በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ወደ አምላክ ቅረብ

“እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ”

“እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ”

አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ጤንነታችሁ ተጠብቆ ረጅም ዕድሜ ብትኖሩ ደስ አይልህም? ሥቃይ፣ መከራና ሞት የተረሱ ነገሮች በሚሆኑበት ዓለም ውስጥ ለመኖርስ ትናፍቃለህ? እንዲህ ዓይነቱ ዓለም ቅዠት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም በቅርቡ እውን ይሆናል፤ ምክንያቱም ይህ እንደሚሆን ይሖዋ ቃል ገብቷል። በራእይ 21:3-5 (ጥቅሱን አንብብ) ላይ የይሖዋ ዓላማ እንዴት እንደተገለጸ ልብ በል።

“[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል።” (ራእይ 21:4) አምላክ የሚጠርገው ምን ዓይነት እንባ ነው? የደስታ እንባን ወይም ደግሞ ዓይናችንን ከጉዳት የሚከላከለውን እንባ አይደለም። እዚህ ተስፋ ላይ የተጠቀሰው በመከራና በሐዘን ምክንያት የሚመጣው እንባ ነው። አምላክ ይህን የሚያደርገው እንዲሁ እንባን በማድረቅ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ሳንፈልግ እንድናነባ የሚያደርጉንን ነገሮች ይኸውም መከራንና ሐዘንን ጨርሶ በማስወገድ ነው።

“ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም።” (ራእይ 21:4) ጠላት ከሆነው ሞት የበለጠ የሐዘን እንባ እንድናነባ የሚያደርግ ምን ነገር ይኖራል? ይሖዋ ታዛዥ የሆኑትን የሰው ልጆች ከሞት መዳፍ ያላቅቃቸዋል። እንዴት? የሞትን ዋነኛ መንስኤ ማለትም ከአዳም የወረስነውን ኃጢአት በማጥፋት ነው። (ሮም 5:12) ይሖዋ፣ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ታዛዥ የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና ደረጃ ያደርሳቸዋል። * ከዚያም “የመጨረሻው ጠላት የሆነው ሞት ይደመሰሳል።” (1 ቆሮንቶስ 15:26) ከዚያ በኋላ ታማኝ የሆኑ ሰዎች አምላክ ለእነሱ ባለው ዓላማ መሠረት ማለትም ፍጹም ጤንነት ኖሯቸው ዘላለም ይኖራሉ።

“ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።” (ራእይ 21:4) ለመሆኑ ምን ዓይነት ሥቃይ ነው የማይኖረው? ኃጢአተኞችና ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን ሳቢያ የሚመጣውና በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት መራራ ያደረገው አእምሯዊ፣ ስሜታዊ እንዲሁም አካላዊ ሥቃይ አይኖርም።

እንባ፣ ሞትና ሥቃይ የሌሉበት ዓለም በቅርቡ ይመጣል። ‘ግን የት?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ‘አምላክ ቃል የገባው በሰማይ ስላለው ሕይወት ይሆን?’ አይደለም። እንዲህ ያልንበትን ምክንያት እስቲ እንመልከት። አንደኛ፣ ስለ ተስፋው የሚናገረው ጥቅስ የሚጀምረው “የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው” በሚሉት ቃላት ሲሆን ሰዎች የሚኖሩት ደግሞ በምድር ላይ ነው። (ራእይ 21:3) ሁለተኛ፣ ጥቅሱ “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም” ይላል፤ በዚያ ዓለም ውስጥ “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም” ሊባል የሚችለው ከዚህ በፊት ሞት ከነበረ ብቻ ነው። ሞት በሰማይ ኖሮ አያውቅም፤ በምድር ላይ ግን ለረጅም ዘመናት ኖሯል። እንግዲያውስ ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አምላክ የተሻለ ሕይወት እንደሚያመጣ የሰጠው ተስፋ የሚፈጸመው በዚህችው ምድር ላይ ነው።

አምላክ በመከራና በሐዘን ሳቢያ እንደ ጎርፍ የሚወርደውን እንባ ያደርቃል

ይሖዋ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ በገባው ተስፋ ላይ እምነት እንድንጥል ይፈልጋል። ወደፊት የሚመጡትን በረከቶች ከገለጸ በኋላ ቀጠል አድርጎ “እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” በማለት ማረጋገጫ ሰጥቷል። አክሎም “እነዚህ ቃላት እምነት የሚጣልባቸውና እውነት” መሆናቸውን ተናግሯል። (ራእይ 21:5) አንተና የምትወዳቸው ሰዎች፣ አምላክ ቃል የገባቸው ተስፋዎች ክብራማ ፍጻሜያቸውን በሚያገኙበት ጊዜ ይህን ከሚያዩት የአምላክ ደስተኛ አገልጋዮች መካከል መሆን የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ለምን አትማርም?

በታኅሣሥ ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል

1 ጴጥሮስ 1-5; 2 ጴጥሮስ 1-3; 1 ዮሐንስ 1-5; 2 ዮሐንስ 1-13; 3 ዮሐንስ 1-14; ይሁዳ 1-25ራእይ 1-22

^ አን.5 ስለ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የበለጠ ለማወቅ ከፈለግህ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 5 ተመልከት።