በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጨረሻው ቀርቧል?

“መጨረሻው” ሲባል ምን ማለት ነው?

“መጨረሻው” ሲባል ምን ማለት ነው?

“መጨረሻው ቀርቧል” የሚሉትን ቃላት ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ በእጁ ይዞ መድረክ ላይ እየተወራጨ የሚደነፋ ሰባኪ ነው? ወይስ የመዓት ቀን ቀርቧል የሚል ምልክት ይዞ በመንገድ ማዕዘን ላይ የቆመ ረጅም ቀሚስ የለበሰና ወገቡን የታጠቀ ጢማም አረጋዊ ሰው? አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ዓይነቶቹን ነገሮች ሲያስቡ ጭንቀት ይለቅባቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ ጥርጣሬ ያድርባቸዋል አሊያም ያሾፋሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ “መጨረሻው ይመጣል” በማለት ይናገራል። (ማቴዎስ 24:14) ይህ ጊዜ “[የአምላክ] ታላቅ ቀን” እና “አርማጌዶን” ተብሎም ተጠርቷል። (ራእይ 16:14, 16) እውነት ነው፣ ይህን ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ የሚሰጡት ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ሰዎችን ግራ ያጋባሉ፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ ለማመን የሚከብዱና ብሩህ ተስፋ የማይሰጡ አስተሳሰቦችም ተስፋፍተዋል። ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻውን ቀን በተመለከተ የሚናገረው ነገር ግልጽ ነው፤ መጨረሻው ሲባል ምን ማለት እንደሆነና ምን ማለት እንዳልሆነ ይገልጻል። በተጨማሪም የአምላክ ቃል መጨረሻው ቅርብ መሆኑን እንድናስተውል ይረዳናል። ከሁሉ በላይ ግን መጽሐፍ ቅዱስ መጨረሻው ሲመጣ በሕይወት መትረፍ የሚቻልበትን መንገድ ያስተምረናል! እስቲ መጀመሪያ ግን መጨረሻውን በተመለከተ አንዳንድ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለይተን ለማወቅና ትርጉሙን ለመረዳት እንሞክር። ታዲያ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር “መጨረሻው” ሲባል ምን ማለት ነው?

መጨረሻው ሲባል ምን ማለት አይደለም?

 1. መጨረሻው ምድር ተቃጥላ የምትጠፋበት ታላቅ የጥፋት ቀን አይደለም።

  መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “ምድርን በመሠረቶቿ ላይ መሠረታት፤ እሷም ለዘላለም ከቦታዋ አትናወጥም” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 104:5) ይህንን ጨምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ጥቅሶች አምላክ ምድርን እንደማያጠፋት፣ እንድትጠፋም እንደማይፈቅድ ያረጋግጡልናል!—መክብብ 1:4፤ ኢሳይያስ 45:18

 2. መጨረሻው የተወሰነለት ጊዜ የሌለው በአጋጣሚ የሚከሰት ነገር አይደለም።

  መጽሐፍ ቅዱስ መጨረሻው አምላክ ጊዜ የወሰነለት ነገር እንደሆነ ይገልጻል። እንዲህ ይላል፦ “ስለዚያ ቀን ወይም ሰዓት ከአብ በቀር በሰማይ ያሉ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም። ስለዚህ የተወሰነው ጊዜ መቼ እንደሆነ ስለማታውቁ ምንጊዜም በንቃት ተከታተሉ፤ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።” (ማርቆስ 13:32, 33) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አምላክ (“አብ”) መጨረሻው እንዲጀምር የሚያደርግበትን ‘የተወሰነ ጊዜ’ ቀጥሯል።

 3. መጨረሻው በሰዎች ወይም ከጠፈር በሚወረወሩ ናዳዎች ምክንያት የሚቀሰቀስ አይደለም።

  መጨረሻው እንዲጀምር የሚያደርገው ምንድን ነው? ራእይ 19:11 “እኔም ሰማይ ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆም፣ ነጭ ፈረስ ነበር። በእሱም ላይ የተቀመጠው ‘ታማኝና እውነተኛ’ ተብሎ ይጠራል” ይላል። በመቀጠልም ቁጥር 19 እንዲህ ይላል፦ “ከዚህ በኋላ አውሬው፣ የምድር ነገሥታትና ሠራዊታቸው በፈረሱ ላይ ከተቀመጠውና ከሠራዊቱ ጋር ለመዋጋት ተሰብስበው አየሁ።” (ራእይ 19:11-21) እዚህ ጥቅስ ላይ ያሉት አብዛኞቹ አገላለጾች ምሳሌያዊ ቢሆኑም አምላክ ጠላቶቹን ለመደምሰስ የመላእክትን ሠራዊት እንደሚልክ መረዳት እንችላለን።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጨረሻው የሚናገረው ነገር ምሥራች እንጂ መጥፎ ዜና አይደለም

መጨረሻው ሲባል ምን ማለት ነው?

 1. የሰብዓዊ መንግሥታት መጨረሻ ይሆናል።

  መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይጠፋ መንግሥት ያቋቁማል። ይህም መንግሥት ለሌላ ሕዝብ አይሰጥም። እነዚህን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ ፈጽሞም ያጠፋቸዋል፤ እሱም ብቻውን ለዘላለም ይቆማል።” (ዳንኤል 2:44) ቀደም ብሎ በሦስተኛው ተራ ቁጥር ላይ እንደተገለጸው “በፈረሱ ላይ ከተቀመጠውና ከሠራዊቱ ጋር ለመዋጋት” የተሰበሰቡት “የምድር ነገሥታትና ሠራዊታቸው” ይጠፋሉ።—ራእይ 19:19

 2. የጦርነት፣ የዓመፅና የፍትሕ መዛባት መጨረሻ ይሆናል።

  አምላክ “ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ ያስወግዳል።” (መዝሙር 46:9) “በምድር ላይ የሚኖሩት ቅኖች ብቻ ናቸውና፤ በእሷም ላይ የሚቀሩት ነቀፋ የሌለባቸው ናቸው። ክፉዎች ግን ከምድር ገጽ ይጠፋሉ፤ ከዳተኞችም ከእሷ ይወገዳሉ።” (ምሳሌ 2:21, 22) “እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ።”—ራእይ 21:4, 5

 3. አምላክንም ሆነ ሰዎችን ማስደሰት ያልቻሉ ሃይማኖቶች መጨረሻ ይሆናል።

  “ነቢያቱ የሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ ካህናቱም በራሳቸው ሥልጣን በኃይል ይገዛሉ። . . . ይሁንና መጨረሻው ሲመጣ ምን ታደርጉ ይሆን?” (ኤርምያስ 5:31) “በዚያ ቀን ብዙዎች እንዲህ ይሉኛል፦ ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም? በስምህ አጋንንትን አላወጣንም? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንም?’ እኔም በዚያ ጊዜ ‘ቀድሞውንም አላውቃችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ!’ እላቸዋለሁ።”—ማቴዎስ 7:21-23

 4. የዚህን ሥርዓት አመለካከት የሚያራምዱና የሚደግፉ ሰዎች መጨረሻ ይሆናል።

  ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል፦ “እንግዲህ የሚፈረድባቸው በዚህ መሠረት ነው፦ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለነበረ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ።” (ዮሐንስ 3:19) መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ ሰው በነበረው በኖኅ ዘመን ስለተከሰተው ዓለም አቀፍ ጥፋት ይገልጻል። “በዚያ ጊዜ የነበረው ዓለም . . . ጠፍቷል። ይህም የሆነው መላዋ ምድር በውኃ በተጥለቀለቀች ጊዜ ነው። ሆኖም በዚያው ቃል አሁን ያሉት ሰማያትም ሆኑ ምድር ለእሳትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለሚጠፉበት የፍርድ ቀን ተጠብቀው ይቆያሉ።”—2 ጴጥሮስ 3:5-7

መጪው “የፍርድ ቀን” እና ‘ጥፋት’ በኖኅ ዘመን ከደረሰው “የዓለም” ጥፋት ጋር እንደተመሳሰለ ልብ በል። በኖኅ ዘመን የጠፋው የትኛው ዓለም ነበር? ፕላኔቷ ምድራችን አልጠፋችም፤ የጠፉት የአምላክ ጠላቶች ይኸውም “ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች” ነበሩ። በተመሳሳይም በመጪው የአምላክ “የፍርድ ቀን” የሚጠፉት የአምላክ ጠላቶች ለመሆን የመረጡ ሰዎች ናቸው። ይሁን እንጂ የአምላክ ወዳጆች ልክ እንደ ኖኅና እንደ ቤተሰቡ ከጥፋቱ ይተርፋሉ።—ማቴዎስ 24:37-42

አምላክ ክፉዎችን ሁሉ ካስወገደ በኋላ ይህች ምድር እንዴት ያማረች እንደምትሆን አስብ! በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጨረሻው የሚናገረው ነገር ምሥራች እንጂ መጥፎ ዜና አይደለም። ያም ሆኖ ‘መጽሐፍ ቅዱስ መጨረሻው መቼ እንደሚመጣ ይነግረናል? በቅርቡ ይመጣ ይሆን? ከመጨረሻው ቀን በሕይወት መትረፍ የምችለውስ እንዴት ነው?’ እያልክ ታስብ ይሆናል።