በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

አምላክ ምን አድርጎልሃል?

አምላክ ምን አድርጎልሃል?

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።”—ዮሐንስ 3:16 የ1954 ትርጉም

ይህ ጥቅስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጣም ከሚታወቁትና በሰፊው ከሚጠቀሱት ጥቅሶች አንዱ ነው። የዚህን ጥቅስ ያህል “አምላክ ከሰው ዘር ጋር ያለውን ግንኙነትና የመዳንን መንገድ ቅልብጭ ባለ አነጋገር የሚገልጽ” ሌላ ጥቅስ እንደሌለ ይነገራል። በዚህም ምክንያት በአንዳንድ አገሮች የዚህ ጥቅስ ሐሳብ ወይም ምዕራፍና ቁጥሩ ብቻውን ብዙውን ጊዜ ሕዝባዊ ዝግጅቶች በሚደረጉበት ወቅት፣ በመኪናና በግንብ ላይ እንዲሁም በሌሎች ስፍራዎች ተጽፎ ይታያል።

ከዚህ መደምደም እንደሚቻለው፣ ጥቅሱን የሚጽፉት ሰዎች የአምላክ ፍቅር የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኙ ዋስትና የሚሰጣቸው መሆኑን ያመኑበት ይመስላል። አንተስ ምን ይሰማሃል? የአምላክ ፍቅር ለአንተ ምን ትርጉም አለው? አምላክ ለአንተ ያለውን ፍቅር የሚገልጽ ምን ነገር እንዳደረገልህ ይሰማሃል?

“ዓለሙን እንዲሁ ወዶአል”

ብዙ ሰዎች ግዑዙን ጽንፈ ዓለም፣ በምድር ላይ ያሉ ነገሮችንና የሰው ልጆችን የፈጠረው አምላክ እንደሆነ ያምናሉ። ሕይወት ያላቸው ነገሮች የተሠሩበት መንገድ በጣም ውስብስብና አስደናቂ መሆኑ እነዚህን ነገሮች ወደ ሕልውና ያመጣ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል እንዳለ ያሳያል። ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ሰዎች፣ ሕይወት ስለሰጣቸው አምላክን በየዕለቱ ያመሰግኑታል። በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች፣ በሕይወት ለመቀጠልና በሚሠሩት ነገር ለመደሰት የቻሉት አምላክ አየር፣ ውኃ፣ ምግብና የመሬት ተፈጥሯዊ ዑደቶች እንዲኖሩ ስላደረገ እንዲሁም ለመኖር የሚያስፈልጉ ሌሎች ነገሮችን ስላሟላላቸው እንደሆነ ይገነዘባሉ።

በእርግጥም ፈጣሪያችንና በሕይወትም እንድንቀጥል የሚያደርገን አምላክ በመሆኑ ላደረገልን ነገሮች በሙሉ ማመስገናችን ተገቢ ነው። (መዝሙር 104:10-28፤ 145:15, 16፤ የሐዋርያት ሥራ 4:24) አምላክ ሕይወት እንዲኖር ለማድረግ ብቻ እንኳ እያደረገ ያለውን ነገር ሁሉ ስናስብ እሱ ለእኛ ያለውን ፍቅር እንመለከታለን። ሐዋርያው ጳውሎስ ጉዳዩን እንደሚከተለው  በማለት ገልጾታል፦ “ሕይወትንና እስትንፋስንም ሆነ ማንኛውንም ነገር ለሰው ሁሉ የሚሰጠው እሱ ስለሆነ . . . ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው።”—የሐዋርያት ሥራ 17:25, 28

ይሁን እንጂ አምላክ፣ ለመኖር የሚያስፈልጉ ነገሮችን ከመስጠት ባለፈ ለእኛ ያለውን ፍቅር በብዙ መንገዶች ገልጾልናል። ለምሳሌ፣ መንፈሳዊ ነገሮችን የመረዳት ችሎታ በመስጠትና ይህን ፍላጎታችንን ለማርካት የሚያስችል ዝግጅት በማድረግ በምድር ላይ ካሉት ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ የላቀ ቦታና ክብር ሰጥቶናል። (ማቴዎስ 5:3) በዚህ መንገድ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች የአምላክ ቤተሰብ አባላት ማለትም የእሱ “ልጆች” የመሆን ተስፋ አላቸው።—ሮም 8:19-21

ዮሐንስ 3:16 ላይ የሚገኘው ሌላው ሐሳብ እንደሚገልጸው አምላክ ፍቅሩን ያሳየን ልጁን ኢየሱስን ወደ ምድር በመላክ ስለ አምላኩና አባቱ እንዲያስተምረን ብሎም ለእኛ ሲል እንዲሞት በማድረግ ነው። ይሁንና ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ለሰው ዘር ሲል መሞቱ አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነና የእሱ ሞት አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ ግልጽ አይሆንላቸውም። እንግዲያው ኢየሱስ መሞቱ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያትና ሞቱ ያለውን ጥቅም አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ማብራሪያ እንመልከት።

‘አንድያ ልጁን ሰጥቷል’

የሰው ዘር በሙሉ ሟች በመሆኑ ለበሽታና ለእርጅና የተጋለጠ ነው። ሆኖም ይሖዋ ለሰው ልጆች የነበረው ዓላማ ይህ አይደለም። ለመጀመሪያዎቹ ሰዎች በምድር ላይ በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ የሚሆነው አንድ ነገር ከተሟላ ብቻ ነው፤ ይኸውም አምላክን ከታዘዙ ብቻ ነው። እሱን ካልታዘዙ እንደሚሞቱ አምላክ ነግሯቸዋል። (ዘፍጥረት 2:17) ይሁንና የመጀመሪያው ሰው በአምላክ ሥልጣን ላይ በማመፅ በራሱና በዘሮቹ ላይ ሞትን አመጣ። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።”—ሮም 5:12

ይሁን እንጂ አምላክ “ፍትሕን ይወዳል።” (መዝሙር 37:28) ምንም እንኳ የመጀመሪያው ሰው ሆን ብሎ የፈጸመውን የዓመፅ ድርጊት ችላ ብሎ ሊያልፈው ባይችልም በአንድ ሰው አለመታዘዝ የተነሳ መላው የሰው ዘር ለዘላለም እየተሠቃየና እየሞተ እንዲቀጥል አልፈረደበትም። ከዚህ ይልቅ “ሕይወት በሕይወት” የሚለውን የሕግ መሥፈርት ተጠቅሞ ፍትሕ እንዲከበር በማድረግ ታዛዥ የሰው ዘሮች ዳግመኛ ዘላለማዊ ሕይወት ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ አመቻቸ። (ዘፀአት 21:23) አሁን የሚነሳው ጥያቄ፣ ‘አዳም ያጠፋው ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ተመልሶ ሊገኝ የሚችለው እንዴት ነው?’ የሚለው ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው አንድ ሰው አዳም ከነበረው ሕይወት ጋር የሚመጣጠን ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ከሰጠ ወይም መሥዋዕት ካደረገ ነው።

ኢየሱስ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ሲል ወደ ምድር መጥቶ ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኗል

የአዳም ዘሮች በሙሉ ፍጹም ባለመሆናቸው ከእነሱ መካከል ማንም እንዲህ ዓይነቱን ዋጋ ማቅረብ እንደማይችል ግልጽ ነው፤ ኢየሱስ ግን ይህን ዋጋ መክፈል ችሏል። (መዝሙር 49:6-9) ኢየሱስ ሲወለድ በዘር የሚተላለፈውን ኃጢአት ባለመውረሱ አዳም ኃጢአት ከመሥራቱ በፊት የነበረው ዓይነት ፍጹም ሕይወት ነበረው። በመሆኑም ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት የሰውን ዘር ከኃጢአት ባርነት ነፃ ለማውጣት ቤዛ ከፍሏል። በዚህ መንገድ የሰው ልጆች፣ አዳምና ሔዋን በአንድ ወቅት የነበራቸው  ዓይነት ፍጹም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። (ሮም 3:23, 24፤ 6:23) ታዲያ ከዚህ ታላቅ የፍቅር መግለጫ ተጠቃሚ ለመሆን ከእኛ የሚጠበቅ ነገር ይኖራል?

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ”

ወደ ዮሐንስ 3:16 ስንመለስ “[በኢየሱስ] የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ” የሚል ሐሳብ እናገኛለን። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው የዘላለም ሕይወት ስጦታ ለማግኘት ከእኛ የሚጠበቅ ነገር አለ። በኢየሱስ ማመን እና እሱን መታዘዝ ያስፈልገናል።

‘መታዘዝ የሚለው ሐሳብ ከየት መጣ? ደግሞስ ኢየሱስ የተናገረው “በእርሱ የሚያምን ሁሉ” የዘላለም ሕይወት እንደሚኖረው አይደለም?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። አዎን፣ እምነት የግድ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እምነት የሚለው ቃል እንዲሁ አንድን ነገር ከመቀበል ያለፈ ነገርን እንደሚያመለክት ማስታወሱ አስፈላጊ ነው። ቫይንስ ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ወርድስ እንደሚገልጸው ዮሐንስ የተጠቀመበት ግሪክኛ ቃል የሚያመለክተው “እንዲሁ አንድን ነገር ማመንን ብቻ ሳይሆን የዚያን ነገር አስፈላጊነት ተቀብሎ እርምጃ መውሰድን” ነው። አንድ ሰው የአምላክን ሞገስ ማግኘት ከፈለገ ኢየሱስ አዳኝ መሆኑን በሐሳብ ደረጃ ከመቀበል ያለፈ ነገር ያስፈልገዋል። ግለሰቡ ከማመን በተጨማሪ ኢየሱስ ያስተማረውን ነገር በሥራ ለማዋል ከልብ ጥረት ማድረግ አለበት። ተግባር ሳይኖር እምነት እንዳለን ብንናገር ከንቱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “እምነትም ያለ ሥራ የሞተ ነው” ይላል። (ያዕቆብ 2:26) በሌላ አነጋገር፣ ከእምነቱ ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ይጠበቅበታል።

ጳውሎስ ነጥቡን ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ሰው ለሁሉም መሞቱን ስለተረዳን ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ይለናል፤ . . . በሕይወት ያሉት ከእንግዲህ ለራሳቸው ከመኖር ይልቅ ለእነሱ ለሞተውና ለተነሳው እንዲኖሩ እሱ ለሁሉም ሞቷል።” (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15) ኢየሱስ ለከፈለልን መሥዋዕት ያለን ልባዊ አድናቆት በሕይወታችን ውስጥ ለውጥ እንድናደርግ ይኸውም ለራሳችን ብቻ ከመኖር ይልቅ ለእኛ ሲል ለሞተው ለኢየሱስ እንድንኖር ሊገፋፋን ይገባል። በሌላ አባባል የኢየሱስን ትምህርት በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ሊሆን ይገባል ማለት ነው። ይህ ደግሞ በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ የምንሰጣቸውን ነገሮች፣ ምርጫዎቻችንን እና የምናደርገውን ማንኛውንም ነገር በተመለከተ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚጠይቅብን የታወቀ ነው። ታዲያ በኢየሱስ የሚያምኑና ይህን በተግባር የሚያሳዩ ሰዎች ምን ሽልማት ያገኛሉ?

“የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ”

በመጨረሻም ዮሐንስ 3:16 እንደሚገልጸው በቤዛው ዝግጅት ላይ እምነት ለሚያሳድሩና በመለኮታዊ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መሠረት ለሚኖሩ ሰዎች አምላክ ተስፋ ሰጥቷል። የአምላክ ዓላማ እንደዚህ ያሉ ታማኝ ሰዎች ‘የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ እንጂ እንዲጠፉ’ አይደለም። ይሁን እንጂ ከአምላክ ፍቅር የሚጠቀሙ ግለሰቦች የሚያገኙት ሽልማት ሁለት ዓይነት ነው።

ኢየሱስ በአንደኛው ቡድን ውስጥ ላሉት ሰዎች በሰማይ ዘላለማዊ ሕይወት እንደሚያገኙ ቃል ገብቶላቸዋል። ለታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ከእሱ ጋር በክብር እንዲገዙ ስፍራ እንደሚያዘጋጅላቸው በግልጽ ነግሯቸው ነበር። (ዮሐንስ 14:2, 3፤ ፊልጵስዩስ 3:20, 21) በሰማይ ለመኖር ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች “የአምላክና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ እንዲሁም ከእሱ ጋር ነገሥታት ሆነው ለአንድ ሺህ ዓመት ይገዛሉ።”—ራእይ 20:6

እንደዚህ ያለውን መብት የሚያገኙት ከክርስቶስ ተከታዮች መካከል የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ብቻ ናቸው። እንዲያውም ኢየሱስ “አንተ ትንሽ መንጋ፣ አባታችሁ መንግሥትን ሊሰጣችሁ ስለፈቀደ አትፍሩ” ብሏል። (ሉቃስ 12:32) ይህ “ትንሽ መንጋ” ምን ያህል ቁጥር ይኖረዋል? ራእይ 14:1, 4 እንዲህ ይላል፦ “እኔም አየሁ፤ እነሆ፣ በጉ [ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ] በጽዮን ተራራ [በሰማይ] ላይ ቆሟል፤ ከእሱም ጋር የእሱ ስምና የአባቱ ስም በግምባራቸው ላይ የተጻፈባቸው አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። . . . እነዚህ ለአምላክና ለበጉ እንደ በኩራት ሆነው ከሰዎች መካከል ተዋጅተዋል።” ወደ ሰማይ የሚሄዱት 144,000 ግለሰቦች በዚህ ምድር ላይ ኖረው ከሞቱት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ሲወዳደሩ በእርግጥም “ትንሽ መንጋ” መባላቸው ተገቢ ነው። እነዚህ ሰዎች ነገሥታት ሆነው እንደሚገዙ ተገልጿል፤ ታዲያ የሚገዙት በማን ላይ ነው?

ኢየሱስ በሰማይ ላይ ከሚገኘው መንግሥት የሚወርደውን በረከት የሚቀበሉ ታማኝ ሰዎችን ስላቀፈ ሌላ ቡድን ተናግሯል። በዮሐንስ 10:16 ላይ እንደምናየው ኢየሱስ “ከዚህ ጉረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነሱንም ማምጣት አለብኝ፤ ድምፄንም ይሰማሉ፤ ሁሉም አንድ መንጋ ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ” በማለት ገልጿል። እነዚህ “በጎች” በመጀመሪያ ለአዳምና ለሔዋን ታስቦላቸው የነበረውን በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ለማግኘት ይጓጓሉ። የእነዚህ በጎች ተስፋ በምድር ላይ መኖር መሆኑን እንዴት እናውቃለን?

 መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ወደ ገነትነት እንደምትቀየር በብዙ ቦታዎች ላይ ይናገራል። ይህንን ማየት ከፈለግህ መጽሐፍ ቅዱስህን ገልጠህ የሚከተሉትን ጥቅሶች ማንበብ ትችላለህ፦ መዝሙር 37:9-11፤ 46:8, 9፤ 72:7, 8, 16፤ ኢሳይያስ 35:5, 6፤ 65:21-23፤ ማቴዎስ 5:5፤ ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 21:4። እነዚህ ጥቅሶች ጦርነት፣ ረሃብ፣ በሽታና ሞት እንደሚቀሩ ይተነብያሉ። በተጨማሪም ጥሩ ሰዎች የራሳቸውን ቤቶች የሚሠሩበት፣ የራሳቸውን መሬት የሚያለሙበትና ከስጋት ነፃ በሆነ ሁኔታ ልጆቻቸውን ማሳደግ የሚችሉበት ጊዜ እንደሚመጣ ጥቅሶቹ ይናገራሉ። * ታዲያ ይህ ተስፋ በሚፈጸምበት ጊዜ መኖር አትፈልግም? እነዚህ ተስፋዎች በቅርቡ እውን እንደሚሆኑ ለማመን በቂ ምክንያት አለን።

አምላክ ብዙ ነገር አድርጎልሃል

አምላክ ለአንተና ለመላው የሰው ዘር ያደረገውን ነገር ሁሉ ቆም ብለህ ብታስብ ቀድሞውንም ቢሆን በጣም ብዙ ነገሮችን እንዳደረገልህ ትረዳለህ። ለምሳሌ ሕይወት፣ የማሰብ ችሎታ፣ አንጻራዊ ጤንነትና በሕይወት ለመቀጠል የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሰጥቶናል። ከዚህ ሁሉ የሚበልጠው ግን ከዮሐንስ 3:16 እንደተረዳነው አምላክ፣ ለእኛ ሲል በሞተው በኢየሱስ አማካኝነት ያዘጋጀው የቤዛ ስጦታ ነው፤ ይህ ስጦታ ብዙ በረከቶችን አስገኝቶልናል።

ሕመም፣ ጦርነት፣ ረሃብ ወይም ሞት በሌለበት ሰላማዊና አስደሳች ዓለም ውስጥ ለዘላለም መኖር፣ ማለቂያ የሌለው ደስታና በረከቶችን እንደሚያስገኝ ጥርጥር የለውም። ይሁንና እነዚያን በረከቶች ማግኘት አለማግኘትህ ሙሉ በሙሉ የተመካው በአንተ ላይ ነው። አሁን መልስ የሚያሻው ‘አንተስ ለአምላክ ምን እያደረግህለት ነው?’ የሚለው ጥያቄ ነው።

^ አን.24 እነዚህን ትንቢቶች በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ተመልከት።