በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

አምላክን ማን ፈጠረው?

አምላክን ማን ፈጠረው?

አንድ አባት ከሰባት ዓመት ልጁ ጋር ሲያወራ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። አባትየው እንዲህ ይለዋል፦ “ድሮ ድሮ፣ ከረጅም ጊዜ በፊት አምላክ ምድርንና በውስጧ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ፈጠረ፤ እንዲሁም ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ፈጠረ።” ልጁም ትንሽ አሰብ ካደረገ በኋላ “አባዬ፣ አምላክንስ ማን ፈጠረው?” ብሎ ይጠይቃል።

“አምላክን ማንም አልፈጠረውም” በማለት አባቱ መልስ ይሰጣል። “እሱ ሁልጊዜም ያለ ነው።” ይህ ቀላል ማብራሪያ ልጁን ለጊዜው ያረካዋል። ይሁን እንጂ እያደገ ሲሄድ ጥያቄው በአእምሮው መመላለሱን ይቀጥላል። አንድ አካል፣ መጀመሪያ ላይኖረው የሚችለው እንዴት እንደሆነ ለመረዳት ይከብደዋል። ምክንያቱም አጽናፈ ዓለምም እንኳ መጀመሪያ አለው። ‘ታዲያ አምላክ ከየት መጣ?’ የሚለው ጉዳይ ይህን ልጅ ያሳስበዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ ይሰጣል? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መልስ በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው አባት ከመለሰበት መንገድ ጋር ይመሳሰላል። ሙሴ “እግዚአብሔር ሆይ፤ . . . ገና ተራሮች ሳይወለዱ፣ ምድርንና ዓለምን ከመፍጠርህ በፊት፣ አንተ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላክ ነህ” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 90:1, 2) በተመሳሳይም ነቢዩ ኢሳይያስ እንደሚከተለው በማለት በአድናቆት ተናግሯል፦ “አታውቅምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው”! (ኢሳይያስ 40:28) ይሁዳም በደብዳቤው ላይ አምላክ “ከዘመናት ሁሉ በፊት” እንደኖረ ጽፏል።—ይሁዳ 25

እነዚህ ጥቅሶች እንደሚጠቁሙትና ሐዋርያው ጳውሎስም እንደተናገረው አምላክ ‘የዘላለም ንጉሥ’ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:17) ይህም ሲባል፣ የቱንም ያህል ወደኋላ ብንመለስ አምላክ ምንጊዜም ነበረ ማለት ነው። ወደፊትም ቢሆን ምንጊዜም ይኖራል። (ራእይ 1:8) በመሆኑም ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ መገለጫ ከሆኑት መሠረታዊ ነገሮች አንዱ ዘላለማዊ መሆኑ ነው።

ይህን ሐሳብ መረዳት ከባድ የሚሆንብን ለምንድን ነው? የሕይወት ዘመናችን አጭር በመሆኑ ስለ ጊዜ ያለን አመለካከት ከይሖዋ በጣም የተለየ ስለሆነ ነው። አምላክ ዘላለማዊ በመሆኑ ለእሱ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን ነው። (2 ጴጥሮስ 3:8) በምሳሌ ለማስረዳት፣ ካደገች በኋላ 50 ቀናት ገደማ ብቻ የምትኖረው ፌንጣ 70 ወይም 80 ዓመት የሚሆነውን የእኛን ሕይወት ርዝመት መረዳት ትችላለች? በጭራሽ! ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ከታላቁ ፈጣሪያችን ጋር ስንወዳደር እኛም እንደ ፌንጣዎች መሆናችንን ይገልጻል። የማመዛዘን ችሎታችንም እንኳ ከእሱ ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። (ኢሳይያስ 40:22፤ 55:8, 9) ስለዚህ ከይሖዋ ጋር በተያያዘ የሰው ልጆች ሙሉ በሙሉ የማይረዷቸው ነገሮች መኖራቸው ምንም አያስደንቅም።

አምላክ ዘላለማዊ እንደሆነ የሚገልጸውን ጽንሰ ሐሳብ ለመረዳት ከባድ ሊሆን ቢችልም ነገሩ ምክንያታዊ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም። አምላክን የፈጠረው ሌላ አካል ቢኖር ኖሮ ይህ አካል ፈጣሪ ይሆን ነበር። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ‘ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው’ ይሖዋ ነው። (ራእይ 4:11) ከዚህም በላይ አጽናፈ ዓለም ያልነበረበት ጊዜ እንዳለ እናውቃለን። (ዘፍጥረት 1:1, 2) ታዲያ አጽናፈ ዓለም ከየት መጣ? አጽናፈ ዓለምን የፈጠረው አካል ከአጽናፈ ዓለም በፊት በሕይወት የነበረ መሆን አለበት። በተጨማሪም ፈጣሪ፣ እንደ አንድያ ልጁና እንደ መላእክት ያሉ ሌሎች የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ወደ ሕልውና ከመምጣታቸው በፊትም ይኖር ነበር። (ኢዮብ 38:4, 7፤ ቆላስይስ 1:15) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በመጀመሪያ አምላክ ብቻውን ይኖር ነበር። አምላክ ወደ ሕልውና የመጣው ተፈጥሮ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ፈጣሪን ሊፈጥር የሚችል ሌላ አካል አልነበረም።

የእኛ ሕልውናም ሆነ የመላው አጽናፈ ዓለም መኖር ዘላለማዊ አምላክ እንዳለ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው። ግዙፉን አጽናፈ ዓለማችንን የፈጠረውና የሚቆጣጠረውን ሕግ የደነገገለት አካል ምንጊዜም በሕይወት የነበረ መሆን አለበት። ለሌሎቹ ነገሮች ሁሉ የሕይወትን እስትንፋስ ሊሰጣቸው የሚችለው እሱ ብቻ ነው።—ኢዮብ 33:4