በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክን መውደድ ከባድ እንዲሆን ያደረጉ ውሸቶች

ውሸት 1—አምላክ ስም የለውም

ውሸት 1—አምላክ ስም የለውም

ብዙዎች ምን ብለው ያምናሉ?

“አምላክ ‘የግል’ ስም አለው ብለን መናገር እንችል እንደሆነ፣ ስም ካለው ደግሞ ያ ስም ማን እንደሆነ ስምምነት ላይ አልደረስንም።”—ፕሮፌሰር ዴቪድ ከኒንግሀም፣ ቲኦሎጂካል ስተዲስ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እውነት

አምላክ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው።” (ኢሳይያስ 42:8) * ይሖዋ ወይም ያህዌ የሚለው የዕብራይስጥ ስም “ይሆናል” የሚል ትርጉም አለው።—ዘፍጥረት 2:4

ይሖዋ በስሙ እንድንጠቀም ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ስሙንም ጥሩ፤ ያደረገውንም በአሕዛብ መካከል አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ከፍ ማለቱንም ዐውጁ።”ኢሳይያስ 12:4

ኢየሱስ በአምላክ ስም ተጠቅሟል። ኢየሱስ ወደ ይሖዋ ሲጸልይ “ስምህን ለእነሱ [ለደቀ መዛሙርቱ] አሳውቄአለሁ፤ ደግሞም አሳውቃለሁ” ብሏል። ኢየሱስ መለኮታዊውን ስም ለደቀ መዛሙርቱ ያሳወቀው ለምንድን ነው? ምክንያቱን ሲገልጽ “እኔን የወደድክበትን ፍቅር እነሱም እንዲያንጸባርቁ እንዲሁም እኔ ከእነሱ ጋር አንድነት እንዲኖረኝ” ብሏል።—ዮሐንስ 17:26

ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?

የሥነ መለኮት ምሁር የሆኑት ዎልተር ሎውሪ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “የአምላክን ስም የማያውቅ ሰው፣ የአምላክን ማንነት ያውቃል ማለት አይቻልም፤ ይህ ሰው አምላክን የሚመለከተው፣ የራሱ ማንነት እንደሌለው ኃይል አድርጎ ከሆነ እሱን ሊወደው አይችልም።”

ቪክቶር የሚባል አንድ ሰው በየሳምንቱ ቤተ ክርስቲያን ይሄድ የነበረ ቢሆንም አምላክን እንደሚያውቀው አይሰማውም ነበር። ቪክቶር እንዲህ ብሏል፦ “የአምላክ ስም፣ ይሖዋ እንደሆነ ስማር ግን ከእሱ ጋር እንደተዋወቅሁ ሆኖ ተሰማኝ። ብዙ ሲወራለት ከሰማሁት አካል ጋር በመጨረሻ የተገናኘሁ ያህል ነበር። አምላክ እውን ሆነልኝ፤ ከእሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረትም ቻልኩ።”

ይሖዋም ስሙን የሚጠቀሙ ሰዎችን ወደ እሱ ያቀርባቸዋል። አምላክ ‘ስሙን የሚያከብሩ’ ሰዎችን በሚመለከት “አባት የሚያገለግለውን ልጁን እንደሚታደግ ሁሉ እኔም እታደጋቸዋለሁ” በማለት ቃል ገብቷል። (ሚልክያስ 3:16, 17) በተጨማሪም አምላክ ስሙን የሚጠሩ ሰዎችን ወሮታ ይከፍላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ይላል።—ሮም 10:13

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 የአዲሱ መደበኛ ትርጉም መቅድም፣ “መለኮታዊው ስም” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር እንዲህ ይላል፦ “‘ያህዌ’ [LORD] ለሚለው ስም . . . ‘እግዚአብሔር’ የሚለው መጠሪያ ትክክለኛ ምትክ ሆኖ በመገኘቱ የሆሄያቱ አጣጣል ወይም ቅርጽ ‘እግዚአብሔር’ የሚለውን መልክ እንዲይዝ ተደርጓል።”