በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ መረዳት ያለው አደጋ

መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ መረዳት ያለው አደጋ

አንዲት ትንሽ ልጅ፣ ከአንድ ፋብሪካ ጭስ ማውጫ እየተትጎለጎለ የሚወጣው ጭስ ደመና የሚመስል ነገር ሲሠራ አየች። ከዚያም ፋብሪካው ደመና የሚሠራ ፋብሪካ እንደሆነ አድርጋ አሰበች። ልጆች፣ ነገሮችን በተሳሳተ መንገድ በመረዳት የሚሠሩት እንዲህ ያለው ቀላል ስህተት ያስቀን ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ግን ነገሮችን በተሳሳተ መንገድ መረዳታችን ሕይወታችንን አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ የመድኃኒት ዕቃ ላይ የተጻፈውን መግለጫ በተሳሳተ መንገድ መረዳት አስከፊ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል።

ከመንፈሳዊ ነገሮች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተሳሳተ መንገድ መረዳት ደግሞ ከዚህም የከፋ ችግር ሊያመጣ ይችላል። ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች የኢየሱስን ትምህርቶች በተሳሳተ መንገድ ተረድተዋቸው ነበር። (ዮሐንስ 6:48-68) እነዚህ ሰዎች ያልገባቸውን ነገር ለመረዳት ከመሞከር ይልቅ ኢየሱስ የሚያስተምረውን ትምህርት ለመቀበል ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀሩ። ይህ እንዴት ያለ ከባድ ኪሳራ ነው!

መመሪያ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን ታነብባለህ? ይህን ማድረግህ የሚያስመሰግን ነው። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ በተሳሳተ መንገድ የተረዳኸው ሐሳብ ይኖር ይሆን? ብዙ ሰዎች እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ብዙዎች በተሳሳተ መንገድ ከሚረዷቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ሐሳቦች መካከል ሦስቱን እስቲ ተመልከት።

  • አንዳንድ ሰዎች “እውነተኛውን አምላክ ፍራ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ በተሳሳተ መንገድ ይረዱታል። ይህ ጥቅስ፣ አምላክ እንዳይቀጣቸው በመፍራት በፊቱ መንቀጥቀጥን የሚያመለክት እንደሆነ ይሰማቸዋል። (መክብብ 12:13) ሆኖም አምላክ፣ የሚያመልኩት ሰዎች ስለ እሱ እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዲያድርባቸው አይፈልግም። እንዲያውም አምላክ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ። እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ። አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ።” (ኢሳይያስ 41:10) አምላክን መፍራት ማለት ለእሱ ጥልቅ አክብሮት ማዳበር ማለት ነው።

  • ምድር በእሳት ተቃጥላ ትጠፋለች?

    አንዳንድ ሰዎች “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው . . . ለመወለድ ጊዜ አለው፤ ለመሞትም ጊዜ አለው” የሚለውን ጥቅስ በተሳሳተ መንገድ ይረዱታል። አምላክ እያንዳንዱ ሰው የሚሞትበትን ጊዜ ወስኗል ብለው ያስባሉ። (መክብብ 3:1, 2) ይሁንና ይህ ጥቅስ እየተናገረ ያለው ስለ ሕይወት ሂደት ማለትም ሞት ማንንም ሰው ሊያጋጥም የሚችል ነገር እንደሆነ ነው። ደግሞም የአምላክ ቃል፣ የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ዕድሜያችንን ሊያስረዝሙት ወይም ሊያሳጥሩት እንደሚችሉ ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋን መፍራት ዕድሜን ያስረዝማል” ይላል። (ምሳሌ 10:27፤ መዝሙር 90:10፤ ኢሳይያስ 55:3) እንዴት? ለምሳሌ ለአምላክ ቃል አክብሮት ካለን እንደ ስካርና የሥነ ምግባር ብልግና ያሉ መጥፎ ድርጊቶችን ከመፈጸም እንቆጠባለን።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

  • አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ ሰማያትና ምድር ‘ለእሳት ተጠብቀው እንደሚቆዩ’ የሚናገረው ሐሳብ ቃል በቃል የሚወሰድ እንደሆነ ይሰማቸዋል፤ ስለሆነም አምላክ ይህችን ምድር ያጠፋታል ብለው ያስባሉ። (2 ጴጥሮስ 3:7) ሆኖም አምላክ ፕላኔቷ ምድር እንድትጠፋ እንደማይፈቅድ ተናግሯል። አምላክ “ምድርን በመሠረቶቿ ላይ [መሥርቷታል]፤ እሷም ለዘላለም ከቦታዋ አትናወጥም።” (መዝሙር 104:5፤ ኢሳይያስ 45:18) በእሳት ተቃጥሎ እንደጠፋ ያህል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚደመሰሰው በምድር ላይ ያለው ብልሹ ሥርዓት እንጂ ግዑዟ ምድር አይደለችም። ሰማያት የሚለው አገላለጽ ደግሞ ቃል በቃል ሲወሰድ ግዑዙን ሰማይ፣ በከዋክብት የተሞላውን ጽንፈ ዓለም ወይም የአምላክን መኖሪያ ያመለክታል። እነዚህን ደግሞ አምላክ እንደማያጠፋቸው የታወቀ ነው።

አንዳንድ ጊዜ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ የሚረዱት ለምንድን ነው?

ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት፣ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያነቡትን ሐሳብ በተሳሳተ መንገድ ሊረዱት ይችላሉ። ሆኖም አምላክ ይህ እንዲሆን የሚፈቅደው ለምንድን ነው? አንዳንዶች እንዲህ ብለው ያስቡ ይሆናል፦ ‘አምላክ ጥበበኛና ሁሉን የሚያውቅ ከሆነ ሁሉም ሰው በቀላሉ ሊረዳው የሚችልና በጣም ግልጽ በሆነ መንገድ የተጻፈ መጽሐፍ ያልሰጠን ለምንድን ነው?’ ብዙ ጊዜ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ እንዲረዱ የሚያደርጓቸውን ሦስት ምክንያቶች እስቲ እንመልከት።

  1. መጽሐፍ ቅዱስ ትሑትና ለመማር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ብቻ ሊረዱት በሚችሉት መንገድ የተጻፈ ነው። ኢየሱስ ወደ አባቱ ሲጸልይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፣ እነዚህን ነገሮች ከጥበበኞችና ከአዋቂዎች ሰውረህ ለትናንሽ ልጆች ስለገለጥክላቸው በይፋ አወድስሃለሁ።” (ሉቃስ 10:21) መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ብቻ ሊረዱት በሚችሉት መንገድ ነው። ‘ጥበበኛና አዋቂ’ ናቸው የሚባሉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የትዕቢት ዝንባሌ ይታይባቸዋል፤ በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ ሊረዱት ይችላሉ። እንደ “ትናንሽ ልጆች” ትሑት የሆኑና የማወቅ ጉጉት ያላቸው ሰዎች ግን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በተሻለ መንገድ ይረዳሉ። በእርግጥም አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈበት መንገድ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ነው!

  2. መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት የሚችሉት በዚህ ረገድ የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ከልባቸው የሚያምኑ ሰዎች ናቸው። ኢየሱስ፣ ሰዎች የእሱን ትምህርት ሙሉ በሙሉ መረዳት እንዲችሉ እርዳታ ማግኘት እንደሚያስፈልጋቸው ተናግሯል። ታዲያ እርዳታ የሚያገኙት እንዴት ነው? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “አብ በስሜ የሚልከው ረዳት ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ሁሉንም ነገር ያስተምራችኋል።” (ዮሐንስ 14:26) ስለዚህ አምላክ ለሰዎች ቅዱስ መንፈሱን ማለትም ኃይሉን በመስጠት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያነቡት ነገር እንዲገባቸው ይረዳቸዋል። ሆኖም፣ አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የእሱን እርዳታ ለማይፈልጉ ሰዎች መንፈሱን አይሰጣቸውም፤ በመሆኑም አብዛኛውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት ይከብዳቸዋል። በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ፣ ጥሩ እውቀት ያላቸው ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት እገዛ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ለመርዳት እንዲነሳሱ ያደርጋቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 8:26-35

  3. ሰዎች አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን መረዳት የሚችሉት አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ብቻ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ ዳንኤል ወደፊት ሰዎች የሚመረምሩት መልእክት እንዲጽፍ ተነግሮት ነበር። አንድ መልአክ እንዲህ ብሎታል፦ “አንተም ዳንኤል ሆይ፣ እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ ቃሉን በሚስጥር ያዝ፤ መጽሐፉንም አትመው።” ለብዙ መቶ ዘመናት በርካታ ሰዎች የዳንኤልን መጽሐፍ ያነበቡት ቢሆንም ሊረዱት አልቻሉም። ሌላው ቀርቶ ዳንኤልም እንኳ ከጻፋቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን አልተረዳቸውም ነበር። “እኔም ሰማሁ፤ ሆኖም ሊገባኝ አልቻለም” በማለት በትሕትና ተናግሯል። ከጊዜ በኋላ ሰዎች ዳንኤል የጻፈውን ትንቢት በትክክል መረዳት የሚችሉበት ጊዜ እንደሚመጣ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ይህ የሚሆነው አምላክ የፈቀደው ጊዜ ሲደርስ ብቻ ነው። መልአኩ ዳንኤልን እንዲህ ብሎታል፦ “ዳንኤል ሆይ፣ ሂድ፤ ምክንያቱም የፍጻሜው ዘመን እስኪመጣ ድረስ ቃሉ በሚስጥር የተያዘና የታተመ ይሆናል።” የአምላክን መልእክቶች የሚረዱት እነማን ናቸው? “የትኛውም ክፉ ሰው ይህን ቃል ሊረዳ አይችልም፤ ጥልቅ ማስተዋል ያላቸው ግን ይረዱታል።” (ዳንኤል 12:4, 8-10) ስለዚህ አምላክ ተገቢው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ የአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ትርጉም ተሰውሮ እንዲቆይ ያደርጋል።

የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ የወሰነው ጊዜ ባለመድረሱ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ የተረዱበት ጊዜ አለ? አዎ። አምላክ ነገሮችን ይበልጥ ግልጽ የሚያደርግበት ጊዜ ሲደርስ ግን ቀድሞ በነበራቸው አረዳድ ላይ ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኞች ሆነዋል። እንዲህ በማድረግ የኢየሱስ ሐዋርያት የተዉትን ምሳሌ ይከተላሉ፤ ትሑት የነበሩት ሐዋርያት፣ ኢየሱስ እርማት በሰጣቸው ጊዜ ሁሉ አመለካከታቸውን ለማስተካከል ፈቃደኞች ሆነዋል።—የሐዋርያት ሥራ 1:6, 7

አንዲት ትንሽ ልጅ ዳመና ስለሚፈጠርበት መንገድ የተሳሳተ አረዳድ ቢኖራት ያን ያህል ችግር ላይኖረው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ነገር ጋር በተያያዘ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በጣም አስፈላጊ ነው፤ በመሆኑም አንድ ሰው በግሉ በማንበብ ብቻ ይህን መልእክት ለመረዳት መሞከሩ በቂ አይደለም። ስለሆነም የምታነበውን ነገር መረዳት እንድትችል የሌሎችን እርዳታ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል። መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስረዱህ የምትጠይቃቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በትሕትና የሚያጠኑ እንዲሁም ቃሉን ለመረዳት የአምላክን ቅዱስ መንፈስ እርዳታ የሚፈልጉ መሆን ይኖርባቸዋል፤ በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች አሁን የምንኖረው አምላክ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንልን በሚፈልግበት ዘመን ላይ እንደሆነ የሚያምኑ ሊሆኑ ይገባል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንድትወያይ አሊያም jw.org/am በተባለው ድረ ገጽ ላይ የሚያወጡትን ጥልቅ ምርምር የተደረገበት ሐሳብ እንድታነብ እንጋብዝሃለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ማስተዋልን ብትጣራ . . . ስለ አምላክ እውቀት ትቀስማለህ” የሚል ዋስትና ይሰጣል።—ምሳሌ 2:3-5