ሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስን መማር ትፈልጋለህ?
የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት—ለሁሉም ሰው
የይሖዋ ምሥክሮች፣ በሚያከናውኑት የስብከት ሥራ በደንብ ይታወቃሉ። ይሁን እንጂ አንተ፣ በመላው ዓለም ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ የምናስተምርበት ፕሮግራም እንዳለን ታውቃለህ?
በ2014 በ240 አገሮች የሚኖሩ ከ8,000,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች በየወሩ 9,500,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ አስተምረዋል። * መጽሐፍ ቅዱስን የምናስተምራቸው ሰዎች ብዛት፣ 140 ገደማ የሚሆኑ አገሮች በተናጠል ካላቸው የሕዝብ ብዛት ይበልጣል!
የይሖዋ ምሥክሮች ይህን የማስተማር ሥራ ለማከናወን በየዓመቱ ወደ አንድ ቢሊዮን ተኩል የሚጠጉ መጽሐፍ ቅዱሶችን፣ መጻሕፍትን፣ መጽሔቶችንና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ጽሑፎችን 700 በሚያህሉ ቋንቋዎች ያዘጋጃሉ! ይህ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የሕትመት ሥራ ሰዎች በሚፈልጉት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ያስችላቸዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራማችንን በተመለከተ ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቱ የሚሰጥበት መንገድ ምን ይመስላል?
የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት ከጉዳዩ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንመረምራለን። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተሉት ላሉ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፦ አምላክ ማን ነው? ምን ዓይነት ባሕርያት አሉት? አምላክ ስም አለው? የሚኖረው የት ነው? ከእሱ ጋር መቀራረብ እንችላለን? በእርግጥ፣ አስቸጋሪ የሚሆነው የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚገኝበትን ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ፈልጎ ማግኘት ነው።
ሰዎች ለጥያቄዎቻቸው በቀላሉ መልስ እንዲያገኙ ለመርዳት አብዛኛውን ጊዜ የምንጠቀመው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን ባለ 224 ገጽ መጽሐፍ * ነው። ይህ መጽሐፍ የተዘጋጀበት ዋነኛ ዓላማ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ትምህርቶች መረዳት እንዲችሉ ማገዝ ነው። ይህ መጽሐፍ ስለ አምላክ፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በሰው ልጆች ላይ ስለሚደርሰው መከራ፣ ስለ ትንሣኤ፣ ስለ ጸሎትና ስለ ሌሎች ብዙ ርዕሰ ጉዳዮች የሚገልጹ ትምህርቶችን አካትቶ የያዘ ነው።
ትምህርቱ የሚሰጠው መቼና የት ነው?
ለአንተ አመቺ የሆነውን ጊዜና ቦታ መምረጥ ትችላለህ።
አንድ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?
ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር በየሳምንቱ ወደ አንድ ሰዓት ገደማ ይመድባሉ። ነገር ግን ትምህርቱ የሚወስደው ጊዜ እንደ ሁኔታው ሊለዋወጥ ይችላል። ፕሮግራሙን ለአንተ እንደሚስማማ ማስተካከል እንችላለን። አንዳንዶች በየሳምንቱ ለ10 ወይም ለ15 ደቂቃ ብቻ ይማራሉ።
ትምህርቱ ምን ያህል ያስከፍላል?
ትምህርቱንም ሆነ የመማሪያ ጽሑፎቹን የምንሰጠው በነፃ ነው። ይህም ኢየሱስ “በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ከሰጠው መመሪያ ጋር የሚስማማ ነው።—ማቴዎስ 10:8
ትምህርቱን ለመጨረስ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል?
ይህ በአንተ ላይ የተመካ ነው። ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተሰኘው መጽሐፍ 19 ትምህርቶችን ይዟል። ከመጽሐፉ ውስጥ አንተ የምትፈልጋቸውን ወይም ሁሉንም ትምህርቶች ለአንተ በሚስማማህ ፍጥነት መማር ትችላለህ።
ትምህርቱን ከወሰድኩ በኋላ የይሖዋ ምሥክር መሆን ይጠበቅብኛል?
አይጠበቅብህም። እያንዳንዱ ሰው የፈለገውን ለማመን ያለውን መብት እናከብራለን። ይሁን እንጂ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ያገኙ ሰዎች ባወቁት ነገር ላይ ተመሥርተው ውሳኔ ሊያደርጉ ይችላሉ።
ተጨማሪ መረጃ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?
jw.org የተሰኘው ድረ ገጽ የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያምኑባቸው ነገሮችና ስለሚያከናውኑት ሥራ ትክክለኛ መረጃ ያቀርባል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንዲሰጠኝ መጠየቅ የምችለው እንዴት ነው?
-
www.jw.org/am በተሰኘው ድረ ገጽ ላይ የሚገኘውን ቅጽ ሙላ።
-
በአካባቢህ ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝ። ▪