መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኑክሌር ጦርነት ምን ይላል?
የዓለም ኃያላን መንግሥታት የኑክሌር መሣሪያ ክምችታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸው ዓለማችንን የኑክሌር ጦርነት ስጋት ላይ ጥሏታል። ይህ ሁኔታ በሰዎች ላይ ስጋት መፍጠሩ የሚጠበቅ ነው፤ ምክንያቱም የኑክሌር መሣሪያዎች ቁጥር በጨመረ መጠን የኑክሌር ጦርነት የሚነሳበት አጋጣሚም የዚያኑ ያህል ይጨምራል። አነስተኛ መጠን ያለው አንድ የኑክሌር መሣሪያ እንኳ ጥቅም ላይ ከዋለ፣ መላውን ዓለም የሚያወድም መጠነ ሰፊ የኑክሌር ጦርነት ይቀሰቀሳል ተብሎ ይፈራል። ቡሌቲን ኦቭ ዚ አቶሚክ ሳይንቲስትስ የተባለው ጽሑፍ እንደገለጸው የምንኖረው “የኑክሌር ጦርነት ከዛሬ ነገ ሊቀሰቀስ በሚችልበት” ጊዜ ላይ ነው።
በእርግጥ የኑክሌር ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል? ከሆነስ ፕላኔታችን ከዚህ ጦርነት ትተርፍ ይሆን? የኑክሌር ጦርነት ሊነሳ ይችላል ከሚለው ስጋት ነፃ መሆን የምንችለውስ እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
በዚህ ርዕስ ውስጥ
መጽሐፍ ቅዱስ የኑክሌር ጦርነት እንደሚነሳ ተንብዮአል?
መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ስለ ኑክሌር ጦርነት አይናገርም። ሆኖም ዓለማችንን የኑክሌር ጦርነት ስጋት ላይ ስለጣሏት ክስተቶችና የሰዎች ባሕርይ አስቀድሞ ተናግሯል።
እስቲ የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ላይ ከሚታየው ሁኔታ ጋር ለማወዳደር ሞክር፦
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች፦ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲህ በማለት ጠየቁ፦ “የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ [ምልክት] ምንድን ነው?” ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል።”—ማቴዎስ 24:3, 7
የዓለም ክስተቶች፦ የኑክሌር መሣሪያ ያላቸውን ጨምሮ በርካታ አገሮች ወደ ትጥቅ ውጊያ የሚገቡበት አጋጣሚ ጨምሯል።
“ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዓለም ወደ ግጭት የሚገባበት አጋጣሚ በጣም እየጨመረ ነው፤ ጦርነቶች እየበዙ ነው።”—ዚ አርምድ ኮንፍሊክት ሎኬሽን ኤንድ ኢቨንት ዳታ ፕሮጀክት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ፦ “በፍጻሜው ዘመን የደቡቡ ንጉሥ [ከሰሜኑ ንጉሥ] ጋር ይጋፋል።”—ዳንኤል 11:40
የዓለም ክስተቶች፦ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ተቀናቃኝ አገሮችና አጋሮቻቸው የላቀውን ቦታ ለመያዝ ሲሉ እርስ በርስ እየተጋፉ ወይም እየተፎካከሩ ነው። በዘመናችን ያሉት ታላላቅ የኑክሌር ኃይሎች ፊት ለፊት ጦርነት ባይገጥሙም የኑክሌር አቅማቸውን በማስፋፋትና በማጠናከር ላይ ይገኛሉ።
“ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በአገሮች መካከል ያለው ግጭት እየጨመረ መሄዱን አስተውለናል፤ በአንዳንዶቹ ግጭቶች ላይ ኃያላን መንግሥታት ከተቃራኒ ጎራዎች ጎን ተሰልፈው ድጋፍ ያደርጋሉ።”—ዚ ኡፕሳላ ኮንፍሊክት ዳታ ፕሮግራም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች፦ “በመጨረሻዎቹ ቀናት ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን [ይመጣል]። ምክንያቱም ሰዎች . . . ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች [ይሆናሉ]።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-3
የዓለም ክስተቶች፦ በዛሬው ጊዜ እንዳሉ ብዙ ሰዎች ሁሉ የዓለም መሪዎችም አለመግባባት ያጋጥማቸዋል። ሰላማዊ በሆነ መንገድ ልዩነታቸውን ከመፍታት ይልቅ ማስፈራሪያ ወይም ኃይል ሊጠቀሙ ይችላሉ። እንዲህ ያለው አካሄድ የኑክሌር ጦርነት ስጋት ይፈጥራል።
“ተባብሮ የመሥራትን መንፈስ የሚያጠናክር ተግባራዊ እርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ ግጭቶች ይበልጥ አውዳሚ እየሆኑ መሄዳቸው የማይቀር ነው።”—ሰሚር ሳራን እና ጄን ኸርማን፣ ወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም።
አምላክ የኑክሌር ጦርነት እንዲነሳ ይፈቅዳል?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረው ነገር የለም። ሆኖም በዘመናችን “የሚያስፈሩ ነገሮች” እንደሚከሰቱ ይናገራል። (ሉቃስ 21:11) ከእነዚህ መካከል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተጣሉት አቶሚክ ቦምቦች ይገኙበታል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ጦርነት እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ይናገራል። ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።
ፕላኔታችን ትተርፍ ይሆን?
አዎ። ሰዎች የኑክሌር መሣሪያዎችን ዳግመኛ ቢጠቀሙ እንኳ አምላክ መላዋን ምድር የሚያወድም ጥፋት እንዲከሰት አይፈቅድም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፕላኔታችን በሕልውናዋ ላይ የተቃጡ አደጋዎችን ማለፍ ብቻ ሳይሆን ለዘላለም የሰው ልጆች መኖሪያ እንደምትሆን ይናገራል።
አንዳንድ ሰዎች፣ ወደፊት በምድር ላይ የሚኖረውን ሁኔታ ሲያስቡ ምድር በኑክሌር ጦርነት ምክንያት ተበክላና ባድማ ሆና ይታያቸዋል፤ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በሕይወት ለመቀጠል ሲታገሉ በዓይነ ሕሊናቸው ይሥላሉ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ጦርነት በምድር ላይ ያስከተለው ማንኛውም ዓይነት ጉዳት ሙሉ በሙሉ እንደሚቀለበስ ይጠቁማል።
አምላክ ውብ በሆነች ምድር ላይ ተደስተን እንድንኖር ይፈልጋል
ፈጣሪያችን ምድርን የፈጠራት ራሷን በራሷ የማደስ አስደናቂ ችሎታ እንዲኖራት አድርጎ ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ወደፊት ደግሞ አምላክ ኃይሉን በመጠቀም ምድርን ቀድሞ ወደነበረችበት ይዞታ ይመልሳታል፤ ምድር ለዘላለም ለሰው ልጆች ተስማሚ የሆነች ውብ መኖሪያ ትሆናለች።—መዝሙር 37:11, 29፤ ራእይ 21:5
“ከኑክሌር ስጋት” ነፃ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
አንዳንዶች “የኑክሌር ስጋት” ማለትም “የኑክሌር ጦርነትና ይህ ጦርነት የሚያስከትለው መዘዝ ፍርሃት” ሕይወታቸውን ተቆጣጥሮታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ተስፋዎች እንዲሁም ጠቃሚ ምክሮች እንዲህ ያሉ ሰዎች ፍርሃታቸው ቀለል እንዲልላቸው ረድተዋል። እንዴት?
መጽሐፍ ቅዱስ ምድርም ሆነ በላይዋ ላይ የሚኖሩት ፍጥረታት ብሩህ ተስፋ እንደሚጠብቃቸው ይናገራል። ይህ ተስፋ “ለሕይወታችን እንደ መልሕቅ” ስለሚሆንልን ጭንቀትን ለመቀነስ ይረዳናል። (ዕብራውያን 6:19 የግርጌ ማስታወሻ) በተጨማሪም ‘ወደፊት ምን ይፈጠር ይሆን?’ በሚል ጭንቀት ከመዋጥ ይልቅ በዛሬዋ ቀን ላይ ማተኮር ጭንቀትን ለመቀነስ ይረዳል። ኢየሱስ እንዳለው “እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው።”—ማቴዎስ 6:34
እንደ እውነቱ ከሆነ ሁላችንም አእምሯዊና ስሜታዊ ጤንነታችንን መንከባከባችን አስፈላጊ ነው። ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ የኑክሌር መሣሪያዎች በተመለከተ ለሚቀርቡ ትንተናዎች፣ ውይይቶችና ትንበያዎች ሳያስፈልግ ራሳችንን አለማጋለጥ ነው። ይህ እውነታውን ላለማየት ዓይንን እንደ መጨፈን ተደርጎ አይቆጠርም። ከዚህ ይልቅ በእኛ ቁጥጥር ሥር ያልሆኑና ምናልባትም ፈጽሞ ሊፈጠሩ የማይችሉ ነገሮችን ማሰብ ከሚያስከትለው ጭንቀት አእምሯችንን ነፃ ለማድረግ እንደሚወሰድ እርምጃ ተደርጎ ሊታይ ይገባል።
ከመጥፎ ዜናዎች ርቀህ በሕይወትህ ውስጥ ባሉት አዎንታዊ ነገሮች ላይ ትኩረት በማድረግ ለአእምሮህ እረፍት ስጠው።
መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ አስተማማኝ ተስፋ ይሰጣል
አምላክ ስለሰጣቸው ተስፋዎች ይበልጥ እየተማርክ ስትሄድ ተስፋ፣ ደስታና ውስጣዊ ሰላም ታገኛለህ።
መጽሐፍ ቅዱስ የኑክሌር አርማጌዶን እንደሚነሳ ተንብዮአል?
አንዳንዶች አርማጌዶን፣ ዓለም አቀፋዊ የኑክሌር ጦርነትን የሚያመለክት ይመስላቸዋል። እንዲህ ያለው ክስተት አውዳሚ እንደሚሆን ማሰባቸው የሚያስገርም አይደለም።
ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “አርማጌዶን” የሚለውን ቃል የሚጠቀምበት ‘በዓለም ነገሥታት ሁሉ’ ማለትም በሰብዓዊ መንግሥታት እና በአምላክ መካከል የሚደረገውን ውጊያ ለማመልከት ነው። a (ራእይ 16:14, 16) አርማጌዶን እንደ ኑክሌር ጦርነት መላዋን ምድር የሚያወድም ጅምላ ጨራሽ ጦርነት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በአርማጌዶን ጦርነት ላይ አምላክ የሚያጠፋው ክፉዎችን ብቻ ነው፤ ይህም እውነተኛ ሰላምና ደህንነት እንዲሰፍን ያደርጋል።—መዝሙር 37:9, 10፤ ኢሳይያስ 32:17, 18፤ ማቴዎስ 6:10
መጽሐፍ ቅዱስ ለጦርነት ምን መፍትሔ ይሰጣል?
ይሖዋ b አምላክ ኃይሉን በመጠቀም በብሔራት መካከል ያለውን ግጭት ያስቆማል እንዲሁም የጦር መሣሪያዎቻቸውን ያወድማል። ይህን የሚያደርገው ወደፊት ሰብዓዊ መንግሥታትን አስወግዶ ምድርን በሚያስተዳድረው ሰማያዊ መንግሥቱ ወይም አገዛዙ አማካኝነት ነው።—ዳንኤል 2:44
የአምላክ መንግሥት፣ በሰላምና በአንድነት መኖር የሚቻልበትን መንገድ ለሰዎች ያስተምራል። መላዋን ምድር የሚገዛው አንድ መንግሥት ብቻ ስለሚሆን ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው ግጭቶች አይኖሩም፤ ሰዎች ስለ ጦርነት እንኳ ጨርሶ የማይማሩበት ጊዜ ይመጣል! (ዳንኤል 2:44) ይህ ምን ውጤት ያስገኛል? “እያንዳንዱም ከወይኑና ከበለስ ዛፉ ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም።”—ሚክያስ 4:4
a “የአርማጌዶን ጦርነት ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።