የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ ትንቢት መያዙ ምን ያሳያል?
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዝርዝር የሰፈሩ ብዙ ትንቢቶች ይገኛሉ። ወደፊት የሚፈጸሙ ነገሮችን በዝርዝር መተንበይ የሚችል ሰው የለም። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ ማግኘታቸው መጽሐፉ የአምላክ ቃል እንደሆነ አሳማኝ ማስረጃ ነው።—ኢያሱ 23:14ን እና 2 ጴጥሮስ 1:20, 21ን አንብብ።
ፍጻሜ ያገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በአምላክ ለማመን ጠንካራ መሠረት ይሆኑናል። (ዕብራውያን 11:1) በተጨማሪም አምላክ ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ የሰጣቸው ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች እንድንሆን ያደርጉናል። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የተረጋገጠ ተስፋ እንዲኖረን ያስችላል።—መዝሙር 37:29ን እና ሮም 15:4ን አንብብ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የሚጠቅሙን እንዴት ነው?
አንዳንድ ትንቢቶች የአምላክ አገልጋዮች እርምጃ እንዲወስዱ ማስጠንቀቂያ ይዘዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች አንዳንድ ትንቢቶች መፈጸማቸውን ሲያዩ ኢየሩሳሌምን ለቀው ወጥተዋል። አብዛኛው የኢየሩሳሌም ሕዝብ ኢየሱስን ባለመቀበሉ ከተማዋ ከጊዜ በኋላ ስትጠፋ ክርስቲያኖች ከአካባቢው ርቀው ሰላም በሰፈነበት ስፍራ ላይ ይገኙ ነበር።—ሉቃስ 21:20-22ን አንብብ።
ፍጻሜ ካገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መረዳት እንደምንችለው የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ሰብዓዊ መንግሥታትንና መስተዳድሮችን ጠራርጎ ያጠፋል። (ዳንኤል 2:44፤ ሉቃስ 21:31) ስለሆነም እያንዳንዱ ሰው አምላክ የሾመውን ንጉሥ ይኸውም የኢየሱስ ክርስቶስን ሞገስ ለማግኘት አሁኑኑ አጣዳፊ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል።—ሉቃስ 21:34-36ን አንብብ።