በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ባሎች—ቤታችሁ ስጋት የሌለበት ቦታ እንዲሆን አድርጉ

ባሎች—ቤታችሁ ስጋት የሌለበት ቦታ እንዲሆን አድርጉ

ንድ ባል፣ ሚስቱ ያለ ስጋት እንድትኖር ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? ብዙ ሰዎች ያደጉት፣ የባል ዋና ኃላፊነት ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር ማቅረብ እንደሆነ በሚታመንበት ማኅበረሰብ ውስጥ ነው። ይሁን እንጂ በገንዘብ ረገድ የሚፈልጉት ነገር ሁሉ ያላቸው አንዳንድ ሚስቶች ባሎቻቸው ስሜታዊ ፍላጎታቸውን እንደማያሟሉላቸው እና ስሜታቸውን እንደማይረዱላቸው ይሰማቸዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ባሎቻቸውን በጣም ይፈሯቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሮዛ የምትባል አንዲት ስፔናዊት ሴት እንደገለጸችው ባሏ ‘የውጭ አልጋ፣ የቤት ቀጋ’ እንደሚባለው ዓይነት ሰው ነው። በናይጄሪያ የምትኖረው ጆይ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ከባለቤቴ ጋር የማንስማማበት ነገር በሚኖርበት ወቅት ‘ባልሽ እኮ ነኝ፤ ያልኩሽን ሁሉ ማድረግ አለብሽ’ ይለኝ ነበር።”

ታዲያ አንድ ባል ኃላፊነቱን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ መወጣት የሚችለው እንዴት ነው? ቤታቸው ሚስቱ ያለ ስጋት የምትኖርበት ‘የእረፍት ቦታ’ እንዲሆን ማድረግ የሚችለውስ እንዴት ነው?ሩት 1:9

ባል ስላለው ኃላፊነት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አምላክ፣ ባልንም ሆነ ሚስትን እኩል አድርጎ የሚመለከታቸው ቢሆንም ሁለቱም በትዳር ውስጥ የየራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ሮም 7:2 አንዲት ያገባች ሴት “ከባሏ ሕግ” በታች እንደሆነች ይገልጻል። ብዙ ተቋሞች የድርጅቱን ሥራ በበላይነት የሚቆጣጠርላቸው ኃላፊ እንደሚሾሙ ሁሉ አምላክም ባልን የሚስት ራስ አድርጎ ሾሞታል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ባሎች ቤተሰባቸውን የመምራት ኃላፊነት አለባቸው።

ታዲያ ባሎች ከሆናችሁ አምላክ የሰጣችሁን ኃላፊነት እንዴት ልትጠቀሙበት ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስ “ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደ . . . ሁሉ እናንተም ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ” ይላል። (ኤፌሶን 5:25) አዎን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አግብቶ ባያውቅም እንኳ የእሱን ምሳሌ መከተላችሁ ጥሩ ባል እንድትሆኑ ሊረዳችሁ ይችላል። እንዲህ የምንለው ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ለባሎች ግሩም ምሳሌ የሚሆነው የኢየሱስ ሕይወት

ኢየሱስ ሌሎች እረፍት እንዲያገኙና ሸክማቸው እንዲቀልላቸው ይጥር ነበር። ኢየሱስ ለተጨቆኑና ችግሮቻቸው ለከበዷቸው ሰዎች “ወደ እኔ ኑ፣ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 11:28, 29) ኢየሱስ ብዙውን ጊዜ ሥቃያቸውን ያስታግሥላቸው፣ እንዲሁም መንፈሳዊ እርዳታ በመስጠት እፎይታ እንዲያገኙ ያደርግ ነበር። ከዚህ አንጻር ብዙዎች ኢየሱስ ሸክማቸውን እንደሚያቀልላቸው በማመን ወደ እሱ ለመቅረብ መፈለጋቸው አያስደንቅም!

 ባሎች ኢየሱስን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው? ሚስትህን ማገዝ የምትችልበትን መንገድ ፈልግ። አንዳንድ ሚስቶች “ባሌ የሚመለከተኝ እንደ ቤት ሠራተኛው አድርጎ ነበር” በማለት በምሬት እንደተናገረችው እንደ ሮዛ ይሰማቸዋል። በአንጻሩ ደግሞ ጥሩ ትዳር ያለው ክዌኩ የሚባል አንድ ባል እንዲህ ብሏል፦ “ሚስቴን ምን ላግዛት እንደምችል እጠይቃታለሁ። ባለቤቴን ስለምወዳት የቤት ውስጥ ሥራዎችን የማከናውነው በራሴ ተነሳስቼ ነው።”

ኢየሱስ አሳቢና ርኅሩኅ ነበር። ለ12 ዓመታት ከባድ በሆነ የጤና ችግር ስትሠቃይ የኖረች አንዲት ምስኪን ሴት ነበረች። ኢየሱስ ሰዎችን በተአምር እንደሚፈውስ ስትሰማ “ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ” ብላ አሰበች። ደግሞም አልተሳሳተችም! ወደ ኢየሱስ ቀርባ የልብሱን ጫፍ ስትነካ ወዲያውኑ ተፈወሰች። በስፍራው የነበሩት አንዳንድ ሰዎች ይህች ሴት አጉል ድፍረት እንዳሳየች ተሰምቷቸው ሊሆን ቢችልም ኢየሱስ ግን ችግሯን ተረድቶላታል። * ስለዚህ በደግነት ‘ልጄ ሆይ፣ ከሚያሠቃይ ሕመምሽ እረፊ’ አላት። ኢየሱስ ሴትየዋን አላሸማቀቃትም ወይም አልገሠጻትም፤ እንዲያውም  ሥቃይዋን እንደተረዳ አሳይቷል። ይህ ታሪክ፣ ኢየሱስ ምን ያህል ርኅሩኅ ሰው እንደነበረ ያሳያል።—ማርቆስ 5:25-34

ባሎች ኢየሱስን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው? ሚስትህ ስሜቷ ጥሩ በማይሆንበት ጊዜ ከወትሮው የተለየ አሳቢነት አሳያት እንዲሁም በትዕግሥት ያዛት። ራስህን በእሷ ቦታ ለማስቀመጥና ስሜቷን ለመረዳት ጥረት አድርግ። ለምሳሌ ያህል፣ ሪካርዶ እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴ በቀላሉ እየተበሳጨች እንደሆነ ካስተዋልኩ ይበልጥ ሊያበሳጯት የሚችሉ ነገሮችን ላለመናገር የተለየ ጥረት አደርጋለሁ።”

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይነጋገር ነበር። ኢየሱስ ወዳጆቹን ስለተለያዩ ነገሮች ያጫውታቸው ነበር። ‘ከአባቴ የሰማሁትን ነገር ሁሉ አሳውቄያችኋለሁ’ ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 15:15) ኢየሱስ ለማሰላሰልና ለመጸለይ ሲል ብቻውን መሆን የሚፈልግበት ጊዜ እንደነበረ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ የውስጥ ስሜቱን አውጥቶ ለደቀ መዛሙርቱ ይነግራቸው ነበር። እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ከመገደሉ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ኢየሱስ ‘እጅግ እንዳዘነ’ ለደቀ መዛሙርቱ በግልጽ ነግሯቸው ነበር። (ማቴዎስ 26:38) ደቀ መዛሙርቱ የሚያበሳጭ ነገር በሚያደርጉበት ጊዜም እንኳ አኩርፏቸው አያውቅም።—ማቴዎስ 26:40, 41

አንድ ሰው ኢየሱስ በተወው ምሳሌ ላይ ማሰላሰሉ ጥሩ ባልና አባት እንዲሆን ይረዳዋል

ባሎች ኢየሱስን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው? ስሜትህንም ሆነ በልብህ ውስጥ ያለውን ነገር ለሚስትህ አካፍላት። አንዲት ሴት፣ ባሏ ከሌሎች ሰዎች ጋር በነፃነት ቢነጋገርም ቤት ውስጥ ሲሆን ዝም እንደሚል ታማርር ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ አና የተባለች ሴት ባሏ የውስጡን አውጥቶ ሲነግራት ምን እንደሚሰማት ስትገልጽ “በጣም እንደሚወደኝና ከእሱ ጋር ይበልጥ እንደተቀራረብኩ ይሰማኛል” ብላለች።

ሚስትህን ለመቅጣት ብለህ አታኩርፋት። አንዲት ሴት እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ባለቤቴ ካበሳጨሁት ለቀናት ያህል ያኮርፈኛል። ይህም የጥፋተኝነት ስሜትና እንደተጠላሁ እንዲሰማኝ ያደርጋል።” ኤድዊን የተባለ አንድ ሰው ግን ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ ለመከተል ጥረት ያደርጋል። “ስበሳጭ ወዲያውኑ መልስ አልሰጥም፤ ይሁንና ችግሩን በግልጽ ተነጋግረን መፍታት የምንችልበትን ትክክለኛ ጊዜ እመርጣለሁ” ብሏል።

በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ጆይ፣ ባሏ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመረ ወዲህ ባሕርይው እንደተሻሻለ ተመልክታለች። ጆይ “ባለቤቴ ባሕርይው የተሻሻለ ሲሆን የኢየሱስን ምሳሌ በመኮረጅ ይበልጥ አፍቃሪ ባል ለመሆን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው” ብላለች። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ባለትዳሮች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸው ጥቅም አስገኝቶላቸዋል። አንተስ እንዲህ ዓይነት ጥቅም ማግኘት ትፈልጋለህ? አንድ የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ እንዲያስተምርህ መጠየቅ ትችላለህ።

^ አን.10 በሙሴ ሕግ መሠረት ሴትዮዋ የነበረችበት ሁኔታ እንደረከሰች ያስቆጥራት ነበር፤ በመሆኑም እሷ የነካችው ሰው ሁሉ ይረክስ ነበር።—ዘሌዋውያን 15:19, 25