መኖር
ዓለማችን በብዙ ችግሮች እየታመሰች ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ በተስፋ እንድንኖር ይረዳናል። እንዴት?
መጽሐፍ ቅዱስ ለዕለታዊ ሕይወታችን የሚጠቅም ምክር ይዟል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) የኑሮ ውጣ ውረዶች እያሉም አዎንታዊ ለመሆን የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮችን ለማግኘት “የሚያስጨንቁ ነገሮችን መቆጣጠር የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ ተስፋ ይሰጣል። (ሮም 15:4) ዛሬም ሆነ ወደፊት የምንጠብቃቸውን የዓለም ክስተቶች በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ ይዟል፤ ይህም ዛሬ ባለው የነውጥ ጊዜ ተረጋግተን እንድንኖር ይረዳናል።
መጽሐፍ ቅዱስን አውቀህ መጠቀም ትፈልጋለህ? በአስተማሪ እገዛ የምንሰጠውን ነፃ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለምን አትሞክረውም?
a “የመዓት ቀን ሰዓት፣ በገዛ እጃችን በሠራናቸው አደገኛ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ዓለማችንን ለማጥፋት ምን ያህል እንደተቃረብን የሚያሳይ ንድፍ ነው። ተምሳሌታዊ ትርጉም ያለው ነው፤ በፕላኔቷ ላይ ሕልውናችን እንዲቀጥል ከተፈለገ ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ አደጋዎችን የሚያስታውሰን ማንቂያ ነው።”—ቡለቲን ኦቭ ዚ አቶሚክ ሳይንቲስትስ