በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት ምንድን ነው?

አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት—በዛሬው ጊዜ

አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት—በዛሬው ጊዜ

በዛሬው ጊዜ ሰዎች በጭቆና ቀንበር ሥር ወድቀዋል። ብዙዎች እረፍት ለማግኘት በተደጋጋሚ ወደ አምላክ የሚጮኹ ሲሆን ‘እፎይታ የምናገኝበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ ያሳስባቸዋል። ታዲያ እነዚህ ሰዎች እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትን ጩኸት አምላክ ይሰማል? በሌላ በኩል፣ ከሚደርስባቸው ጭቆና ለመገላገል ጦርነትን እንደ አማራጭ ስለሚከተሉ ሰዎች ምን ማለት ይቻላል? አምላክ፣ የሚያካሂዱት ጦርነት ተገቢ እንደሆነ በመቁጠር ጥረታቸውን ይደግፋል?

አርማጌዶን ጦርነቶችን ሁሉ የሚያስወግድ ጦርነት ይሆናል

በመጀመሪያ፣ የሚከተለውን እውነታ ማወቃችን ሊያጽናናን ይችላል፦ አምላክ በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ያለውን መከራ ያያል፤ ደግሞም እርምጃ መውሰዱ አይቀርም። (መዝሙር 72:13, 14) በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘መከራ ለሚቀበሉ ሰዎች እረፍት እንደሚሰጣቸው’ ቃል ገብቷል። ይህ የሚሆነው መቼ ነው? “ጌታ ኢየሱስ ከኃያላን መላእክቱ ጋር ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ . . . አምላክን በማያውቁትና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ለሚገልጸው ምሥራች በማይታዘዙት ላይ የበቀል እርምጃ ይወስዳል።” (2 ተሰሎንቄ 1:7, 8) ኢየሱስ የሚገለጠው ወደፊት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ያንን ጊዜ ‘ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ታላቅ ቀን’ ወይም አርማጌዶን በማለት ይጠራዋል።—ራእይ 16:14, 16

ወደፊት በሚካሄደው በዚያ ጦርነት ላይ አምላክ ክፉዎችን ለመዋጋት የሚጠቀመው ሰዎችን ሳይሆን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስንና ሌሎች ኃያላን መንፈሳዊ ፍጥረታትን ነው። ይህ የሰማይ ሠራዊት ማንኛውንም ዓይነት ጭቆና ያስወግዳል።—ኢሳይያስ 11:4፤ ራእይ 19:11-16

ዛሬም አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት አልተለወጠም። አሁንም ቢሆን አምላክ ጦርነትን የሚያየው ጭቆናና ክፋትን ለማስቆም የሚያስችል ትክክለኛ መንገድ አድርጎ ነው። ይሁን እንጂ በታሪክ ዘመናት በሙሉ እንደታየው እንዲህ ዓይነቱ ጦርነት መቼ መካሄድና ማን መዋጋት እንዳለበት የሚወስነው አምላክ ራሱ ነው። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው አምላክ ወደፊት በሚያካሂደው ጦርነት ክፋትን ለማስቆምና ጨቋኞችን ለመበቀል ወስኗል፤ በጦርነቱ ላይ የሚዋጋው ደግሞ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እንግዲያው በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የሚካሄዱት ጦርነቶች፣ የቱንም ያህል ተገቢ ቢመስሉም የአምላክ ድጋፍ የላቸውም።

ይህን በምሳሌ ለማስረዳት፣ አባታቸው በሌለበት መጣላት የጀመሩ ሁለት ወንድማማቾችን ለማሰብ ሞክር። እነዚህ ልጆች መጣላታቸውን አቁመው አባታቸውን በስልክ አናገሩት። አንደኛው ልጅ ጠቡን የጀመረው ወንድሙ እንደሆነ ሲገልጽ ሌላኛው ደግሞ ወንድሙ መጥፎ ነገር እንዳደረገበት ይናገራል። ሁለቱም አባታቸው እነሱን እንደሚደግፍ በማሰብ ስሞታ አሰሙ። ይሁን እንጂ አባታቸው ሁለቱንም ከሰማ በኋላ ቤት መጥቶ እስኪያስታርቃቸው ድረስ መጣላት እንዲያቆሙ ነገራቸው። ወንድማማቾቹ ለተወሰነ ጊዜ ከጠበቁት በኋላ በድጋሚ መጣላት ጀመሩ። አባትየው ቤት ሲደርስ ልጆቹ መመሪያውን ባለማክበራቸው ሁለቱንም ቀጣቸው።

በዛሬው ጊዜም እርስ በርስ የሚዋጉ ብሔራት ብዙውን ጊዜ አምላክ ከእነሱ ጎን እንዲቆም ይጸልያሉ። አምላክ ግን የትኛውንም ወገን አይደግፍም። ከዚህ ይልቅ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ” እንዲሁም “ራሳችሁ አትበቀሉ” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ሮም 12:17, 19) ከዚህም በላይ የሰው ልጆች እሱ በአርማጌዶን የሚወስደውን እርምጃ ‘በትዕግሥት መጠበቅ’ እንዳለባቸው ተናግሯል። (መዝሙር 37:7 የግርጌ ማስታወሻ) ብሔራት፣ አምላክ እርምጃ እስኪወስድ ድረስ ከመጠበቅ ይልቅ ጦርነትን አማራጭ ሲያደርጉ አምላክ ድርጊታቸውን በእብሪት የተወሰደ የኃይል እርምጃ አድርጎ ስለሚመለከተው በሁኔታው አይደሰትም። በመሆኑም አምላክ በአርማጌዶን ጦርነት ቁጣውን ይገልጻል፤ እንዲሁም ‘ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ በማስወገድ’ በብሔራት መካከል የሚካሄደው ግጭት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ ያደርጋል። (መዝሙር 46:9፤ ኢሳይያስ 34:2) በእርግጥም አርማጌዶን ጦርነቶችን ሁሉ የሚያጠፋ ጦርነት ይሆናል።

የጦርነት መወገድ የአምላክ መንግሥት ከሚያመጣቸው ብዙ በረከቶች መካከል አንዱ ነው። ኢየሱስ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም” በሚለው የታወቀ ጸሎቱ ላይ ስለዚህ መንግሥት ተናግሯል። (ማቴዎስ 6:10) የአምላክ መንግሥት ጦርነትን ብቻ ሳይሆን የጦርነት ዋነኛ መንስኤ የሆነውን ክፋትን ጭምር ያስወግዳል። * (መዝሙር 37:9, 10, 14, 15) የኢየሱስ ተከታዮች የአምላክ መንግሥት የሚያመጣውን በረከት በጉጉት መጠበቃቸው አያስገርምም።—2 ጴጥሮስ 3:13

ይሁንና የአምላክ መንግሥት መከራን፣ ጭቆናንና ክፋትን በሙሉ እስኪያስወግድ የምንጠብቀው ለምን ያህል ጊዜ ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ ማግኘታቸው የምንኖረው በዚህ የነገሮች ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀናት’ ውስጥ እንደሆነ ይጠቁማል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) * በቅርቡ የአምላክ መንግሥት በአርማጌዶን ጦርነት አማካኝነት የመጨረሻዎቹ ቀናት እንዲደመደሙ ያደርጋል።

ቀደም ብሎ እንደተገለጸው ለመጨረሻ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ጦርነት የሚጠፉት ‘ስለ ጌታችን ኢየሱስ ለሚገልጸው ምሥራች የማይታዘዙ’ ሰዎች ይሆናሉ። (2 ተሰሎንቄ 1:8) ይሁን እንጂ አምላክ ክፉዎችን ጨምሮ በማንም ሰው ሞት እንደማይደሰት አስታውስ። (ሕዝቅኤል 33:11) አምላክ በዚህ የመጨረሻ ጦርነት “ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ” ፍጻሜው ከመምጣቱ በፊት በአሁኑ ጊዜ ስለ ጌታችን ኢየሱስ የሚገልጸው ምሥራች “ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር” እንዲሰበክ እያደረገ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:8, 9፤ ማቴዎስ 24:14፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) አዎን፣ በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያካሂዱት ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ አማካኝነት ሰዎች አምላክን ማወቅ፣ ስለ ኢየሱስ ለሚገልጸው ምሥራች መታዘዝና በሕይወት ተርፈው ጦርነት የማይኖርበትን ጊዜ ማየት የሚችሉበት አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል።

^ አን.9 በተጨማሪም የአምላክ መንግሥት፣ የሰው ዘር ጠላት የሆነውን ሞትን ያጠፋል። በዚህ መጽሔት ላይ “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው” በሚለው ርዕስ ሥር እንደተገለጸው አምላክ በታሪክ ዘመናት በሙሉ በተደረጉት ጦርነቶች ያለቁትን ጨምሮ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች ከሞት ያስነሳል።

^ አን.10 የመጨረሻዎቹን ቀናት አስመልክቶ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ተመልከት።