ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ሐዋርያው ጳውሎስ የሮም ዜግነት ያለው መሆኑ ምን ጥቅም አስገኝቶለታል?

ጳውሎስ “ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ!” በማለት ተናግሯል

የሮም ዜግነት ያለው አንድ ሰው በሮም ግዛት ውስጥ የትም ቦታ ቢሄድ ዜግነቱ አንዳንድ መብቶችና ጥቅሞች ያስገኝለት ነበር። አንድ የሮም ዜጋ የሚጠየቀው በሚኖርበት ከተማ ሕግ ሳይሆን በሮም ሕግ ነበር። ግለሰቡ ቢከሰስ በአካባቢው ሕግ መሠረት ምርመራ እንዲካሄድበት ሊስማማ ቢችልም በሮም ችሎት ፊት ቃሉን ለመስጠት ያለው መብት ይከበርለት ነበር። የሞት ቅጣት ቢበየንበት ደግሞ ለንጉሠ ነገሥቱ ይግባኝ የማለት መብት ነበረው።

እንደዚህ ያሉትን መብቶች መሠረት በማድረግ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የነበረ ሲሰሮ የሚባል አንድ ሮማዊ የፖለቲካ ሰው “አንድን የሮም ዜጋ ማሰር ወንጀል ነው፤ መግረፍ ደግሞ ክፋት ነው” ብሎ ነበር፤ አክሎም በአንድ የሮም ዜጋ ላይ የሞት ቅጣት ማስፈጸም ወላጅን ወይም የቅርብ ዘመድን ከመግደል እንደማይተናነስ ተናግሯል።

ሐዋርያው ጳውሎስ በመላው የሮም ግዛት ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ሰብኳል። የሮም ዜግነቱ ያስገኘለትን መብት የተጠቀመባቸውን ሦስት አጋጣሚዎች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እናነባለን፦ (1) የፊልጵስዩስ አስተዳዳሪዎች እሱን በመግረፋቸው የመብት ጥሰት እንደፈጸሙበት ነግሯቸዋል። (2) በኢየሩሳሌም ሊደርስበት ከነበረው ግርፋት ለመዳን ሲል የሮም ዜጋ እንደሆነ ገልጿል። (3) የፍርድ ጉዳዩን ቄሳር ማለትም የሮም ንጉሠ ነገሥት እንዲያይለት ይግባኝ ብሏል።—የሐዋርያት ሥራ 16:37-39፤ 22:25-28፤ 25:10-12

በጥንት ዘመን እረኞች ደሞዝ የሚከፈላቸው እንዴት ነበር?

የበጎችና የፍየሎች ሽያጭ የተመዘገበበት በኪዩኒፎርም የተጻፈ ውል፣ 2050 ዓ.ዓ. ገደማ

ያዕቆብ የአጎቱን የላባን መንጎች ለ20 ዓመታት ጠብቋል። ያዕቆብ ለመጀመሪያዎቹ 14 ዓመታት ለሰጠው አገልግሎት ላባ ሁለት ልጆቹን የዳረለት ሲሆን ለተቀሩት 6 ዓመታት ላከናወነው ሥራ ደግሞ ክፍያውን ያገኘው ከመንጎቹ ነው። (ዘፍጥረት 30:25-33) ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው የተሰኘ መጽሔት እንደሚገልጸው “በላባና በያዕቆብ መካከል የተደረጉትን የመሰሉ የእረኝነት ውሎች በጥንት ዘመን በነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችና አንባቢዎች ዘንድ በጣም የሚታወቁ ልማዶች ናቸው ሊባል ይችላል።”

በአሁኗ ኢራቅ ውስጥ በሚገኙት በኑዚ፣ በላርሳ እና በሌሎች ቦታዎች በተደረጉ ቁፋሮዎች ከዚህ ጋር የሚመሳሰሉ ጥንታዊ ውሎች ተገኝተዋል። አብዛኞቹ ውሎች የሚቆዩት ለአንድ ዓመት ይኸውም በጎች ከሚሸለቱበት ጊዜ አንስቶ በቀጣዩ ዓመት እስከሚሸለቱበት ጊዜ ድረስ ነው። እረኞቹ ለመንከባከብ የሚዋዋሏቸው እንስሳት ብዛት የሚጻፍ ከመሆኑም በላይ ዕድሜያቸውና ፆታቸውም ይመዘገባል። ከአንድ ዓመት በኋላ የመንጋው ባለቤት አስቀድሞ በተዋዋሉት መሠረት ለእሱ የሚደርሰውን ሱፍ፣ የወተት ተዋጽኦዎች፣ ግልገሎች፣ ወዘተ ይቀበላል። ከዚህ የተረፈውን በሙሉ ደግሞ እረኛው ይወስዳል።

በመንጋው ውስጥ የሚገኙት እንስሳት ጭማሪ ለእረኛው በተሰጡት እንስት በጎች ብዛት ላይ የተመካ ነው። በጥቅሉ ሲታይ 100 እንስት በጎች 80 ጠቦቶችን እንዲያፈሩ ይጠበቅ ነበር። የእንስሳቱ ብዛት ከሚጠበቀው ካነሰ እረኛው የጎደለውን እንዲያካክስ ይጠበቅበት ነበር። ስለዚህ እረኛው በአደራ የተሰጡትን እንስሳት በጥሩ ሁኔታ ለመንከባከብ የሚያነሳሳ ትልቅ ምክንያት ነበረው ማለት ነው።