ነቅታችሁ ጠብቁ!
አንድ ከፍተኛ የጤና ባለሥልጣን፣ ማኅበራዊ ሚዲያ በወጣቶች ላይ ስለደቀነው ስጋት አስጠነቀቁ—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ግንቦት 23, 2023 አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ የጤና ባለሥልጣን፣ ማኅበራዊ ሚዲያ በወጣቶች ላይ እያደረሰ ስላለው ጉዳት ማኅበረሰቡን አስጠነቀቁ።
“ማኅበራዊ ሚዲያ ለልጆችና ለታዳጊዎች አንዳንድ ጥቅሞች ይኖሩት ይሆናል፤ ያም ሆኖ በአእምሮ ጤንነታቸውና በደህንነታቸው ላይ ከባድ ስጋት እንደደቀነ የሚጠቁሙ ነገሮችን እየተመለከትን ነው።”—ማኅበራዊ ሚዲያ እና የወጣቶች የአእምሮ ጤና፦ የአሜሪካ የማኅበረሰብ ጤና ባለሥልጣን ምክረ ሐሳብ 2023
ምክረ ሐሳቡ ለስጋት ምክንያት የሚሆኑ ነገሮችን በምርምር ውጤቶች አስደግፎ አቅርቧል።
ከ12 እስከ 15 ዓመት ባሉ ታዳጊዎች ላይ የተደረገ ጥናት እንዳሳየው “ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በቀን ከ3 ሰዓት በላይ የሚያሳልፉ [ወጣቶች] የድባቴና የጭንቀት ምልክቶችን ጨምሮ በአእምሮ ሕመም የመጠቃት አጋጣሚያቸው በእጥፍ ይጨምራል።”
በ14 ዓመት ታዳጊዎች ላይ የተደረገው ጥናት እንዳሳየው ደግሞ “ማኅበራዊ ሚዲያ በብዛት የሚጠቀሙ [ወጣቶች] ለአንዳንድ ችግሮች የመጋለጣቸው አጋጣሚ ሰፊ ነው፤ እነሱም የእንቅልፍ ችግር፣ የኢንተርኔት ጉልበተኞች ጥቃት፣ የራስን መልክ መጥላት፣ ለራስ ዝቅ ያለ አመለካከትና የድባቴ ምልክቶች ናቸው። እነዚህ ችግሮች ከወንዶች ልጆች ይልቅ በአመዛኙ በሴቶች ላይ እንደሚታዩ ተስተውሏል።”
ወላጆች ልጆቻቸውን ከእነዚህ አደጋዎች መጠበቅ የሚችሉት እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ ምክር ይሰጣል።
ወላጆች ማድረግ የሚችሉት ነገር
ትኩረት ስጡ። እንደ ወላጅ መጠን ማኅበራዊ ሚዲያ በልጃችሁ ላይ ሊያደርስ የሚችላቸውን ጉዳቶች አስቡባቸው፤ ይህን ግምት ውስጥ አስገብታችሁ ‘ይጠቀም ወይስ አይጠቀም?’ የሚለውን ወስኑ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ልጅን ሊሄድበት በሚገባው መንገድ አሠልጥነው።”—ምሳሌ 22:6
ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ለማወቅ “ልጄ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲጠቀም ልፍቀድለት?” የሚለውን ርዕስ አንብቡ።
ልጃችሁ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲጠቀም ከፈቀዳችሁለት፣ ሊያጋጥሙት ለሚችሉት አደጋዎች ንቁ ሁኑ፤ ኢንተርኔት ላይ ለሚያደርገው ነገር ትኩረት ስጡ። ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?
ልጃችሁ ኢንተርኔት ላይ ለመጥፎ ነገር እንዳይጋለጥ አድርጉ። ልጃችሁ ኢንተርኔት ላይ ሊያጋጥሙት የሚችሉ መጥፎ ነገሮችን እንዲለይና አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሠልጥኑት።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የፆታ ብልግናና ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት ወይም ስግብግብነት በመካከላችሁ ከቶ አይነሳ፤ አሳፋሪ ምግባር፣ የማይረባ ንግግርም ሆነ ጸያፍ ቀልድ የማይገቡ ነገሮች ናቸው።”—ኤፌሶን 5:3, 4
ምን ማድረግ እንደምትችሉ ጠቃሚ ምክሮች ለማግኘት “በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ ልጃችሁ ማኅበራዊ ሚዲያን በማይጎዳ መንገድ እንዲጠቀም ማሠልጠን” የሚለውን ርዕስ አንብቡ።
ገደብ አውጡ። ለምሳሌ ልጃችሁ መቼና ለምን ያህል ጊዜ ማኅበራዊ ሚዲያ እንደሚጠቀም መመሪያ አውጡ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የምትመላለሱት . . . እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ፤ . . . ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት።”—ኤፌሶን 5:15, 16
ያወጣችሁት ገደብ እንደሚጠቅመው ልጃችሁን ለማስረዳት ማኅበራዊ ድረ ገጾችን ስትጠቀም አስተዋይ ሁን የሚለውን የነጭ ሰሌዳ አኒሜሽን ተጠቀሙ።