በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ሞትን እፈራ ነበር!

ሞትን እፈራ ነበር!
  • የትውልድ ዘመን፦ 1964

  • የትውልድ አገር፦ እንግሊዝ

  • የኋላ ታሪክ፦ በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለች ልጅ የወለደችና ብልሹ ሕይወት ትመራ የነበረች ሴት

የቀድሞ ሕይወቴ

የተወለድኩት የእንግሊዝ ዋና ከተማ በሆነችው በለንደን ውስጥ በሚገኝ ፓዲንግተን የተባለ ሕዝብ የሚበዛበት አካባቢ ነው። የምኖረው ከእናቴና ከሦስት ታላላቅ እህቶቼ ጋር ነበር። አባቴ የአልኮል መጠጥ ሱስ ስለነበረበት ከቤተሰቡ ጋር አብሮ የማይሆንባቸው ብዙ ጊዜያት ነበሩ።

ልጅ ሳለሁ እናቴ ሁሌ ማታ ማታ እንድጸልይ አስተምራኝ ነበር። የመዝሙር መጽሐፍን ብቻ የያዘች ትንሽ መጽሐፍ ቅዱስ ነበረችኝ፤ መዝሙሮቹን የራሴ ዜማ አውጥቼ እዘምራቸው ነበር። በአንድ ወቅት አንድ መጽሐፍ ሳነብ “ነገ የሚባል ቀን የማይኖርበት ጊዜ ይመጣል” የሚል ሐሳብ አነበብኩ፤ ይህ አባባል ከአእምሮዬ ሊወጣ አልቻለም። እነዚህ ቃላት ስለ ወደፊቱ ጊዜ እያሰብኩ እንቅልፍ አጥቼ እንዳድር አደረጉኝ። ‘ሕይወት ይህ ብቻ ሊሆን አይችልም’ እንዲሁም ‘የተፈጠርኩት ለምንድን ነው?’ እያልኩ አስብ ነበር። መሞት አልፈልግም ነበር!

በኋላም ስለ መናፍስታዊ ድርጊቶች የማወቅ ጉጉት አደረብኝ። የሞቱ ሰዎችን ለማነጋገር እሞክር ነበር፤ በተጨማሪም ከትምህርት ቤት ጓደኞቼ ጋር ወደ መቃብር ቦታዎች እንሄድ እንዲሁም አስፈሪ ፊልሞችን እናይ ነበር። ይህን ማድረግ አስፈሪ ቢሆንም ያስደስተን ነበር።

ገና የአሥር ዓመት ልጅ ሳለሁ መጥፎ ሕይወት ውስጥ ገባሁ። ትምባሆ ማጨስ የጀመርኩ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሱሰኛ ሆንኩ። ከጊዜ በኋላም ማሪዋና ማጨስ ጀመርኩ። የአልኮል መጠጥ መጠጣት የጀመርኩት ገና በ11 ዓመቴ ነበር። ጣዕሙን ባልወደውም የስካር ስሜቱ ደስ ይለኝ ነበር። ሙዚቃና ጭፈራም እወድ ነበር። ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ወደ ጭፈራ ቤቶችና የምሽት ክበቦች እሄድ ነበር። ሌሊት ላይ ከቤት ተደብቄ እወጣና ልክ ከመንጋቱ በፊት ማንም ሳያየኝ ተመልሼ እገባለሁ። በቀጣዩ ቀን ስለሚደክመኝ ከትምህርት ቤት እቀር ነበር። ትምህርት ቤት በምሆንበት ጊዜም እንኳ መጠጥ እጠጣ ነበር።

ትምህርቴን በማጠናቅቅበት የመጨረሻ ዓመት ላይ በጣም መጥፎ ውጤት አመጣሁ። ከዚያ በፊት እናቴ ምን ያህል መጥፎ ሕይወት እንደምመራ አታውቅም ነበር፤ በመሆኑም ውጤቴን ስታይ በጣም አዘነች፤ እንዲሁም ተበሳጨች። በዚህም የተነሳ ከእናቴ ጋር ተጣላን፤ ከዚያም ቤቱን ጥዬ ወጣሁ። ለተወሰነ ጊዜ ያህል፣ ከወንድ ጓደኛዬ ከቶኒ ጋር አብሬ ኖርኩ፤ ቶኒ ራስተፈሪያን ነበር። ቶኒ በወንጀል ድርጊቶች ይካፈል እንዲሁም ዕፅ ያዘዋውር ነበር፤ በዚያ ላይ ደግሞ በጣም ዓመፀኛ ነበር። ብዙም ሳይቆይ አረገዝኩ፤ ከዚያም ገና በ16 ዓመቴ ወንድ ልጃችንን ወለድኩ።

 መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

ለመጀመሪያ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘሁት ላላገቡ እናቶችና ልጆቻቸው በተዘጋጀ ሆስቴል ውስጥ እኖር በነበረበት ወቅት ነው። ይህን መኖሪያ የሰጠን የአካባቢው መስተዳድር ነው። የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሁለት ሴቶች፣ በዚያ ይኖሩ ከነበሩ ወጣት እናቶች መካከል አንዳንዶቹን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ይመጡ ነበር። አንድ ቀን እኔም በሚያደርጉት ውይይት ላይ ተካፈልኩ። የይሖዋ ምሥክሮቹ እንደተሳሳቱ ላሳምናቸው ፈልጌ ነበር። ሆኖም ለነበሩኝ በርካታ ጥያቄዎች በሙሉ ረጋ ብለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ግልጽ የሆነ መልስ ሰጡኝ። ያሳዩኝ ደግነትና አሳቢነት በጣም ማረከኝ። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን እንድማር ያቀረቡልኝን ግብዣ ተቀበልኩ።

ብዙም ሳይቆይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማርኩት ነገር ሕይወቴን ለወጠው። ከልጅነቴ ጀምሮ ሞትን እፈራ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ስማር ግን ኢየሱስ የሞቱ ሰዎች እንደሚነሱ ያስተማረውን ትምህርት አወቅኩ! (ዮሐንስ 5:28, 29) በተጨማሪም አምላክ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልኝ ተማርኩ። (1 ጴጥሮስ 5:7) በተለይ በኤርምያስ 29:11 ላይ የሚገኘው ጥቅስ ልቤን ነካው፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “‘ለእናንተ የማስበውን ሐሳብ በሚገባ አውቀዋለሁና’ ይላል ይሖዋ፤ ‘ለእናንተ የማስበው ጥፋትን ሳይሆን ሰላምን እንዲሁም የተሻለ ሕይወትንና ተስፋን ነው።’” እኔም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ሊኖረኝ እንደሚችል አመንኩ።—መዝሙር 37:29

የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛ ፍቅር አሳይተውኛል። ለመጀመሪያ ጊዜ በስብሰባቸው ላይ ስገኝ በዚያ የነበረው መንፈስ በጣም ደስ የሚል ነበር፤ ሁሉም ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልኝ! (ዮሐንስ 13:34, 35) በዚያ የነበረው ሁኔታ በአካባቢዬ ባለ ቤተ ክርስቲያን ስገኝ ካየሁት በጣም የተለየ ነበር። የነበርኩበት ሁኔታ ጥሩ ባይሆንም የይሖዋ ምሥክሮች በደስታ ተቀብለውኛል። ጊዜ ሰጥተው ተንከባክበውኛል፤ እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ አድርገውልኛል። ከአንድ ትልቅና አፍቃሪ ቤተሰብ ጋር እንደተቀላቀልኩ ተሰማኝ።

የአምላክን የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ማሟላት ከፈለግኩ በሕይወቴ ውስጥ ለውጥ ማድረግ እንዳለብኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ተረዳሁ። ሲጋራ ማጨሴን ማቆም ቀላል አልነበረም። እንዲሁም የምሰማቸው አንዳንድ የሙዚቃ ዓይነቶች ማሪዋና የማጨስ ፍላጎቴን እንደሚቀሰቅሱት ተገነዘብኩ፤ ስለዚህ የማዳምጠውን የሙዚቃ ዓይነት ቀየርኩ። በተጨማሪም ከልክ በላይ እንድጠጣና እንድሰክር ስለሚገፋፉኝ ወደ ጭፈራ ቤቶችና የምሽት ክበቦች መሄድ አቆምኩ። እንዲሁም በጀመርኩት የሕይወት ጎዳና እንድቀጥል የሚረዱኝና ጥሩ ተጽዕኖ የሚያሳድሩብኝ ጓደኞች አፈራሁ።—ምሳሌ 13:20

በዚህ ጊዜ ቶኒም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምሮ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለጥያቄዎቹ መልስ ስለሰጡት የሚማረው ነገር እውነት እንደሆነ ተገነዘበ። በሕይወቱ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ አደረገ፤ ዓመፀኛ ከሆኑት ጓደኞቹ ጋር የነበረውን ግንኙነት አቆመ፤ በወንጀል ድርጊቶች መካፈል ተወ፤ እንዲሁም ማሪዋና ማጨሱን አቆመ። ሁለታችንም ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ማስደሰት ከፈለግን ሥነ ምግባር የጎደለውን አኗኗራችንን መተውና ልጃችንን በተገቢው መንገድ ማሳደግ እንዳለብን ተረዳን። በመሆኑም በ1982 ተጋባን።

“አሁን፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜም ሆነ ስለ ሞት በመጨነቅ እንቅልፍ አጥቼ አላድርም።”

እኔ ማድረግ የምፈልጋቸውን ለውጦች በማድረግ ረገድ የተሳካላቸውን ሰዎች የሕይወት ታሪክ የያዙ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! * መጽሔቶችን እየፈለግኩ አነብብ እንደነበር ትዝ ይለኛል። የእነዚህ ሰዎች ምሳሌ በጣም አበረታቶኛል! ጥረት ማድረጌን እንድቀጥልና ተስፋ እንዳልቆርጥ ብርታት ሰጥቶኛል። ይሖዋ ተስፋ እንዳይቆርጥብኝ በተደጋጋሚ እጸልይ ነበር። ከዚያም እኔና ቶኒ ሐምሌ 1982 ተጠምቀን የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን።

ያገኘሁት ጥቅም

ይሖዋ አምላክ ጋር ወዳጅነት መመሥረቴ ሕይወቴን ታድጎልኛል። እኔና ቶኒ ከባድ ችግር ባጋጠመን ወቅት ይሖዋ ደግፎናል። ችግሮች ሲያጋጥሙን በይሖዋ መታመን እንዳለብን ተምረናል፤ ደግሞም ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን እንደረዳንና የሚያስፈልገንን ሁሉ እንዳሟላልን ተመልክተናል።—መዝሙር 55:22

ወንድ ልጃችንና ሴት ልጃችን ይሖዋን እንዲያውቁ መርዳት በመቻላችን በጣም ደስተኛ ነኝ። አሁን ደግሞ የእነሱም ልጆች ስለ አምላክ እየተማሩ እንደሆነ ስመለከት ደስታ ይሰማኛል።

አሁን፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜም ሆነ ስለ ሞት በመጨነቅ እንቅልፍ አጥቼ አላድርም። እኔና ቶኒ ጊዜያችንን የምናሳልፈው በየሳምንቱ የይሖዋ ምሥክሮችን የተለያዩ ጉባኤዎች በመጎብኘትና በዚያ የሚሰበሰቡትን በማበረታታት ነው። ከጉባኤዎቹ ጋር አብረን በመሆን፣ ሰዎች በኢየሱስ ካመኑ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኙ እናስተምራለን።

^ አን.17 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።