በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ከፍትሕ መዛባትና ከዓመፅ ጋር የራሴን ትግል አደርግ ነበር

ከፍትሕ መዛባትና ከዓመፅ ጋር የራሴን ትግል አደርግ ነበር
  • የትውልድ ዘመን፦ 1960

  • የትውልድ አገር፦ ሊባኖስ

  • የኋላ ታሪክ፦ በከንግ ፉ የሠለጠነ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግሁት እስራኤልንና ሊባኖስን በሚያዋስነው ድንበር አቅራቢያ በምትገኝ ረሚሽ የምትባል ከተማ ነው፤ በወቅቱ የእርስ በርስ ጦርነት ነበረ። የተቀበሩ ቦንቦች ሲፈነዱና ንጹሐን ሰዎች እጃቸውን ወይም እግራቸውን ሲያጡ ተመልክቻለሁ፤ ያየሁት ነገር እስካሁንም ከአእምሮዬ አልጠፋም። ኑሮ ከባድ ሲሆን ወንጀልና ዓመፅ ተስፋፍቶ ነበር።

 

ቤተሰባችን ከካቶሊክ ሃይማኖት ምሥራቃዊ አብያተ ክርስቲያናት አንዱ የሆነው የማሮናይት ቤተ ክርስቲያን ተከታይ ነበር። አባቴ 12 አባላት ለነበሩት ቤተሰባችን በቁሳዊ የሚያስፈልገውን ለማቅረብ ደፋ ቀና ስለሚል ሕይወቱ በሥራ የተወጠረ ነበር፤ እናቴ ግን የተቀረነው የቤተሰቡ አባላት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንድንሄድ ታደርግ ነበር። ውሎ አድሮ ግን፣ እንደ ማኅበረሰቡ ሁሉ ቤተ ክርስቲያንም ደካሞችን እንደማትደግፍ ተሰማኝ።

በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለሁ ከንግ ፉ የሚባለው የማርሻል አርት መስክ ትኩረቴን ሳበው። በዚህ መስክ ጥብቅ ሥልጠና የወሰድኩ ሲሆን በእጅና በእግር ምቶችን በመሰንዘር እንዲሁም የተለያዩ የማርሻል አርት መሣሪያዎችን በመጠቀም ረገድ ጥሩ ችሎታ አዳበርኩ። ‘ጦርነቱን ማስቆም ባልችልም እንኳ ዓመፀኛ ሰዎችን ለማስቆም መሞከር እችላለሁ’ ብዬ አስብ ነበር። ሁለት ሰዎች ሲጣሉ ካየሁ ወዲያውኑ ጣልቃ እገባለሁ። በተፈጥሮዬ ግልፍተኛ በመሆኔ በትንሽ በትልቁ እቆጣ ነበር። የፍትሕ መዛባትንና ዓመፅን ለማስቀረት የራሴን ትግል አደርግ ስለነበር በደቡባዊ ሊባኖስ በሙሉ ሰዎች ይፈሩኝ ነበር።

በ1980 በቤሩት ከሚገኝ የከንግ ፉ ቡድን ጋር ተቀላቀልኩ። ከተማዋ በየቀኑ በቦምብ፣ በመድፍና በሮኬት ትደበደብ የነበረ ቢሆንም እኔ ከሥልጠናው አልቀርም ነበር። ብሩስ ሊ የተባለውን የአሜሪካ ዜግነት ያለው ትውልደ ቻይናዊ ተዋናይና የከንግ ፉ ሻምፒዮን አኗኗር ለመኮረጅ ከማደርገው ጥረት እንዲሁም ከመብላትና ከመተኛት ሌላ ሕይወት አልነበረኝም። የብሩስ ሊን የፀጉር አበጣጠር፣ አረማመድና ከንግ ፉ በሚያሳይበት ጊዜ የሚያሰማውን ድምፅ ሳይቀር ኮረጅኩ። ፈገግታ የሚባል ነገር በፊቴ ላይ ፈጽሞ አይታይም ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? ግቤ ቻይና ሄጄ የከንግ ፉ ባለሙያ መሆን ነበር። ለቻይና ጉዞዬ ለመዘጋጀት ከባድ ልምምድ እያደረግሁ ባለሁበት ወቅት አንድ ምሽት ላይ በር ሲንኳኳ ሰማሁ። በሩን ስከፍት አንድ ጓደኛዬን ከሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር አገኘሁት። ልምምድ ላይ ስሆን የምለብሰውን ጥቁር ልብስ ለብሼና ላብ በላብ ሆኜ ነበር፤ ሰዎቹን “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም የማውቀው ነገር የለም” አልኳቸው። ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ሕይወቴ ሊለወጥ መሆኑን አላወቅሁም ነበር።

 

የይሖዋ ምሥክሮቹ፣ ሰዎች በራሳቸው ጥረት የፍትሕ መዛባትንና ዓመፅን መቼም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ የማይችሉት ለምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳዩኝ። እንዲህ ላሉት ችግሮች ዋነኛው መንስኤ ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ አስረዱኝ። (ራእይ 12:12) በፊታቸው ላይ የሚነበበው ሰላምና የመተማመን ስሜት አስደነቀኝ። እንዲሁም አምላክ ስም እንዳለው ሲያስተምሩኝ ልቤ ተነካ። (መዝሙር 83:18 NW) በተጨማሪም “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጥቂቱ ይጠቅማል፤ ለአምላክ ማደር ግን ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ ሕይወት የሚሆን ተስፋ ስላለው ለሁሉም ነገር ይጠቅማል” የሚለውን በ⁠1 ጢሞቴዎስ 4:8 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ አሳዩኝ። ይህ ሐሳብ በሕይወቴ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳደረ።

የሚያሳዝነው ነገር፣ የይሖዋ ምሥክሮቹ ተመልሰው እንዳይመጡ ቤተሰቦቼ ነግረዋቸው ስለነበር ከእነሱ ጋር የነበረኝ ግንኙነት ተቋረጠ። ያም ሆኖ ከንግ ፉ መለማመዴን ለማቆምና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ወሰንኩ። ወንድሞቼ ውሳኔዬን ባይወዱትም የይሖዋ ምሥክሮችን ፈልጌ እንደገና ለማግኘትና ከእነሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ቆርጬ ነበር።

የይሖዋ ምሥክሮችን መፈለጌን ተያያዝኩት፤ ይሁን እንጂ ላገኛቸው አልቻልኩም። በዚህ መሃል አባቴ በድንገት በመሞቱና በቤተሰባችን ላይ ሌሎች አሳዛኝ ነገሮች በመድረሳቸው ከባድ ሐዘን ላይ ወደቅሁ። በአንድ የግንባታ ኩባንያ ሥራ ጀምሬ ነበር፤ አንድ ቀን አዴል የሚባል አንድ የሥራ ባልደረባዬ ፊቴ ላይ ሐዘን የሚነበበው ለምን እንደሆነ ጠየቀኝ። ከዚያም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘው የትንሣኤ ተስፋ ነገረኝ። ይህ አፍቃሪና ደግ የይሖዋ ምሥክር ለቀጣዮቹ ዘጠኝ ወራት መጽሐፍ ቅዱስን አስጠናኝ።

በጥናቴ እየገፋሁ ስሄድ በባሕሪዬ ላይ ትልቅ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልገኝ መገንዘብ ጀመርኩ። ይህን ማድረግ ቀላል አልነበረም። ነጭናጫና በቀላሉ የምቆጣ ሰው ነበርኩ። ቁጣዬን መቆጣጠርና በስሜት ከመመራት መቆጠብ የምችለው እንዴት እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተማርኩ። ለምሳሌ ያህል፣ በማቴዎስ 5:44 ላይ “ለጠላቶቻችሁ ፍቅር ማሳየታችሁን እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ መጸለያችሁን ቀጥሉ” የሚለው ኢየሱስ የሰጠው ምክር ይገኛል። ሮም 12:19 ላይ ደግሞ “ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ከዚህ ይልቅ ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ይላል ይሖዋ’” በማለት ያስጠነቅቃል። እነዚህና ሌሎችም ጥቅሶች ቀስ በቀስ ውስጣዊ ሰላም እንዳገኝ ረዱኝ።

ያገኘሁት ጥቅም፦

ቤተሰቦቼ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴን መጀመሪያ ላይ ቢቃወሙም አሁን ለይሖዋ ምሥክሮች አክብሮት አላቸው። እንዲያውም አንዱ ወንድሜ የይሖዋ ምሥክር ሆኗል፤ እናታችንም እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ የእኛን እምነት ደግፋ ለሌሎች ትናገር ነበር።

በተጨማሪም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውድ ባልደረባዬ የሆነችልኝን አኒታ የተባለች ግሩምና ታማኝ ሚስት በማግኘት ተባርኬያለሁ። ከ2000 ጀምሮ እኔና አኒታ የምንኖረው በኤስኪልስቱና፣ ስዊድን ሲሆን አረብኛ ተናጋሪ ለሆኑ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እናስተምራለን።

የዓመፅ ሰለባ ለሚሆኑ ሰዎች አሁንም ቢሆን በጣም አዝናለሁ። ይሁን እንጂ ለዚህ ችግር ዋነኛው መንስኤ ምን እንደሆነና አምላክ በቅርቡ መቋጫ እንደሚያበጅለት ማወቄ እውነተኛ ደስታና ሰላም ይሰጠኛል።—መዝሙር 37:29

እኔና ባለቤቴ አገልግሎት በጣም እንወዳለን። ሰዎችን ስለ ይሖዋ ማስተማር ያስደስተናል