በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት ምንድን ነው?

አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት ምንድን ነው?

ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ ትሰጣለህ? ብዙ ሰዎች አምላክ ጦርነትን እንደሚደግፍ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች አምላክ በጥንት ዘመን አንዳንድ አገልጋዮቹን በጦርነት እንዲካፈሉ መመሪያ መስጠቱን ማስረጃ አድርገው የሚያቀርቡ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባም ቢሆን የዚህን እውነተኝነት ያረጋግጣል። ሌሎች ደግሞ የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ጠላቶቻቸውን እንዲወዱ እንዳስተማረ ይገልጻሉ። (ማቴዎስ 5:43, 44) በመሆኑም አምላክ በአንድ ወቅት ስለ ጦርነት የነበረው አመለካከት እንደተለወጠና በዛሬው ጊዜ ጦርነትን እንደማይደግፍ ይሰማቸዋል።

አንተስ ምን ይሰማሃል? አምላክ ጦርነትን ይደግፋል? ከሆነስ በዛሬው ጊዜ ግጭቶች ሲካሄዱ ከየትኛው ወገን ጎን ይቆማል? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘትህ ስለ ጦርነት ባለህ አመለካከት ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ጦርነትን እንደሚደግፍ እንዲሁም አንተ የምትደግፈውን ወገን እንደሚያግዝ ብታውቅ እንደምትደሰት ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም የአንተ ወገን ድል እንደሚቀናው እርግጠኛ ነህ። በሌላ በኩል ደግሞ አምላክ የሚደግፈው በተቃራኒ ወገን ያለውን ሠራዊት እንደሆነ ብታውቅ ምን ይሰማሃል? በጉዳዩ ላይ ያለህን አቋም እንደገና ማጤን እንዳለብህ ሊሰማህ ይችላል።

ይሁንና አንድ ወሳኝ ጉዳይ አለ፦ አምላክ ስለ ጦርነት ያለውን አመለካከት ማወቅህ ለእሱ ባለህ አመለካከት ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። የሰው ልጆች በሚያካሂዱት ጦርነት የተነሳ ክፉኛ ከተጎዱት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ከሆንክ ለሚከተሉት ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ ማወቅ እንደምትፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም፦ አንዳንዶች እንደሚሰማቸው አምላክ ጦርነትን ይወዳል? ሰዎች በጦርነት እንዲሠቃዩ ይፈቅዳል? ወይም ጦርነት እንዲካሄድ ያበረታታል? አሊያም በጦርነት እጁን ባያስገባም ሌሎች ሲጨቆኑ ዝም ብሎ ያያል?

መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መልስ የዚህ ፍጹም ተቃራኒ መሆኑን ስታውቅ ልትገረም ትችላለህ። እንዲያውም አምላክ ጥንትም ሆነ ዛሬ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት ፈጽሞ አልተለወጠም። በጥንት ዘመንም ሆነ ኢየሱስ ምድር ላይ በኖረበት በመጀመሪያው መቶ ዘመን አምላክ ስለ ጦርነት ምን አመለካከት እንደነበረው መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን እንመልከት። እንዲህ ማድረጋችን አምላክ በዛሬው ጊዜ ስለ ጦርነት ምን አመለካከት እንዳለው እንዲሁም ጦርነት ወደፊትም ይቀጥል እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ይረዳናል።