ነቅታችሁ ጠብቁ!
ምድራችንን ማስተዳደር የሚችል የተረጋጋ መንግሥት አለ?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግሥታት ቀውስ ውስጥ ገብተዋል። የተረጋጉ በሚመስሉ አገሮችም እንኳ መንግሥታት በተለያዩ ምክንያቶች እየተናጡ ነው፤ የባለሥልጣናት ቅሌት፣ ተቀራራቢ የምርጫ ውጤቶች፣ የፖለቲካ ክፍፍልና የሕዝብ ዓመፅ ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው አንድ የተረጋጋ መንግሥት አለ። አንተም ስለዚህ መንግሥት ሰምተህ ታውቅ ይሆናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ ባስተማረው ጸሎት ላይ የተጠቀሰ መንግሥት ነው።
“እንግዲያው እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ። መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም።’”—ማቴዎስ 6:9, 10
መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ መንግሥት ምን ይላል?
የአምላክ መንግሥት—የተረጋጋ መንግሥት
ይህ መንግሥት የሚያስተዳድረው ከሰማይ ሆኖ ነው።
ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት” በማለት የጠራው ይህን መንግሥት ነው። (ማቴዎስ 4:17፤ 5:3, 10, 19, 20) “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም” ያለው ለዚህ ነው።—ዮሐንስ 18:36
ይህ መንግሥት የሰው ልጆች ያዋቀሯቸውን መንግሥታት አጥፍቶ በምትካቸው ይገዛል።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “[ይህ] መንግሥት . . . እነዚህን [የሰዎች] መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ ፈጽሞም ያጠፋቸዋል፤ እሱም ብቻውን ለዘላለም ይቆማል።”—ዳንኤል 2:44
ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ የሚያስተዳድረው ይህ መንግሥት ፈጽሞ አይጠፋም።
መጽሐፍ ቅዱስ “የገዢነት ሥልጣኑ የማያልፍና ዘላለማዊ፣ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው” ይላል።—ዳንኤል 7:13, 14
ይህ መንግሥት በምድር ላይ ሰላምና ደህንነት ያሰፍናል።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እያንዳንዱ ሰው በተከለው ወይንና በለስ ጥላ ሥር በሰላም ያርፋል። የሚያስፈራውም ነገር አይኖርም።”—ሚክያስ 4:4 የ1980 ትርጉም
ስለ አምላክ መንግሥት ተማር
ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ጊዜውን ያዋለው ‘የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ’ ነው። (ማቴዎስ 9:35) እንዲህ ሲልም ትንቢት ተናግሯል፦
“ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴዎስ 24:14
ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው ምሥራች በአሁኑ ወቅት ከ240 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ እየታወጀ ነው። አንተስ ስለዚህ መንግሥት እንዲሁም ከአገዛዙ ተጠቃሚ ለመሆን ማድረግ ስለሚጠበቅብህ ነገር ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ?
የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? የሚለውን ቪዲዮ እንድትመለከት እንጋብዝሃለን።