በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት መኖር ይችላል?

የሞቱ ሰዎች ተስፋ አላቸው?

የሞቱ ሰዎች ተስፋ አላቸው?

ዳግመኛ በሕይወት መኖር ይችላሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ የኢየሱስን ድምፅ ሰምተው የሚወጡበት ሰዓት ይመጣል።’ዮሐንስ 5:28, 29

ኢየሱስ ከላይ የተናገረው ሐሳብ በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር መቃብሮች ባዶ የሚሆኑበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚጠቁም ነው። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ፈርናንዶ “ለመጀመሪያ ጊዜ ዮሐንስ 5:28, 29⁠ን ሳነብ በጣም ተደንቄ ነበር። ጥቅሱ እውነተኛ ተስፋ የሰጠኝ ሲሆን ስለወደፊቱ ጊዜም ብሩህ አመለካከት እንዲኖረኝ አስችሎኛል” በማለት ተናግሯል።

በጥንት ዘመን የኖረው ታማኙ ኢዮብ፣ አምላክ ከሞት ሊያስነሳው እንደሚችል እምነት ነበረው። ኢዮብ “ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት ሊኖር ይችላል?” ሲል ጠይቋል። ከዚያም በሙሉ ልብ እንዲህ የሚል መልስ ሰጥቷል፦ “እፎይታ የማገኝበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ፣ የግዳጅ አገልግሎት በምፈጽምበት ዘመን [በመቃብር የሚያሳልፈውን ጊዜ ያመለክታል] ሁሉ በትዕግሥት እጠብቃለሁ። አንተ ትጣራለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ።”—ኢዮብ 14:14, 15

የአልዓዛር ትንሣኤ የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ እንድንጠባበቅ ያስችለናል

የአልዓዛር እህት ማርታ ስለ ትንሣኤ ተስፋ ታውቅ ነበር። አልዓዛር በሞተ ጊዜ ኢየሱስ “ወንድምሽ ይነሳል” አላት። በዚህ ጊዜ ማርታ “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ። በእኔ የሚያምን ሁሉ ቢሞት እንኳ እንደገና ሕያው ይሆናል” አላት። (ዮሐንስ 11:23-25) ከዚያም ኢየሱስ ወዲያውኑ አልዓዛርን ከሞት አስነሳው! ይህ አስደሳች ታሪክ ወደፊት ለሚፈጸመው ታላቅ ክንውን እንደ ቅምሻ ነው። በዚያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትንሣኤ ሲከናወን ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር ይታይህ!

ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ የሚሄዱ ይኖራሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? የአምላክ ቃል የኢየሱስ ትንሣኤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ከሚገኙት ስምንት ትንሣኤዎች እንደሚለይ ይጠቁማል። እነዚያ ስምንት ሰዎች ከሞት ከተነሱ በኋላ የኖሩት እዚሁ ምድር ላይ ነው። ሆኖም የኢየሱስን ትንሣኤ በተመለከተ እንዲህ የሚል ዘገባ እናነባለን፦ “ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሄደ ሲሆን አሁን በአምላክ ቀኝ ይገኛል።” (1 ጴጥሮስ 3:21, 22) ከኢየሱስ ሌላ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ የሚሄድ ይኖራል? ኢየሱስ ቀደም ብሎ ለሐዋርያቱ “ሄጄ ቦታ ባዘጋጀሁላችሁ ጊዜ እኔ ባለሁበት እናንተም እንድትሆኑ እንደገና መጥቼ እኔ ወዳለሁበት እወስዳችኋለሁ” ብሏቸው ነበር።—ዮሐንስ 14:3

ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ በዚያ ለደቀ መዛሙርቱ ቦታ አዘጋጅቶላቸዋል። ሰማያዊ ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች  አጠቃላይ ቁጥር 144,000 ነው። (ራእይ 14:1, 3) ሆኖም እነዚህ የኢየሱስ ተከታዮች እዚያ ሄደው ምን ያደርጋሉ?

ብዙ የሚሠሩት ሥራ ይኖራቸዋል! መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በመጀመሪያው ትንሣኤ ተካፋይ የሆኑ ሁሉ ደስተኞችና ቅዱሳን ናቸው፤ ሁለተኛው ሞት በእነዚህ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ከዚህ ይልቅ የአምላክና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከእሱም ጋር ለ1,000 ዓመት ይነግሣሉ።” (ራእይ 20:6) ሰማያዊ ትንሣኤ የሚያገኙት እነዚህ ሰዎች ነገሥታትና ካህናት በመሆን ከክርስቶስ ጋር ምድርን ይገዛሉ።

ቀጥሎስ እነማን ይነሳሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? የአምላክ ቃል ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ይዟል፦ “እነዚህ ሰዎች ራሳቸው ተስፋ እንደሚያደርጉት ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ በአምላክ ተስፋ አደርጋለሁ።”የሐዋርያት ሥራ 24:15

የአምላክ ቃል በቢሊዮን የሚቆጠሩ የሞቱ ሰዎች ዳግም ሕያው እንደሚሆኑ ማረጋገጫ ይሰጠናል

ጳውሎስ “ጻድቃን” በማለት ከጠራቸው ሰዎች ውስጥ እነማን ይገኙበታል? አንድ ምሳሌ እንመልከት። ታማኙ ዳንኤል በሕይወቱ መገባደጃ ላይ “ታርፋለህ፤ ሆኖም በዘመኑ ፍጻሜ ዕጣ ፋንታህን ለመቀበል ትነሳለህ” በማለት ተነግሮት ነበር። (ዳንኤል 12:13) ዳንኤል ከሞት ሲነሳ የሚኖረው የት ነው? “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።” (መዝሙር 37:29) ኢየሱስም ቢሆን “ገሮች ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:5) ዳንኤልም ሆነ ሌሎች ታማኝ ወንዶችና ሴቶች በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ዳግም ሕያው ይሆናሉ።

ጳውሎስ “ዓመፀኞች” በማለት ከጠራቸው ሰዎች መካከል እነማን ይገኙበታል? የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመማርና ተግባራዊ ለማድረግ አጋጣሚ ያላገኙ እዚህ ምድር ላይ ኖረው ያለፉ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይገኙበታል። ከሞት ከተነሱ በኋላ ስለ ይሖዋ * እና ስለ ኢየሱስ የመማር እንዲሁም ለተደረገላቸው ነገር አመስጋኝነታቸውን የሚገልጹበት አጋጣሚ ያገኛሉ። (ዮሐንስ 17:3) አምላክን ለማገልገል የሚመርጡ ሰዎች ሁሉ እንደ ይሖዋ እነሱም ለዘላለም ይኖራሉ።

አምላክን ለማገልገል የሚመርጡ ሁሉ የተሟላ ደስታና ጤንነት አግኝተው ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይኖራቸዋል

በምድር ላይ ምን ዓይነት ሁኔታ ይኖራል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? አምላክ “እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።” (ራእይ 21:4) በተጨማሪም “ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ።”—ኢሳይያስ 65:21

ከሞት ከሚነሱ ወዳጅ ዘመዶችህ ጋር እንዲህ ባለ ሁኔታ ስትኖር ይታይህ! ሆኖም መልስ የሚያሻው አንድ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፦ ትንሣኤ እንደሚኖር እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

^ አን.15 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።