በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

ክርስቲያኖች በዓለ ትንሣኤን ሊያከብሩ ይገባል?

ክርስቲያኖች በዓለ ትንሣኤን ሊያከብሩ ይገባል?

ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ስለ በዓለ ትንሣኤ ሲናገር “የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የሚከበርበት የክርስቲያኖች ዋነኛ በዓል” እንደሆነ ገልጿል። ይሁንና ክርስቲያኖች ይህን በዓል ሊያከብሩ ይገባል?

የአንድን ጥንታዊ ቅርስ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ዕቃውን በጥንቃቄ መመርመር አስፈላጊ ነው። በተመሳሳይም በዓለ ትንሣኤ በክርስቲያኖች ሊከበር የሚገባው በዓል መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ከዚህ በዓል ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ዝርዝር ጉዳዮችን መመርመር ይኖርብናል።

በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲያከብሩ ያዘዘው ትንሣኤውን ሳይሆን ሞቱን ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን በዓል ‘የጌታ ራት’ በማለት ጠርቶታል።—1 ቆሮንቶስ 11:20፤ ሉቃስ 22:19, 20

በተጨማሪም ኢንሳይክሎፒዲያው እንደሚናገረው በበዓለ ትንሣኤ ላይ የሚከናወኑት አብዛኞቹ ሥነ ሥርዓቶች ከኢየሱስ ትንሣኤ ጋር “ምንም የሚያገናኛቸው ነገር” የለም፤ ከዚህ ይልቅ “ሲወርድ ሲዋረድ ከመጡ ባሕሎች የተወረሱ ናቸው።” ለምሳሌ ያህል፣ ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን በብዙ የዓለም ክፍሎች ውስጥ ተቀባይነት ስላገኙት የበዓለ ትንሣኤ ተምሳሌቶች ይኸውም ስለ እንቁላልና ስለ ጥንቸል ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እንቁላሉ፣ እንደ ሞት ከሚቆጠረው . . . የእንቁላል ቅርፊት ሰብሮ ለሚወጣው አዲስ ሕይወት ተምሳሌት ሆኖ ያገለግላል።” አክሎም “ጥንቸል ትታወቅ የነበረው ከፍተኛ የመራባት ችሎታ ያላት ፍጥረት በመሆኗ ነው፤ ስለዚህ ለጸደይ ወቅት መቃረብ ምሳሌ ሆና ታገለግል ነበር” ብሏል።

የመካከለኛው ዘመን ሥነ ጽሑፍ ፕሮፌሰር የሆኑት ፊሊፕ ዎልተር፣ እንዲህ ዓይነቶቹ ልማዶች የበዓለ ትንሣኤ ክፍል ሊሆኑ የቻሉት እንዴት እንደሆነ ገልጸዋል። ፕሮፌሰሩ እንደገለጹት ከሆነ “አረማዊ ሃይማኖቶችን ወደ ክርስትና ለመለወጥ” ሲባል “እንደ ሞት በሚቆጠረው የክረምት ወቅትና እንደ ሕይወት በሚቆጠረው የጸደይ ወቅት መካከል የሚኖረውን ሽግግር” ምክንያት በማድረግ ይከበር የነበረው የአረማውያን በዓል ከኢየሱስ ትንሣኤ ጋር እንዲዛመድ ተደረገ። አክለውም፣ ይህ በዓል በአረማውያኑ ቀን መቁጠሪያ ላይ “የክርስትና በዓላት” እንዲገቡ በማድረግ ረገድ ትልቅ ቦታ ያለው እርምጃ እንደነበረው ገልጸዋል፤ ይህም የአረማውያንን ሃይማኖት የሚከተሉ ብዙ ሰዎች እምነታቸውን እንዲቀይሩ አድርጓል።

በዚህ መንገድ ሰዎችን “ወደ ክርስትና የመለወጥ” ሂደት የተከናወነው ሐዋርያት በሕይወት በነበሩበት ጊዜ አይደለም፤ ምክንያቱም ሐዋርያት እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት ‘አግደውት’ ነበር። (2 ተሰሎንቄ 2:7) ሐዋርያው ጳውሎስ እሱ ‘ከሄደ በኋላ’ “ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች [እንደሚነሱ]” አስጠንቅቆ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30) እንዲሁም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ አንዳንድ ሰዎች ክርስቲያኖችን ለማሳሳት ይሞክሩ እንደነበር ሐዋርያው ዮሐንስ ጽፏል። (1 ዮሐንስ 2:18, 26) ውሎ አድሮ የአረማውያን የሃይማኖት ልማዶች ወደ ክርስትና ሰርገው የሚገቡበት መንገድ ተመቻቸ።

“ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ።”—2 ቆሮንቶስ 6:14

ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ የበዓለ ትንሣኤ ልማዶች ምንም ክፋት እንደሌላቸው የሚሰማቸው ሰዎች አሉ፤ ምክንያቱም ይህ ሁኔታ “አረማውያን” የኢየሱስ ትንሣኤ ስላለው ትርጉም የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል ብለው ያስባሉ። ሆኖም ጳውሎስ በዚህ ሐሳብ ፈጽሞ እንደማይስማማ የታወቀ ነው። ጳውሎስ በሮማ ግዛት ውስጥ ሲዘዋወር ብዙ የአረማውያን ልማዶችን የተመለከተ ቢሆንም ሰዎች ስለ ኢየሱስ የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኙ በማሰብ እነዚህን ልማዶች ተቀብሏቸው አያውቅም። ከዚህ በተቃራኒ ክርስቲያኖችን እንዲህ በማለት አስጠንቅቋቸዋል፦ “ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ። ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ኅብረት አለው? ወይም ብርሃን ከጨለማ ጋር ምን ያገናኘዋል? ‘ስለዚህ ከመካከላቸው ውጡና ራሳችሁን ለዩ’ ይላል ይሖዋ፤ ‘ርኩስ የሆነውንም ነገር መንካት አቁሙ።’”—2 ቆሮንቶስ 6:14, 17

ታዲያ ከበዓለ ትንሣኤ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ልማዶችን በአጭሩ መመርመራችን ምን መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ያደርገናል? ‘ክርስቲያኖች በዓለ ትንሣኤን ሊያከብሩ አይገባም’ የሚል መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ያደርገናል።