በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የአምላክ መንግሥት ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?

የአምላክ መንግሥት—ኢየሱስ ትልቅ ቦታ የሰጠው ለምንድን ነው?

የአምላክ መንግሥት—ኢየሱስ ትልቅ ቦታ የሰጠው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ስለ ብዙ ነገሮች አስተምሯል። ለምሳሌ ያህል እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው፣ አምላክን ማስደሰት የሚችሉት እንዴት እንደሆነና እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተከታዮቹን አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:5-13፤ ማርቆስ 12:17፤ ሉቃስ 11:28) ይሁን እንጂ ከሌሎች ነገሮች ሁሉ ይበልጥ ይናገር የነበረው ስለ አምላክ መንግሥት ነው፤ ስለዚህ ጉዳይ መናገር ከሁሉ የበለጠ ያስደስተው ነበር።—ሉቃስ 6:45

ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው የኢየሱስ ሕይወት በዋነኝነት ያተኮረው ‘የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበክና በማወጅ’ ላይ ነበር። (ሉቃስ 8:1) ሰዎችን ስለ አምላክ መንግሥት ለማስተማር ሲል በመላው የእስራኤል ምድር በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን በእግር በመጓዝ ብዙ ለፍቷል። የኢየሱስን አገልግሎት በሚዘግቡት አራት ወንጌሎች ውስጥ የአምላክ መንግሥት ከ100 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል። ከእነዚህ መካከል አብዛኛውን የተናገረው ኢየሱስ ነው፤ ያውም ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ከተናገራቸው ሐሳቦች መካከል በወንጌሎች ላይ የሰፈረው የተወሰነው ብቻ ነው!—ዮሐንስ 21:25

ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ለዚህ መንግሥት ትልቅ ቦታ የሰጠው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ አምላክ እሱን የዚህ መንግሥት መሪ አድርጎ እንደመረጠው ያውቅ ነበር። (ኢሳይያስ 9:6፤ ሉቃስ 22:28-30) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ትኩረት ያደረገው በሚያገኘው ሥልጣን ወይም ክብር ላይ አልነበረም። (ማቴዎስ 11:29፤ ማርቆስ 10:17, 18) ኢየሱስ ስለዚህ መንግሥት ለማወጅ የተነሳሳው ለራሱ ጥቅም አስቦ ሳይሆን ሌሎች ጠንካራ ምክንያቶች ስላሉት ነው። ኢየሱስ በፊትም ሆነ አሁን፣ * ትኩረቱን በአምላክ መንግሥት ላይ እንዲያደርግ ያነሳሳው ዋነኛ ምክንያት ይህ መንግሥት እሱ ለሚወዳቸው አካላት ማለትም በሰማይ ላለው አባቱና ለታማኝ ተከታዮቹ የሚያስገኘው ጥቅም ነው።

መንግሥቱ ለኢየሱስ አባት የሚያስገኘው ጥቅም

ኢየሱስ በሰማይ ላለው አባቱ ጥልቅ ፍቅር አለው። (ምሳሌ 8:30 የ1954 ትርጉም፤ ዮሐንስ 14:31) ኢየሱስ እንደ ፍቅር፣ ርኅራኄና ፍትሕ ያሉትን የአባቱን ተወዳጅ ባሕርያት ያደንቃል። (ዘዳግም 32:4፤ ኢሳይያስ 49:15፤ 1 ዮሐንስ 4:8) በመሆኑም ‘አምላክ በሰዎች ላይ ለሚደርሰው መከራ ደንታ የለውም’ ወይም ‘አምላክ መከራ እንዲደርስብን ይፈልጋል’ እንደሚሉት ያሉ ስለ አባቱ የሚነገሩ ውሸቶችን መስማት እንደሚያሳዝነው ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ፣ የአምላክ መንግሥት ጊዜው ሲደርስ በአባቱ ስም ላይ የተከመረውን ነቀፋ እንደሚያስወግድ ያውቅ ነበር፤ “የመንግሥቱን ምሥራች” የማወጅ ከፍተኛ ፍላጎት እንዲኖረው ያደረገው አንዱ ምክንያት ይህ ነው። (ማቴዎስ 4:23፤ 6:9, 10) ታዲያ የአምላክ መንግሥት በአምላክ ስም ላይ የተከመረውን ነቀፋ የሚያስወግደው እንዴት ነው?

ይሖዋ በዚህ መንግሥት አማካኝነት ለሰብዓዊው ቤተሰብ ጥቅም የሚያስገኝ ሥር ነቀል እርምጃ ይወስዳል። እንዲሁም የታማኝ ሰዎችን ‘እንባ ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል።’ ይሖዋ ለእንባ መንስኤ የሚሆኑ ነገሮችን በሙሉ ያስወግዳል፤ “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም” የሚለው ተስፋ እንዲፈጸም ያደርጋል። (ራእይ 21:3, 4) አምላክ በዚህ መንግሥት አማካኝነት በሰዎች ላይ የሚደርሰውን መከራና ሥቃይ በሙሉ ያስቀራል። *

 ከዚህ አንጻር ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ ለሰዎች ለመንገር ይጓጓ የነበረ መሆኑ አያስደንቅም! ይህ መንግሥት አባቱ ምን ያህል ኃያልና ርኅሩኅ መሆኑን እንደሚያሳይ ያውቅ ነበር። (ያዕቆብ 5:11) በተጨማሪም ኢየሱስ፣ መንግሥቱ ከአባቱ በተጨማሪ ሌሎችን ማለትም ታማኝ የሆኑ ሰዎችን እንደሚጠቅም ያውቅ ነበር፤ ኢየሱስ ታማኝ ለሆኑ ሰዎችም ፍቅር አለው።

መንግሥቱ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች የሚያስገኘው ጥቅም

ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከረጅም ጊዜ በፊት አንስቶ በሰማይ ከአባቱ ጋር ይኖር ነበር። አብ ሁሉንም ነገር የፈጠረው በልጁ ተጠቅሞ ነው፤ ከተፈጠሩት ነገሮች መካከል ስፍር ቁጥር የሌላቸው ከዋክብትና የከዋክብት ረጨቶች እንዲሁም ሕያዋን ፍጥረታት የሚርመሰመሱባት ውቧ ፕላኔታችን ይገኙበታል። (ቆላስይስ 1:15, 16) ይሁንና ኢየሱስ ከእነዚህ ሁሉ አብልጦ የሚወደው ‘የሰው ልጆችን’ ነበር።—ምሳሌ 8:31

ኢየሱስ ለሰዎች የነበረው ፍቅር አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት በግልጽ ታይቷል። ገና አገልግሎቱን ሲጀምር እንደገለጸው ወደ ምድር የመጣው ለድሆች ‘ምሥራች ለማወጅ’ ነው። (ሉቃስ 4:18) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሰዎችን እንደሚወድ በመናገር ብቻ አልተወሰነም። ለሰዎች ያለውን ፍቅር በተደጋጋሚ በተግባር አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ እሱን ለመስማት ብዙ ሰዎች ተሰብስበው ባየ ጊዜ “በጣም አዘነላቸው፤ ሕመምተኞቻቸውንም ፈወሰ።” (ማቴዎስ 14:14) አስከፊ በሽታ የያዘው አንድ ሰው ወደ እሱ ቀርቦ “ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት እምነቱን ሲገልጽለት ኢየሱስ በርኅራኄ “እፈልጋለሁ፣ ንጻ” አለው። ኢየሱስ በፍቅር ተገፋፍቶ ይህን ሰው ፈውሶታል። (ሉቃስ 5:12, 13) ኢየሱስ ወዳጁ የነበረችው ማርያም ወንድሟ አልዓዛር ሞቶ ስታለቅስ ባያት ጊዜ “መንፈሱ ታወከ፤ ውስጡም ተረበሸ።” እንዲሁም “እንባውን አፈሰሰ።” (ዮሐንስ 11:32-36) ከዚያም ኢየሱስ እጅግ አስገራሚ ነገር አደረገ፤ ይኸውም ከሞተ አራት ቀን የሆነውን አልዓዛርን ከሞት አስነሳው።—ዮሐንስ 11:38-44

እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ በዚያን ጊዜ የሰዎችን ችግር ለማቃለል ያደረገው ነገር ጊዜያዊ መሆኑን ያውቅ ነበር። ይዋል ይደር እንጂ የፈወሳቸው ሰዎች በሙሉ እንደገና መታመማቸው፣ ከሞት ያስነሳቸውም ቢሆኑ እንደገና መሞታቸው እንደማይቀር ተገንዝቧል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለዘለቄታው የሚያስወግደው የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ያውቅ ነበር። ኢየሱስ ተአምራት ማድረግ ብቻ ሳይሆን “የመንግሥቱን ምሥራች” በቅንዓት ይሰብክ የነበረው ለዚህ ነው። (ማቴዎስ 9:35) እሱ የፈጸማቸው ተአምራት የአምላክ መንግሥት በቅርቡ በመላው ምድር የሚያመጣቸውን በረከቶች የሚያሳዩ ናሙናዎች ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ጊዜ አስመልክቶ ምን እንደሚል ተመልከት።

  •  የጤና ችግሮች አይኖሩም።

    “በዚያን ጊዜም የዕውር ዐይኖች ይገለጣሉ፤ የደንቈሮም ጆሮዎች ይከፈታሉ። አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤ የድዳውም አንደበት በደስታ ይዘምራል።” በተጨማሪም “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።”—ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6

  • ሞት አይኖርም።

    “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29

    “ሞትንም ለዘላለም ይውጣል። ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።”—ኢሳይያስ 25:8

  • የሞቱ ሰዎች ከሞት ይነሳሉ።

    “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ ነገር የሠሩ ደግሞ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።”—ዮሐንስ 5:28, 29

    “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት [ይነሳሉ]።”—የሐዋርያት ሥራ 24:15

  • የመኖሪያ ቤት እጦት ወይም ሥራ አጥነት አይኖርም።

    “ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። ከእንግዲህ ለሌሎች መኖሪያ ቤት አይሠሩም፤ ወይም ሌላው እንዲበላው አይተክሉም፤ . . . እኔ የመረጥኋቸው፣ በእጃቸው ሥራ ለረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል።”—ኢሳይያስ 65:21, 22

  • ጦርነት አይኖርም።

    “ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል።”—መዝሙር 46:9

    “ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ጦርነትንም ከእንግዲህ አይማሩም።”—ኢሳይያስ 2:4

  •  የምግብ እጥረት አይኖርም።

    “ምድር ፍሬዋን [ትሰጣለች]፤ እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል።”—መዝሙር 67:6

    “በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ።”—መዝሙር 72:16

  • ድህነት አይኖርም።

    “ችግረኞች ግን መቼም ቢሆን አይረሱም።”—መዝሙር 9:18

    “ችግረኛው በጮኸ ጊዜ፣ ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል። ለድኾችና ለችግረኞች ይራራል፤ ምስኪኖችንም ከሞት ያድናል።”—መዝሙር 72:12, 13

የአምላክ መንግሥት የሚያመጣቸውን እነዚህን በረከቶች መመልከትህ ኢየሱስ ለዚህ መንግሥት ትልቅ ቦታ የሰጠው ለምን እንደሆነ እንድትገነዘብ አልረዳህም? ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት፣ መስማት ለሚፈልግ ሰው ሁሉ ስለዚህ መንግሥት ለመናገር ይጓጓ ነበር፤ ምክንያቱም የአምላክ መንግሥት በዛሬው ጊዜ የሚታዩትን አሳዛኝ ችግሮች ሁሉ እንደሚያስወግድ ያውቅ ነበር።

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጹትን የአምላክ መንግሥት የሚያመጣቸውን ተስፋዎች ለማግኘት ትጓጓለህ? ከሆነ ስለዚህ መንግሥት የበለጠ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? ደግሞስ መንግሥቱ ከሚያመጣቸው በረከቶች ተቋዳሽ ለመሆን ምን ማድረግ ትችላለህ? የእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች የመጨረሻ ክፍል ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

^ አን.5 ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ የሚኖረው በሰማይ ሲሆን ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላም ለአምላክ መንግሥት ትልቅ ቦታ መስጠቱን እንደቀጠለ ግልጽ ነው።—ሉቃስ 24:51

^ አን.8 አምላክ ለተወሰነ ጊዜ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምን እንደሆነ ለማወቅ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ተመልከት።