በእምነታቸው ምሰሏቸው | ሄኖክ
‘አምላክን በሚገባ ደስ አሰኝቷል’
ሄኖክ ረጅም ዕድሜ ኖሯል። ለመገመት የሚከብድ ቢሆንም ይህ ሰው ለ365 ዓመታት ኖሯል፤ የሄኖክ ዕድሜ በዛሬው ጊዜ ካለው በጣም ረጅም የሚባል ዕድሜ ጋር እንኳ ሲወዳደር ከአራት እጥፍ በላይ ነው! በወቅቱ ከነበረው ዓለም አንጻር ሲታይ ግን ሄኖክ ረጅም ዕድሜ ኖሯል ሊባል አይችልም። በዚያን ጊዜ ማለትም ከ5,000 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት የነበረው የሰዎች ዕድሜ በዛሬው ጊዜ ካለው የሰዎች ዕድሜ ጋር ጨርሶ አይወዳደርም። ሄኖክ ሲወለድ የመጀመሪያው ሰው አዳም ዕድሜው ከስድስት መቶ ዓመት በላይ የነበረ ሲሆን ሄኖክ ከተወለደ በኋላም ከሦስት መቶ ዓመት በላይ ኖሯል! አንዳንዶቹ የአዳም ዘሮች ከዚህም የበለጠ ዕድሜ ኖረዋል። ስለዚህ የ365 ዓመቱ ሄኖክ፣ ገና ብዙ ዕድሜ መኖር የሚችል ጠንካራ ሰው ነበር ማለት ይቻላል። የሚያሳዝነው ግን ሄኖክ ከዚህ በኋላ ብዙ ዕድሜ አልኖረም።
የሄኖክ ሕይወት አደጋ ላይ የወደቀ ይመስላል። ከጥቂት ጊዜ በፊት የአምላክን መልእክት የነገራቸው ሰዎች የሰጡት መጥፎ ምላሽ ፊቱ ላይ ድቅን እያለበት ሲሸሽ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። የሰዎቹ ፊት በንዴት ጠቁሯል። እነዚህ ሰዎች ሄኖክን በጣም ይጠሉታል። የተናገረው መልእክት በጣም አበሳጭቷቸዋል፤ ሄኖክን ለላከው አምላክም ከፍተኛ ጥላቻ አላቸው። የሄኖክ አምላክ በሆነው በይሖዋ ላይ ጥቃት መሰንዘር አይችሉም፤ ሄኖክን ግን ማጥቃት ይችላሉ! ምናልባትም ሄኖክ ዳግመኛ የቤተሰቡን ዓይን የማየት አጋጣሚ እንደማያገኝ ተሰምቶት ይሆናል። ሚስቱና ሴቶች ልጆቹ ወይም ልጁ ማቱሳላ አሊያም ደግሞ የልጅ ልጁ ላሜህ ትዝ ብለውት ይሆን? (ዘፍጥረት 5:21-23, 25) የሄኖክ ሕይወት በዚሁ ያበቃ ይሆን?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሄኖክ ብዙም የሚናገረው ነገር የለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኘው ስለ ሄኖክ የሚናገሩ ሦስት አጫጭር ዘገባዎችን ብቻ ነው። (ዘፍጥረት 5:21-24፤ ዕብራውያን 11:5፤ ይሁዳ 14, 15) ይሁንና እነዚህ ጥቅሶች ግሩም እምነት ስለነበረው ስለዚህ ሰው በቂ መረጃ ይሰጡናል። አንተስ እንደ ሄኖክ የምታስተዳድረው ቤተሰብ አለህ? ትክክል እንደሆነ ለምታውቀው ነገር ጥብቅና ለመቆም ስትል አስቸጋሪ ሁኔታዎችን የተጋፈጥክበት ጊዜ አለ? ከሆነ ሄኖክ ካሳየው እምነት ብዙ ትምህርት ልታገኝ ትችላለህ።
“ሄኖክ ከእውነተኛው አምላክ ጋር መሄዱን ቀጠለ”
በሄኖክ ዘመን የሰው ዘር ይከተል የነበረው ጎዳና በጣም የተበላሸ ነበር። ሄኖክ በአዳም የትውልድ መስመር ሰባተኛው ሰው ነበር። እርግጥ ነው፣ በወቅቱ የነበሩት ሰዎች አካላዊ ሁኔታ አዳምና ሔዋን በአንድ ወቅት ለነበራቸው ፍጽምና በጣም ቅርብ ነበር። በዚያ ጊዜ ሰዎች በጣም ረጅም ዕድሜ ይኖሩ የነበረውም ለዚህ ነው። ሆኖም የሰዎች መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ሁኔታ በጣም ተበላሽቶ ነበር። ዓመፅ ተስፋፍቶ ነበር። እንዲህ ያለው ዓመፅ የጀመረው ከአዳም በኋላ ሁለተኛ ትውልድ የሆነው ቃየን አቤልን በገደለበት ወቅት ነው። እንዲያውም ከቃየን ዘሮች መካከል አንዱ፣ ከቃየን ይበልጥ ዓመፀኛና ተበቃይ በመሆኑ ኩራት ሳይሰማው አልቀረም! በሦስተኛው ትውልድ ላይ ደግሞ አንዳንዶች ለየት ያለ ዓመፅ መፈጸም ጀመሩ። ሰዎች የይሖዋን ስም መጥራት ጀመሩ፤ ሆኖም ስሙን ይጠሩ የነበረው እሱን እንደ አምላክ እንደሚቆጥሩትና እንደሚፈሩት በሚያሳይ መንገድ አልነበረም። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው እነዚህ ሰዎች የአምላክን ቅዱስ ስም፣ አክብሮት በጎደለውና እሱን በሚያቃልል መንገድ ይጠቀሙበት ነበር።—ዘፍጥረት 4:8, 23-26
በሄኖክ ዘመን፣ እንዲህ ዓይነቱ ብልሹ ሃይማኖት በጣም ተስፋፍቶ የነበረ ይመስላል። በመሆኑም ሄኖክ እያደገ ሲሄድ አንድ ምርጫ ማድረግ ነበረበት። በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ጋር ተመሳስሎ ለመኖር ይመርጥ ይሆን? ወይስ ሰማይንና ምድርን የፈጠረውን እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ይፈልግ ይሆን? ሄኖክ፣ ይሖዋን ዘፍጥረት 5:22 “ሄኖክ . . . ከእውነተኛው አምላክ ጋር መሄዱን ቀጠለ” በማለት ይነግረናል። ይህ መግለጫ፣ ሄኖክ አምላክን በማይታዘዝ ዓለም ውስጥ አምላክን የሚታዘዝ ብቸኛ ሰው እንደነበረ ይጠቁማል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ በዚህ መንገድ የሚገልጸው የመጀመሪያው ሰው እሱ ነው።
በሚያስደስት መንገድ በመመላለሱ ምክንያት ሰማዕት ሆኖ ስለሞተው ስለ አቤል ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት አድርጎ ሊሆን ይችላል። ሄኖክ የአቤልን ፈለግ ለመከተል መርጧል።ይሄው ጥቅስ፣ ሄኖክ ማቱሳላን ከወለደ በኋላ ከይሖዋ ጋር መሄዱን እንደቀጠለ ይናገራል። በመሆኑም ሄኖክ 65 ዓመት ገደማ ሲሆነው የራሱ ቤተሰብ እንደነበረው መመልከት እንችላለን። ሄኖክ ሚስት ነበረችው፤ እርግጥ የሚስቱ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተገለጸም። በተጨማሪም ቁጥራቸው ያልተገለጸ ‘ወንዶችና ሴቶች ልጆች’ ነበሩት። ቤተሰቡን የመንከባከብ ኃላፊነት ያለበት አንድ አባት ከአምላክ ጋር መሄድ ከፈለገ ቤተሰቡን አምላክ በሚፈልገው መንገድ መያዝ ይጠበቅበታል። ሄኖክ ምንጊዜም ለሚስቱ ታማኝ እንዲሆን ይሖዋ እንደሚጠብቅበት ተገንዝቦ ነበር። (ዘፍጥረት 2:24) ልጆቹንም ቢሆን ስለ ይሖዋ አምላክ ለማስተማር የተቻለውን ያህል ጥረት እንዳደረገ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይህ ምን ውጤት አስገኘ?
በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ዘገባ ስለዚህ ጉዳይ ዝርዝር መረጃ አይሰጠንም። የጥፋት ውኃ እስከመጣበት ዓመት ድረስ በሕይወት ስለነበረውና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ሰዎች ሁሉ ረጅም ዕድሜ ስለኖረው ስለ ሄኖክ ልጅ ስለ ማቱሳላ እምነት፣ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚናገሩት ነገር የለም። ሆኖም ማቱሳላ፣ ላሜህ የሚባል ልጅ ነበረው። ላሜህና አያቱ ሄኖክ በአንድ ዘመን ላይ ኖረዋል፤ ምክንያቱም ላሜህ የተወለደው አያቱ ሄኖክ ከመሞቱ ከመቶ ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ነው። ላሜህ ጠንካራ እምነት ያለው ሰው ነበር። በይሖዋ መንፈስ መሪነት ስለ ልጁ ስለ ኖኅ ትንቢት የተናገረ ሲሆን ይህ ትንቢት ከጥፋት ውኃው በኋላ ፍጻሜውን አግኝቷል። እንደ ቅድመ አያቱ እንደ ሄኖክ ሁሉ ኖኅም፣ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች መካከል ከአምላክ ጋር የሄደ ብቸኛው ሰው እንደሆነ ተነግሮለታል። ኖኅ ሄኖክን አግኝቶት አያውቅም። ሆኖም ሄኖክ ትልቅ ውርስ ትቶለት አልፏል። ኖኅ ቅድመ አያቱ ሄኖክ ስላሳየው ግሩም እምነት ሰምቶ ሊሆን ይችላል፤ ኖኅ ምናልባትም ከአባቱ ከላሜህ፣ ከአያቱ ከማቱሳላ አሊያም ደግሞ ኖኅ 366 ዓመት እስኪሆነው ድረስ በሕይወት ከኖረው ከሄኖክ አባት ከያሬድ ስለ ሄኖክ ታሪክ ሰምቶ ሊሆን ይችላል።—ዘፍጥረት 5:25-29፤ 6:9፤ 9:1
በሄኖክና በአዳም መካከል ያለውን ልዩነት እስቲ አስበው። አዳም ፍጹም የነበረ ቢሆንም በይሖዋ ላይ ኃጢአት በመሥራት ለዘሮቹ ዓመፅና መከራ አውርሷል። ሄኖክ ግን ፍጹም ባይሆንም እንኳ ከአምላክ ጋር በመሄድ ለዘሮቹ ግሩም የእምነት ምሳሌ አውርሷቸዋል። አዳም የሞተው ሄኖክ የ308 ዓመት ሰው ሳለ ነበር። የአዳም ቤተሰቦች ራስ ወዳድ የሆነው አባታቸው ሲሞት አዝነው ይሆን? ስለዚህ ጉዳይ የምናውቀው ነገር የለም። የሆነው ሆኖ፣ ሄኖክ “ከእውነተኛው አምላክ ጋር መሄዱን [ቀጥሏል]።”—ዘፍጥረት 5:24
አንተም ቤተሰብ የምታስተዳድር ከሆነ ሄኖክ ከተወው የእምነት ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንደምትችል ተመልከት። የቤተሰብህን ቁሳዊ ፍላጎት ማሟላት አስፈላጊ እንደሆነ ባይካድም የቤተሰብህን መንፈሳዊ ፍላጎት የማሟላትን ያህል አስፈላጊ የሆነ ነገር የለም። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ይህን ፍላጎት ማሟላት የምትችለው በምትናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን በተግባርም ምሳሌ በመሆን ነው። የአምላክን መሥፈርቶች በመከተል ልክ እንደ ሄኖክ ከአምላክ ጋር ለመሄድ ከመረጥክ ቤተሰቦችህ ሊከተሉ የሚችሉት ግሩም ምሳሌ ልታወርሳቸው ትችላለህ።
ሄኖክ ‘ስለ እነዚህ ሰዎች ተንብዮአል’
ሄኖክ እምነት በሌለው ዓለም ውስጥ የእምነት ሰው ሆኖ ሲኖር ብቸኝነት ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። አምላኩ ይሖዋስ ሄኖክን *
ተመልክቶት ይሆን? አዎ። አንድ ቀን ይሖዋ ይህን ታማኝ አገልጋዩን አነጋገረው። ሄኖክ በዘመኑ ለነበሩት ሰዎች አንድ መልእክት እንዲያስተላልፍ አምላክ ተልእኮ ሰጠው። በዚህ መንገድ ይሖዋ ሄኖክን ነቢይ አድርጎ ላከው፤ በመሆኑም መልእክታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ ከሚገኙ ነቢያት መካከል ሄኖክ የመጀመሪያው ነው። ይህን ማወቅ የቻልነው የኢየሱስ ወንድም የሆነው ይሁዳ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ፣ ሄኖክ ስለተናገረው ትንቢት በመንፈስ መሪነት በመጻፉ ነው።ሄኖክ የተናገረው ትንቢት ምን ነበር? ትንቢቱ እንዲህ የሚል ነበር፦ “እነሆ! ይሖዋ ከአእላፋት ቅዱሳን መላእክቱ ጋር መጥቷል፤ የመጣውም በሁሉ ላይ ለመፍረድ፣ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለአምላክ አክብሮት በጎደለው መንገድ የፈጸሙትን ክፉ ድርጊትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ኃጢአተኞች በእሱ ላይ የተናገሩትን ክፉ ቃል ለማጋለጥ ነው።” (ይሁዳ 14, 15) እዚህ ላይ ሄኖክ ትንቢቱን የተናገረው ልክ እንደተፈጸመ ማለትም አምላክ በትንቢቱ ላይ የተገለጸውን ነገር እንደፈጸመ አድርጎ እንደሆነ አስተውለህ ይሆናል። ሌሎች በርካታ ትንቢቶችም የተጻፉት በዚህ መንገድ ነው። ነቢዩ፣ ገና ያልተፈጸመን ነገር እንደተፈጸመ አድርጎ የተናገረው ትንቢቱ መፈጸሙ እንደማይቀር ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ስለሆነ ነው።—ኢሳይያስ 46:10
ሄኖክ ይህን የፍርድ መልእክት ሲያውጅ ወይም እያዳመጡት ላሉ ሰዎች ሲሰብክ ምን ዓይነት ሁኔታ ያጋጠመው ይመስልሃል? የማስጠንቀቂያ መልእክቱ በጣም ኃይለኛ ነበር፤ እነዚህ ሰዎች “ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው” እንደሆኑ የሚገልጽ ከመሆኑም ሌላ ድርጊታቸው ‘ለአምላክ አክብሮት የሌለው’ እና ‘ክፉ’ እንደሆነ ይናገራል። ትንቢቱ የሰው ልጆች ከኤደን ከተባረሩ በኋላ የገነቡት ዓለም ሙሉ በሙሉ ብልሹ መሆኑን የሚገልጽ ነው። በወቅቱ የነበረው ዓለም፣ ይሖዋ ለጦርነት ከተሰለፉትና ኃያላን ከሆኑት “አእላፋት ቅዱሳን መላእክቱ” ጋር በሚመጣበት ጊዜ ከባድ ጥፋት ይጠብቀው ነበር። ሄኖክ ይህን መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ በድፍረት አውጇል፤ ያውም ብቻውን! በወቅቱ ወጣት የነበረው ላሜህ አያቱ ያሳየውን ድፍረት በመገረም ተመልክቶ ሊሆን ይችላል። በእርግጥም ሄኖክ ያሳየው ድፍረት የሚያስገርም ነበር።
ሄኖክ ስላሳየው እምነት መመርመራችን እኛም ለምንኖርበት ዓለም ያለን አመለካከት አምላክ ካለው አመለካከት ጋር ተመሳሳይ መሆን አለመሆኑን ቆም ብለን እንድናስብ ያነሳሳን ይሆናል። ሄኖክ በድፍረት ያወጀው የፍርድ መልእክት በዚያ ዘመን ለነበረው ዓለም ያስፈልግ እንደነበረ ሁሉ አሁን ላለንበት ዓለምም አስፈላጊ ነው። ሄኖክ በተናገረው ማስጠንቀቂያ መሠረት ይሖዋ በኖኅ ዘመን የነበረውን ፈሪሃ አምላክ የሌለው ዓለም በውኃ አጥፍቶታል። በዚያን ወቅት የተከሰተው ጥፋት ወደፊት ለሚመጣው ይበልጥ ታላቅ የሆነ ጥፋት ምሳሌ ሆኗል። (ማቴዎስ 24:38, 39፤ 2 ጴጥሮስ 2:4-6) አምላክ በዚያ ወቅት እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ፈሪሃ አምላክ በሌለው በዚህ ዓለም ላይ የጽድቅ ፍርዱን ለማስፈጸም ከአእላፋት ቅዱሳን መላእክቱ ጋር በተጠንቀቅ እየተጠባበቀ ነው። እያንዳንዳችን ሄኖክ ያወጀውን ማስጠንቀቂያ ልብ ማለት እንዲሁም ይህን ማስጠንቀቂያ ለሌሎች መናገር ያስፈልገናል። እርግጥ ቤተሰቦቻችንና ጓደኞቻችን ከእኛ የተለየ አቋም ይይዙ ይሆናል። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ብቻችንን እንደሆንን ሊሰማን ይችላል። ሆኖም ይሖዋ ሄኖክን እንዳልተወው ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ታማኝ አገልጋዮቹንም አይተዋቸውም!
‘ሞትን እንዳያይ ወደ ሌላ ቦታ ተወሰደ’
የሄኖክ ሕይወት ያበቃው እንዴት ነበር? የሄኖክ አሟሟት፣ ከሕይወቱ የበለጠ አስገራሚና ትኩረት የሚስብ ነው። በዘፍጥረት ላይ የሚገኘው ዘገባ የሚናገረው የሚከተለውን ብቻ ነው፦ “ሄኖክ ከእውነተኛው አምላክ ጋር መሄዱን ቀጠለ። አምላክ ስለወሰደውም ከዚያ በኋላ አልተገኘም።” (ዘፍጥረት 5:24) አምላክ ሄኖክን የወሰደው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ተጨማሪ መረጃ ይሰጠናል፦ “ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ወደ ሌላ ቦታ ተወሰደ፤ አምላክ ወደ ሌላ ቦታ ስለወሰደውም የትም ቦታ ሊገኝ አልቻለም፤ ከመወሰዱ በፊት አምላክን በሚገባ ደስ እንዳሰኘ ተመሥክሮለት ነበርና።” (ዕብራውያን 11:5) ጳውሎስ “ሞትን እንዳያይ . . . ተወሰደ” ሲል ምን ማለቱ ነው? አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አምላክ ሄኖክን ወደ ሰማይ እንደወሰደው ይናገራሉ። ሆኖም ይህ ሊሆን አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ በመሄድ ረገድ የመጀመሪያ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ይናገራል።—ዮሐንስ 3:13
ታዲያ ሄኖክ “ሞትን እንዳያይ . . . ተወሰደ” የተባለው ከምን አንጻር ነው? ሄኖክ በጠላቶቹ እጅ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዳይገደል ይሖዋ ታድጎት መሆን አለበት፤ በዚህ መንገድ ሳይሠቃይ በሞት እንዲያንቀላፋ በማድረግ ወስዶታል ሊባል ይችላል። ከመወሰዱ በፊት ግን “አምላክን በሚገባ ደስ እንዳሰኘ ተመሥክሮለት ነበር።” እንዴት? ልክ ከመሞቱ በፊት፣ አምላክ ገነት የሆነችውን ምድር በራእይ አሳይቶት ሊሆን ይችላል። ሄኖክ በይሖዋ ፊት ሞገስ እንዳገኘ የሚያሳየውን ይህን ግልጽ ምልክት ካየ በኋላ በሞት አንቀላፋ። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሄኖክን ጨምሮ ስለ ሌሎች ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ሲናገር “እምነታቸውን እንደጠበቁ ሞቱ” ብሏል። (ዕብራውያን 11:13) ከዚያ በኋላ ጠላቶቹ አስከሬኑን ለመፈለግ ሞክረው ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም የሄኖክ አስከሬን “የትም ቦታ ሊገኝ አልቻለም”፤ ይህ የሆነው ይሖዋ እነዚህ ሰዎች አስከሬኑን እንዳያረክሱት ወይም የሐሰት አምልኮን ለማራመድ እንዳይጠቀሙበት ለማገድ ሲል ስለሰወረው ሊሆን ይችላል። *
መጽሐፍ ቅዱስ ሄኖክ “ተወሰደ” ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ተመልክተናል፤ አሁን ደግሞ ሕይወቱ ያበቃው እንዴት እንደሆነ በዓይነ ሕሊናችን ለመሳል እንሞክር። እስቲ የሚከተለው ሁኔታ እንደተፈጠረ አድርገን እናስብ። ሄኖክ ከጠላቶቹ ሲሸሽ ቆይቶ አሁን በጣም ደክሞታል። ጠላቶቹ በተናገረው የፍርድ መልእክት ደማቸው ፈልቶ እያሳደዱት ነው። ሄኖክ መደበቂያ ቦታ አግኝቶ አረፍ አለ፤ ይሁንና ጠላቶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈልገው እንደሚያገኙት ገብቶታል። በአሰቃቂ ሁኔታ የሚገደልበት ጊዜ በጣም እንደተቃረበ ተሰምቶታል። አረፍ እንዳለ ወደ አምላኩ መጸለይ ጀመረ። ከዚያም አስገራሚ የሆነ የመረጋጋት ስሜት ተሰማው። ልክ በእውን እንደሚያየው ያለ ራእይ እየተመለከተ ጭልጥ ብሎ ሄደ።
ሄኖክ፣ እሱ ከሚያውቀው በጣም የተለየ ዓለም በፊቱ ወለል ብሎ ሲታየው በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ቦታው ልክ እንደ ኤደን ገነት ያለ ውብ ስፍራ ነው፤ ሆኖም ሰዎች እንዳይገቡ የሚከለክሉ ኪሩቤል በዚያ የሉም። ጤናማና ወጣት የሆኑ ብዙ ወንዶችና ሴቶች ይታያሉ። የአካባቢውን ሰላም የሚያደፈርስ ምንም ነገር የለም። ሄኖክን ያስመረረው ጥላቻና ስደትም ሙሉ በሙሉ ተወግዷል። ከዚያም ይሖዋ እንደተደሰተበትና እንደሚወደው እንዲሁም በፊቱ ሞገስ እንዳገኘ ተሰማው። ወደፊት በዚህ ቦታ መኖሩ እንደማይቀር እርግጠኛ ሆነ። ሄኖክ ከምንጊዜውም ይበልጥ ውስጣዊ ሰላምና የመረጋጋት ስሜት ተሰማው፤ ከዚያም ዓይኖቹን ሲከድን ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወሰደው።
ሄኖክ እስካሁን በሞት እንዳንቀላፋ ይገኛል፤ ሆኖም ገደብ የሌለው የማስታወስ ችሎታ ያለው ይሖዋ አምላክ፣ ሄኖክን ፈጽሞ አይረሳውም! ኢየሱስ ቃል በገባው መሠረት፣ አምላክ የሚያስታውሳቸው ሰዎች በሙሉ የክርስቶስን ድምፅ ሰምተው ከመቃብር ይወጣሉ፤ ከዚያም ውብ በሆነና ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ይኖራሉ።—ዮሐንስ 5:28, 29
አንተስ እንዲህ ባለው ዓለም ውስጥ መኖር አትፈልግም? ሄኖክን በአካል ስታገኘው ምን ያህል እንደምትደሰት አስበው። ሄኖክ ብዙ አስደናቂ ታሪኮችን ሊነግረን እንደሚችል መገመት ትችላለህ! የእሱን አሟሟት በተመለከተ የገመትነው ነገር ትክክል ይሁን አይሁን ይነግረናል። ይሁንና በአሁኑ ጊዜም ከሄኖክ ልንማር የሚገባን አስፈላጊ ትምህርት አለ። ጳውሎስ ስለ ሄኖክ ከተናገረ በኋላ “ያለ እምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም” ብሏል። (ዕብራውያን 11:6) በእርግጥም ሄኖክ ድፍረትና እምነት በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተላችን በጣም አስፈላጊ ነው!
^ አን.14 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን፣ ይሁዳ ይህን ሐሳብ የወሰደው መጽሐፈ ሄኖክ ከሚባል አንድ የአዋልድ መጽሐፍ እንደሆነ ይናገራሉ፤ ይህ የአዋልድ መጽሐፍ ምንጩ ያልታወቀና እውነት የማይመስሉ ታሪኮችን የያዘ ከመሆኑም ሌላ ሄኖክ እንደጻፈው ተደርጎ መነገሩ ሐሰት ነው። መጽሐፉ የሄኖክን ትንቢት በትክክል የሚጠቅስ ቢሆንም ይህ ሐሳብ የተወሰደው አሁን ከጠፋ ጥንታዊ ጽሑፍ ላይ ወይም በቃል ሲተላለፍ ከቆየ ታሪክ ሊሆን ይችላል። ይሁዳም ይህን ትንቢት ያገኘው ከተመሳሳይ ምንጭ ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ደግሞ የሄኖክን ሕይወት ከሰማይ ሆኖ የተመለከተው ኢየሱስ ነግሮት ሊሆን ይችላል።
^ አን.20 አምላክ የሙሴና የኢየሱስ አስከሬንም ቢሆን እንዳይገኝ ያደረገው ሰዎች አስከሬናቸውን እንዳያረክሱት ወይም የሐሰት አምልኮን ለማራመድ እንዳይጠቀሙበት ለማገድ ሲል ሊሆን ይችላል።—ዘዳግም 34:5, 6፤ ሉቃስ 24:3-6፤ ይሁዳ 9