በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክ ስለ አንተ ያስባል?

አምላክ ሊያጽናናህ ይችላል

አምላክ ሊያጽናናህ ይችላል

“ሐዘንተኞችን የሚያጽናናው አምላክ . . . እንድንጽናና አደረገን።”—2 ቆሮንቶስ 7:6

‘የአምላክ ልጅ ወድዶኛል፤ ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል።’—ገላትያ 2:20

አንዳንዶች የሚጠራጠሩበት ምክንያት፦ አንዳንድ ሰዎች መጽናኛ ማግኘት በጣም በሚያስፈልጋቸው ጊዜም እንኳ አምላክ ጣልቃ ገብቶ ችግሮቻቸውን እንዲቋቋሙ እንዲረዳቸው መጠየቅ ራስ ወዳድነት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ራኬል የምትባል አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “በዓለም ላይ ያለውን ሕዝብ ብዛት እንዲሁም የሚደርሱባቸውን ከባድ ችግሮች ስመለከት እኔን የሚያሳስቡኝ ችግሮች ከቁም ነገር የማይገቡ እንደሆኑ ስለሚሰማኝ የአምላክን እርዳታ ከመለመን ወደኋላ እላለሁ።”

የአምላክ ቃል ምን ያስተምራል? አምላክ፣ የሰው ልጆችን ለመርዳትና ለማጽናናት አስደናቂ የሆነ እርምጃ ወስዷል። በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ያለው ሰው ሁሉ ኃጢአትን ወርሷል፤ በመሆኑም የአምላክን መሥፈርቶች መቼም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ማሟላት አንችልም። ይሁን እንጂ አምላክ “[ስለወደደን] ለኃጢአታችን የማስተሰረያ መሥዋዕት እንዲሆን ልጁን” ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስን ልኮልናል። (1 ዮሐንስ 4:10) አምላክ በኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት አማካኝነት የኃጢአት ይቅርታ፣ ንጹሕ ሕሊናና ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዲኖረን አስችሎናል። * ይሁን እንጂ ይህ መሥዋዕት አምላክ በጥቅሉ ለመላው የሰው ዘር እንደሚያስብ የሚያሳይ ብቻ ነው? ወይስ ለአንተም በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልህ ያሳያል?

ሐዋርያው ጳውሎስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኢየሱስ ባቀረበው መሥዋዕት ልቡ በጥልቅ ስለተነካ “የምኖረው በወደደኝና ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ በሰጠው በአምላክ ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው” በማለት ጽፏል። (ገላትያ 2:20) በእርግጥ ኢየሱስ የሞተው ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ነበር። ሆኖም ጳውሎስ የኢየሱስን መሥዋዕት፣ አምላክ ለእሱ በግሉ የሰጠው ስጦታ እንደሆነ አድርጎ ተመልክቶታል።

የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት አምላክ ለአንተም በግልህ የሰጠህ ስጦታ ነው። ይህ ስጦታ አንተ ለአምላክ ምን ያህል ውድ እንደሆንክ ያረጋግጣል። ስጦታው “ዘላለማዊ መጽናኛና መልካም ተስፋ” ሊሰጥህ ይችላል፤ ይህ ደግሞ “በመልካም ሥራና ቃል ሁሉ [ያጸናሃል]።”—2 ተሰሎንቄ 2:16, 17

ሆኖም ኢየሱስ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ካቀረበ ወደ 2,000 የሚጠጉ ዓመታት አልፈዋል። ታዲያ አምላክ በዛሬው ጊዜ ወደ አንተ መቅረብ እንደሚፈልግ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

^ አን.5 ስለ ኢየሱስ መሥዋዕት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 5 ተመልከት።