መዳን የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
“ከሴት የተወለደ ሰው፣ ዘመኑ አጭርና በመከራ የተሞላ ነው፤ እንደ አበባ ይፈካል፤ ይረግፋልም፤ እንደ ጥላ ይፈጥናል፤ አይጸናምም።”—ኢዮብ 14:1, 2
ከጥንት ጀምሮ ሰዎች፣ ወጣትና ጤነኛ ሆነው ለዘላለም መኖር ቢችሉ ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን ሲያልሙ ኖረዋል። የሚያሳዝነው ግን ሁላችንም መሞታችን አይቀርም። ኢዮብ ከሦስት ሺህ ከሚበልጡ ዓመታት በፊት የተናገረው ከላይ የተጠቀሰው ሐሳብ ዛሬም እውነት ነው።
ፍጻሜ ለሌለው ጊዜ መኖር በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ ሰዎች አጥብቀው የሚፈልጉት ነገር ነው። አምላክ ለዘላለም የመኖር ምኞትን እንዲሁም ስለዚህ ዓይነቱ ሕይወት የማሰብ ችሎታን በልባችን ውስጥ እንዳስቀመጠ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (መክብብ 3:11) ታዲያ የሰው ልጆችን የሚወደው አምላክ፣ ልናገኘው የማንችለውን ምኞት በውስጣችን ያስቀምጣል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ይመስልሃል? ‘አይመስለኝም’ ብለህ ከመለስክ ትክክል ነህ። የአምላክ ቃል ሞትን ጠላት ብሎ ይጠራዋል፤ እንዲሁም ወደፊት ሞት ‘እንደሚደመሰስ’ ተስፋ ይሰጣል።—1 ቆሮንቶስ 15:26
ሞት ጠላት መሆኑ የሚያጠራጥር ነገር አይደለም። ትክክለኛ አስተሳሰብ ያለው ሰው መሞት እንደማይፈልግ የታወቀ ነው። አንድ አደገኛ ሁኔታ ሲያጋጥመን ወዲያውኑ ለመደበቅ ወይም ሸሽተን ለማምለጥ እንሞክራለን። ስንታመም ጤንነታችን የሚመለስበትን መንገድ እናፈላልጋለን። ሕይወታችንን አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ነገሮች ለመራቅ የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን።
ታዲያ ይህ የረጅም ዘመን ጠላታችን ይደመሰሳል ብለን ለማመን የሚያስችል ምክንያት አለ? አዎ፣ አለ። ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክ ሰዎችን የፈጠረው ጥቂት ዓመታት ኖረው እንዲሞቱ አይደለም። አምላክ ሰዎችን ሲፈጥር ሞት የእሱ ዓላማ ክፍል አልነበረም። የይሖዋ ዓላማ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነው፤ ደግሞም እሱ ዓላማውን ከዳር ማድረስ የሚችል አምላክ ነው።—ኢሳይያስ 55:11
ታዲያ ሞት የሚወገደው እንዴት ነው? ከጥንት ዘመን ጀምሮ ሰዎች ለሞት መፍትሔ ለማግኘት እልህ አስጨራሽ ትግል ሲያደርጉ ኖረዋል፤ ሆኖም ጥረታቸው መና ቀርቷል። በዘመናችንም ቢሆን ሰዎች እንዲህ ዓይነት ጥረት ማድረጋቸውን አላቆሙም። የሳይንስ ሊቃውንት አንዳንድ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ክትባቶችንና መድኃኒቶችን ሠርተዋል። ሕይወት ባላቸው ነገሮች ውስጥ ስለሚገኘው የጄኔቲክ አሠራር ምርምር አድርገዋል። እንዲሁም በብዙ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ከመቶ ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በአማካይ ረዘም ያለ ዕድሜ እየኖሩ ነው። ይህም ሁሉ ሆኖ ግን ሞትን ድል መንሳት አልተቻለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ሁሉም . . . ተመልሰው ወደ ዐፈር ይሄዳሉ።”—መክብብ 3:20
ደስ የሚለው ነገር፣ ለዘመናት የኖረው የዚህ ችግር መፍትሔ የሚገኘው በሰዎች ጥበብ አይደለም። ይሖዋ አምላክ ከሞት የምንድንበትን መንገድ ያዘጋጀልን ሲሆን በዚህ ዝግጅት ትልቁን ሚና የሚጫወተው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።