በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ባለ ታሪኮች ስማቸው ያልተጠቀሰው ለምንድን ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ባለ ታሪኮች ስማቸው ያልተጠቀሰው ለምንድን ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የሩት መጽሐፍ ውስጥ የሙሴ ሕግ የሚያዝዘውን ግዳጅ ለመፈጸም ፈቃደኛ ያልሆነ አንድ ሰው የተገለጸ ሲሆን ይህ ሰው በስም አልተጠቀሰም። (ሩት 4:1-12) ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስማቸው ያልተጠቀሰ ባለ ታሪኮች በሙሉ ልክ እንደዚህ ሰው መጥፎ ናቸው ማለት ነው? ወይም ስማቸው ያልተገለጸው ያን ያህል ቦታ ስላልተሰጣቸው ነው?

በፍጹም። እስቲ ሌላ ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ ፋሲካን ለማክበር ዝግጅት ሲያደርግ ደቀ መዛሙርቱ ‘ወደ ከተማ ሄደው እገሌ የተባለን ሰው’ እንዲያነጋግሩና ለበዓሉ የሚያስፈልጉትን ነገሮች በቤቱ እንዲያዘጋጁ አዟቸው ነበር። (ማቴዎስ 26:18) እዚህ ላይ “እገሌ” ተብሎ የተጠቀሰው ግለሰብ በስም ያልተጠራው መጥፎ ሰው ስለነበረ ወይም ያን ያህል ቦታ ስላልተሰጠው እንደሆነ አድርገን ማሰብ ይኖርብናል? በጭራሽ፤ እዚህ ላይ የተጠቀሰው ሰው የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንደነበረ ጥርጥር የለውም። ይሁንና ስሙ ከዘገባው ጋር ምንም ዝምድና ስለሌለው ሳይጠቀስ ቀርቷል።

ከዚህም በተጨማሪ ክፉ ሆነው በስም የተጠቀሱ በርካታ ግለሰቦች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ታማኝ ቢሆኑም ስማቸው ያልተጠቀሰ ብዙ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የመጀመሪያዋ ሴት ሔዋን፣ ስሟ በሰፊው ይታወቃል። ሆኖም ራስ ወዳድና ዓመፀኛ መሆኗ አዳም ኃጢአት እንዲሠራ አስተዋጽኦ አድርጓል፤ ይህ ደግሞ በሁላችንም ላይ ከባድ መዘዝ አስከትሏል። (ሮም 5:12) በአንጻሩ ደግሞ የኖኅ ሚስት ስሟ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አልተጠቀሰም፤ ይሁን እንጂ ባሏ በጣም አስፈላጊ የሆነ ሥራ ሲያከናውን የራሷን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግና ታዛዥ በመሆን እሱን ስለደገፈችው ልትመሰገን ይገባል። ስሟ አለመጠቀሱ ምንም ቦታ እንዳልተሰጣት ወይም የአምላክን ሞገስ ማጣቷን እንደማያመለክት ግልጽ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ቁልፍ ሚና የተጫወቱ አልፎ ተርፎም የጀግንነት ተግባር የፈጸሙ ስማቸው ያልተጠቀሰ የሌሎች በርካታ ሰዎችን ታሪክ ይዟል። የሶርያ የጦር አዛዥ በሆነው በንዕማን ቤት አገልጋይ የነበረችውን እስራኤላዊት ልጅ ማስታወስ ይቻላል። እመቤቷ ለሆነችው ለንዕማን ሚስት በእስራኤል ስለነበረው የይሖዋ ነቢይ በድፍረት ተናግራለች። ይህ ደግሞ አንድ ትልቅ ተአምር እንዲፈጸም ምክንያት ሆኗል። (2 ነገሥት 5:1-14) የእስራኤላዊው መስፍን የዮፍታሔ ልጅም አስደናቂ የሆነ የእምነት ምሳሌ ትታለች። አባቷ የገባውን ስዕለት ለመፈጸም ስትል ባል የማግባትና ልጆች የመውለድ አጋጣሚዋን መሥዋዕት አድርጋለች። (መሳፍንት 11:30-40) በተመሳሳይም ስማቸው ያልተጠቀሰ ከ40 የሚበልጡ የመዝሙር መጽሐፍ ጸሐፊዎችና ከፍተኛ ኃላፊነቶችን በታማኝነት የተወጡ ነቢያት ይገኛሉ።—1 ነገሥት 20:37-43

ምናልባትም ከዚህ ይበልጥ የሚያስደንቀው ታማኝ መላእክት የተዉት ምሳሌ ነው። በብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መላእክት ቢኖሩም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስም የተጠቀሱት ሁለቱ ማለትም ገብርኤልና ሚካኤል ብቻ ናቸው። (ዳንኤል 7:10፤ ሉቃስ 1:19፤ ይሁዳ 9) የተቀሩት ግን ስማቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተገለጸም። ለምሳሌ ያህል፣ የሳምሶን አባት የሆነው ማኑሄ ወደ እሱ የመጣውን መልአክ “የተናገርኸው ሲፈጸም እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠይቆት ነበር። ታዲያ መልአኩ ምን መለሰለት? ‘ስሜን ለምን ትጠይቃለህ?’ ብሎት ነበር። መልአኩ ልኩን የሚያውቅ በመሆኑ ለአምላክ ብቻ የሚገባውን ክብር ለራሱ ለመውሰድ አልፈለገም።—መሳፍንት 13:17, 18

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንዳንዶቹን በስም ጠቅሶ ሌሎቹን የማይጠቅስበትን ምክንያት አያብራራም። ይሁን እንጂ ዝና ወይም እውቅና ለማግኘት ሳያስቡ አምላክን በታማኝነት ካገለገሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጹ ባለ ታሪኮች ብዙ ነገር መማር እንችላለን።