መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
ጥያቄዎቼን በሙሉ የመለሱልኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነው!
የትውልድ ዘመን 1950
የትውልድ አገር ስፔን
የኋላ ታሪክ የካቶሊክ መነኩሲት የነበረች
የቀድሞ ሕይወቴ፦
እኔ በተወለድኩበት ጊዜ ወላጆቼ በሰሜናዊ ምዕራብ ስፔን ባለችው ጋሊሺያ የምትባል የገጠር መንደር አንድ አነስተኛ እርሻ ነበራቸው። እኔ ከስምንት ልጆች መካከል አራተኛ ነኝ። አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት ነበረን። በዚያን ጊዜ ስፔን ውስጥ ከቤቱ ቢያንስ አንዱን ልጅ ወደ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ወይም ገዳም ማስገባት የተለመደ ነበር። በመሆኑም ከእኛ ቤተሰብ፣ አንዱ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ሲገባ ሁለታችን ገዳም ገባን።
ታላቅ እህቴን ተከትዬ ማድሪድ ወደሚገኝ አንድ የሴቶች ገዳም የገባሁት በ13 ዓመቴ ነበር። በገዳሙ የነበረው መንፈስ ፍቅር የሰፈነበት አልነበረም። በገዳሙ ውስጥ ደንቦች፣ የጸሎት ሥርዓቶችና ጭቆና ያለበት ሕይወት እንጂ የወዳጅነት መንፈስ የሚባል ነገር አልነበረም። ማለዳ ተነስተን ለማሰላሰል በገዳሙ ውስጥ ባለው የጸሎት ቤት እንሰባሰባለን፤ እኔ ግን ብዙውን ጊዜ አእምሮዬ ባዶ ስለሚሆንብኝ የማሰላስለው ነገር አልነበረም። በኋላም መንፈሳዊ መዝሙሮችን እንዘምራለን፤ እንዲሁም የቁርባን ሥርዓት እናደርጋለን፤ ይህ ሁሉ የሚካሄደው በላቲን ቋንቋ ነው። በዚህም ምክንያት ምንም ነገር አይገባኝም ነበር፤ ከዚህም በላይ አምላክ ከእኔ በጣም ሩቅ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ከሰዎች ጋር ምንም ሳላወራ ቀኑ ያልፋል። እኔና እህቴ እንኳ ስንገናኝ “ሰላም ለንጽሕት ማርያም” ከማለት ውጪ ምንም አንነጋገርም። መነኮሳቱ ከምግብ በኋላ ለግማሽ ሰዓት ያህል ብቻ እንድናወራ ይፈቅዱልን ነበር። ከወላጆቼ ጋር ሳለሁ ከነበረኝ ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት ፍጹም የተለየ ነበር! ብቸኝነት ስለሚሰማኝ ብዙ ጊዜ አለቅስ ነበር።
ከአምላክ ጋር የቀረበ ዝምድና እንዳለኝ ፈጽሞ ተሰምቶኝ ባያውቅም በ17 ዓመቴ ቃለ መሐላ ፈጽሜ መነኩሲት ሆንኩ። በእርግጥ፣ ያደረግኩት የሚጠበቅብኝን ነገር ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ አምላክ ለዚህ መብት የመረጠኝ ስለመሆኑ መጠራጠር ጀመርኩ። መነኮሳቱ፣ እንዲህ ዓይነት ጥርጣሬ ያላቸው ሰዎች መጨረሻቸው በገሃነመ እሳት መጣል እንደሆነ ይናገሩ ነበር። ያም ሆኖ ጥርጣሬው ከውስጤ አልወጣም። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን እንዳላገለለ፣ እንዲያውም ጊዜውን የሚያሳልፈው ሌሎችን በማስተማርና በመርዳት እንደሆነ አውቅ ነበር። (ማቴዎስ 4:23-25) ሃያ ዓመት ሲሆነኝ መነኩሲት ሆኜ እንድቀጥል የሚያደርግ ምንም ምክንያት እንደሌለኝ ተሰማኝ። የሚገርመው ነገር መነኩሲት ሆኜ ለመቀጠል ጥርጣሬ ካለኝ በተቻለ መጠን ቶሎ ከገዳሙ እንድወጣ የገዳሙ እመምኔት (የሴቶች ገዳም አስተዳዳሪ) ነገረችኝ። ይህን ያለችው በሌሎች ላይ ተጽዕኖ እንዳላሳድር ስለፈራች ይመስለኛል። ስለዚህ ገዳሙን ለቅቄ ወጣሁ።
ወደ ቤት ስመለስ ወላጆቼ ስሜቴን በጣም ተረዱልኝ። ይሁን እንጂ በመንደራችን ሥራ ማግኘት ስላልቻልኩ ወንድሜ ወደሚኖርበት ወደ ጀርመን ሄድኩ። ወንድሜ፣ ከአገራቸው ውጭ የሚኖሩ ስፔናውያን የመሠረቱት የአንድ ኮሚኒስት ቡድን አባል ነበረ። እኔም ለሠራተኞች መብትና ለሴቶች እኩልነት ከሚታገሉት ከእነዚህ ሰዎች ጋር ስሆን ጥሩ ስሜት ተሰማኝ። ስለዚህ እኔም ኮሚኒስት ሆንኩ፤ በኋላም ከቡድኑ አባላት አንዱን አገባሁ። የኮሚኒስት ጽሑፎችን ሳሰራጭና በተቃውሞ ሰልፎች ስካፈል ጠቃሚ ነገር እንዳከናወንኩ ይሰማኝ ጀመር።
ከጊዜ በኋላ ግን እንደገና ተስፋ ቆረጥኩ። ኮሚኒስቶች ብዙውን ጊዜ የሚሰብኩትን ነገር ተግባራዊ እንደማያደርጉ ተሰማኝ። በ1971 የተወሰኑ ወጣት የቡድናችን አባላት ፍራንክፈርት ያለውን የስፔን ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ባቃጠሉ ጊዜ ጥርጣሬዬ ይበልጥ ተጠናከረ። ይህን ያደረጉት የስፔን አምባገነናዊ መንግሥት የሚፈጽመውን የፍትሕ መጓደል ለመቃወም ነበር። እኔ ግን በዚህ መንገድ ተቃውሞን መግለጽ ስህተት እንደሆነ አምን ነበር።
የመጀመሪያ ልጄን ስወልድ፣ በኮሚኒስት ስብሰባዎች ላይ መገኘቴን ላቆም እንደሆነ ለባለቤቴ ነገርኩት። የቀድሞ ጓደኞቼ አራስ ሆኜ ሊጠይቁኝ ስላልመጡ በጣም ብቸኝነት ተሰማኝ። ሕይወት ትርጉም የለሽ ሆነብኝ። የኅብረተሰቡን ሕይወት ለማሻሻል ጥረት ማድረግ በእርግጥ ጥቅም ያለው ስለመሆኑ ጥርጣሬ አደረብኝ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?
በ1976 ሁለት ስፔናውያን የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን መጥተው አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ሰጡኝ። ሁለተኛ ጊዜ ሊጠይቁኝ ሲመጡ በሰዎች ላይ ስለሚደርሰው መከራ፣ መድልዎና ግፍ በተመለከተ የጥያቄ መዓት አዥጎደጎድኩባቸው። ጥያቄዎቼን በሙሉ የመለሱልኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መሆኑ አስገረመኝ! እኔም መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና የቀረበልኝን ግብዣ ምንም ሳላንገራግር ተቀበልኩ።
መጀመሪያ ላይ የማጠናው እንዲሁ ለማወቅ ያህል ብቻ ነበር። ይሁን እንጂ እኔና ባለቤቴ በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚካሄዱ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ስንጀምር ሁኔታው ተለወጠ። በዚህ ጊዜ ሁለተኛ ልጃችንን ወልደን ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ስብሰባ ይዘውን በመሄድና በስብሰባው ወቅት ልጆቻችንን በመያዝ ደግነት አሳዩን። በዚህም የተነሳ የይሖዋ ምሥክሮችን እየወደድኳቸው መጣሁ።
እንደዚያም ሆኖ በሃይማኖት ላይ ያሉኝ አንዳንድ ጥርጣሬዎች አልተወገዱም ነበር። አንድ ወቅት ቤተሰቤን ለመጠየቅ ወደ ስፔን ሄድኩ። ቄስ የሆነው አጎቴ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን እንዳቆም ተስፋ ሊያስቆርጠኝ ሞክሮ ነበር። ይሁን እንጂ በአካባቢው የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በጣም ረዱኝ። በጀርመን እንደነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉ እነሱም ለጥያቄዎቼ በሙሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መልስ ሰጡኝ። ወደ ጀርመን ስመለስ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን ለመቀጠል ወሰንኩ። ባለቤቴ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱን ቢያቆምም እኔ ግን ማጥናቴን ቀጠልኩ። በ1978 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።
ያገኘሁት ጥቅም፦
ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ማወቄ ሕይወቴ ዓላማ ያለው እንዲሆን አስችሎኛል። ለምሳሌ ያህል፣ 1 ጴጥሮስ 3:1-4 ሚስቶች “ጥልቅ አክብሮት” በማሳየት ለባሎቻቸው ‘እንዲገዙ’ እና “በአምላክ ዓይን ከፍተኛ ዋጋ ያለውን . . . ገር መንፈስ” እንዲኮተኩቱ ያበረታታል። እንዲህ ያሉት መመሪያዎች የሚስትነትና የእናትነት ድርሻዬን እንድወጣ ረድተውኛል።
አሁን የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩ 35 ዓመታት አልፈዋል። በእውነተኛው ዓለም አቀፍ መንፈሳዊ ቤተሰብ ውስጥ በመታቀፍ አምላክን ማገልገል በመቻሌ ደስተኛ ነኝ፤ እንዲሁም ከአምስቱ ልጆቼ አራቱ እንደዚሁ እያደረጉ መሆናቸውም ያስደስተኛል።