በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን አስደሳች ማድረግ

የመጽሐፍ ቅዱስን ንባቤን አስደሳች ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስን ንባቤን አስደሳች ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን ስለ ማንበብ ስታስብ ምን ይሰማሃል? አሰልቺ እንደሆነ ይሰማሃል? ወይስ አስደሳች? በአብዛኛው ይህን የሚወስነው የምታነብበት መንገድ ነው። የማንበብ ጉጉት እንዲያድርብህና ንባብህ ይበልጥ አስደሳች እንዲሆንልህ ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

እምነት የሚጣልበትና ቀለል ባለ ቋንቋ የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ምረጥ። የምታነበው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ከባድ ወይም በአሁኑ ጊዜ የማይሠራባቸው ቃላት የበዙበት ከሆነ ንባብህ አስደሳች እንደማይሆንልህ የታወቀ ነው። ስለዚህ ልብህን የሚነካና ለመረዳት ቀላል የሆነ ቋንቋ የሚጠቀም ትርጉም ፈልግ። ሆኖም ትርጉሙ በጥንቃቄና በትክክለኛው መንገድ የተተረጎመ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብሃል። *

የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተጠቀም። በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን በመጽሐፍ መልክ ታትሞ ብቻ ሳይሆን በኤሌክትሮኒክ ቅጂም ማግኘት ይቻላል። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ኢንተርኔት ላይ እንዳለህ አሊያም በኮምፒውተር፣ በታብሌት ወይም በሞባይል ስልክ ላይ አውርደህ ማንበብ ትችላለህ። አንዳንድ አፕሊኬሽኖች፣ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ስታነብ ከጥቅሱ ጋር ተዛማጅ የሆኑ ሌሎች ጥቅሶችን በቀላሉ ለማውጣት ወይም ከተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ጋር ለማመሳከር የሚያስችል ገጽታ አላቸው። ከማንበብ ይልቅ መስማት የምትመርጥ ከሆነ ደግሞ በድምፅ የተቀዳ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገኝባቸው ቋንቋዎችም አሉ። ብዙ ሰዎች በትራንስፖርት ሲጓዙ፣ ልብስ ሲያጥቡ ወይም አመቺ በሆኑ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ሲካፈሉ የተቀዳ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ማዳመጥ ያስደስታቸዋል። ታዲያ አንተስ የሚቀልህን ዘዴ መርጠህ ለምን አትሞክረውም?

መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የተዘጋጁ መሣሪያዎችን ተጠቀም። እነዚህ መሣሪያዎች ከንባብህ ይበልጥ ጥቅም እንድታገኝ ይረዱሃል። ለምሳሌ ያህል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ  የተጠቀሱ ቦታዎችን የሚያሳዩ ካርታዎች አሉ፤ እነዚህ ካርታዎች በምታነበው ክፍል ውስጥ የተጠቀሱት ቦታዎች የት እንደሚገኙ ለማወቅና ዘገባውን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ያግዙሃል። በዚህ መጽሔት ላይ እንዲሁም በjw.org/am ላይ “የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች” በሚለው ዓምድ ሥር የሚወጡት ርዕሶች የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ምን መልእክት እንደሚያስተላልፉ እንድትገነዘብ ይረዱሃል።

የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቀም። መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ማንበብ ከባድ እንደሆነ ከተሰማህ ይበልጥ ትኩረትህን ከሚስበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለምን አትጀምርም? እንዲህ ማድረግህ የማንበብ ጉጉትህ እንዲቀሰቀስ ይረዳሃል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተደጋጋሚ ስለሚጠቀሱ ሰዎች ማወቅ ከፈለግክ ስለ እነዚህ ሰዎች የሚገልጸው ዘገባ የሚገኝበትን ክፍል መርጠህ ማንበብ ትችላለህ። “ በውስጡ ስለተጠቀሱት ሰዎች በማንበብ መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር” በሚለው ሣጥን ውስጥ የተጠቀሰውን ሐሳብ እንደ ናሙና መጠቀም ትችላለህ። አሊያም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በርዕሰ ጉዳይ ወይም ነገሮች በተከናወኑበት ቅደም ተከተል መሠረት ማንበብ ትፈልግ ይሆናል። ከእነዚህ ዘዴዎች መካከል አንዱን ለምን አትሞክርም?

^ አን.4 ብዙዎች አዲስ ዓለም ትርጉምን ትክክለኛ፣ እምነት የሚጣልበትና ለማንበብ ቀላል ሆኖ አግኝተውታል። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ከ130 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች ይገኛል። ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማግኘት ከፈለግክ ከjw.org/am ላይ ማውረድ ወይም JW Library የተባለውን አፕሊኬሽን መጫን ትችላለህ። አሊያም ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ቤትህ ድረስ እንዲያመጡልህ መጠየቅ ትችላለህ።