በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት

አምላክ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው መከራ ያሳስበዋል?

አምላክ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው መከራ ያሳስበዋል?

የይሖዋ ምሥክሮች ከሰዎች ጋር ምን ዓይነት ውይይት እንደሚያደርጉ የሚያሳይ ምሳሌ ከዚህ በታች ቀርቧል። ዮሐና የምትባል አንዲት የይሖዋ ምሥክር ከቤት ወደ ቤት ስትሰብክ ሐና የምትባል ሴት እንዳገኘች አድርገን እናስብ።

አምላክ እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዲደርስ ለምን ይፈቅዳል?

ዮሐና፦ ጤና ይስጥልኝ፣ በዚህ አካባቢ ለሚገኙ ሰዎች ይህን ትራክት እያሰራጨሁ ነው። ርዕሱ እውነቱን ማወቅ ትፈልጋለህ? ይላል። ወስደሽ ልታነቢው ትችያለሽ።

ሐና፦ ስለ ሃይማኖት ነው?

ዮሐና፦ አዎ፣ በሽፋኑ ላይ የተዘረዘሩትን ስድስት ጥያቄዎች ልብ አልሻቸው? ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል . . .

ሐና፦ አይ፣ ይቅርብኝ፤ ጊዜሽን አላባክንብሽ።

ዮሐና፦ እንዲህ ያልሽበትን ምክንያት ልትነግሪኝ ትችያለሽ?

ሐና፦ ይቅርታ አድርጊልኝና እኔ አምላክ መኖሩን እንኳ እጠራጠራለሁ።

ዮሐና፦ ስሜትሽን በግልጽ ስለነገርሽኝ ደስ ብሎኛል። እስቲ አንድ ነገር ልጠይቅሽ፦ ከበፊቱም እንዲሁ ነበር የሚሰማሽ?

ሐና፦ አይ፣ ልጅ እያለሁ ቤተ ክርስቲያን እሄድ ነበር። አሁን ግን ቤተ ክርስቲያን ከሄድኩ በጣም ቆይቻለሁ።

ዮሐና፦ አሃ፣ ይኸውልሽ የእኔ እህት፣ እኔ የማምንበትን ነገር እንድትቀበዪኝ ልጫንሽ አልፈልግም። ግን እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ያደረግሽበትን ምክንያት ባውቅ ደስ ይለኛል። አምላክ መኖሩን እንድትጠራጠሪ ያደረገሽ ነገር አለ?

ሐና፦ አዎ። የዛሬ 17 ዓመት እናቴ የመኪና አደጋ ደርሶባት ነበር።

ዮሐና፦ በጣም ያሳዝናል፤ ከባድ ጉዳት ደረሰባት?

ሐና፦ አዎ፣ ከአደጋው በኋላ ሽባ ሆናለች።

ዮሐና፦ እንዴት ያሳዝናል! መቼም ሁኔታው ጎድቶሽ መሆን አለበት።

ሐና፦ በጣም፤ በዚያ ላይ ደግሞ ‘አምላክ ካለ እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዲደርስ ለምን ይፈቅዳል? አምላክ ይህ ሁሉ መከራ ሲደርስብን ዝም ብሎ የሚመለከተው ለምንድን ነው?’ የሚሉት ጥያቄዎች ከአእምሮዬ ሊወጡ አልቻሉም።

‘ለምን’ ብሎ መጠየቅ ስህተት ነው?

ዮሐና፦ እንዲህ የሚሰማሽ መሆኑ እንዲሁም እንደ እነዚህ ያሉ ጥያቄዎች በአእምሮሽ መጉላላታቸው ምንም ስህተት የለውም። መከራ ሲደርስብን ‘ይህ የደረሰብኝ ለምንድን ነው?’ ብሎ ማሰብ ያለ ነገር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ታማኝ ሰዎችም እንኳ እንዲህ ያለ ጥያቄ ተፈጥሮባቸው ነበር!

ሐና፦ እውነትሽን ነው?

ዮሐና፦ ለምን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንዳንድ ምሳሌዎችን አላሳይሽም?

ሐና፦ ደስ ይለኛል።

ዮሐና፦ በዕንባቆም ምዕራፍ 1 ቁጥር 2 እና 3 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ጥቅስ ልብ በይ። ታማኝ ነቢይ የሆነው ዕንባቆም አምላክን እንዲህ ብሎ ጠይቆት ነበር፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ለርዳታ እየተጣራሁ፣ አንተ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ‘ግፍ በዛ’ ብዬ እየጮኽሁ፣ አንተ የማታድነው እስከ መቼ ነው? ስለ ምን በደልን እንዳይ አደረግኸኝ?” እነዚህ ጥያቄዎች አንቺ ካነሳሻቸው ጥያቄዎች ጋር አይመሳሰሉም?

ሐና፦ አዎ፣ ይመሳሰላሉ።

ዮሐና፦ ዕንባቆም እነዚህን ጥያቄዎች በመጠየቁ አምላክ አልተቆጣውም፤ ወይም እምነት እንደሚጎድለው አልነገረውም።

ሐና፦ እህም፣ የሚገርም ነው።

ይሖዋ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው መከራ ያሳዝነዋል

ዮሐና፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ የሚደርስብንን ሥቃይ እንደሚመለከትና ነገሩ እንደሚያሳስበው ይናገራል።

ሐና፦ ምን ማለትሽ ነው?

ዮሐና፦ አንድ ምሳሌ ልስጥሽ፤ እስቲ በዘፀአት 3:7 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ እንመልከት። ጥቅሱን ታነቢዋለሽ?

ሐና፦ እሺ፤ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር፣ እንዲህ አለ ‘በግብፅ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ።’”

ዮሐና፦ አመሰግንሻለሁ። በዚህ ጥቅስ መሠረት አምላክ በሕዝቦቹ ላይ የሚደርሰውን መከራ የሚመለከት ይመስልሻል?

 ሐና፦ አዎ፣ ይመስላል።

ዮሐና፦ ደግሞም አምላክ፣ ሕዝቦቹ ስለሚደርስባቸው መከራ የሚያውቀው ነገር እንዲሁ ላይ ላዩን እንዳልሆነ ልብ በዪ። በጥቅሱ መጨረሻ ላይ ያለውን ሐሳብ እስቲ በድጋሚ ተመልከቺ። አምላክ “ሥቃያቸውንም ተረድቻለሁ” ብሏል። እንዲህ ብሎ የተናገረው አምላክ፣ የሕዝቦቹ ሁኔታ የማያሳስበው ወይም ችግራቸውን የማይረዳ ነው ሊባል ይችላል?

ሐና፦ አይመስለኝም።

ዮሐና፦ አምላክ የሚደርስብንን መከራ ከማየት ባለፈ በደረሰው ነገር ስሜቱ ይነካል ወይም ያዝናል ማለት ነው፤ አይደል?

ሐና፦ እውነት ነው።

ዮሐና፦ ይህን በአእምሯችን ይዘን፣ የአምላክ ሕዝቦች ሥቃይ በደረሰባቸው ወቅት አምላክ ምን እንደተሰማው የሚገልጽ ሌላ ምሳሌ እንመልከት። ታሪኩ በኢሳይያስ 63:9 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። የጥቅሱ የመጀመሪያ ክፍል “በጭንቃቸው ሁሉ ተጨነቀ” ይላል። ታዲያ በሕዝቦቹ ላይ የደረሰው መከራ የአምላክንም ስሜት ነክቶታል ማለት አንችልም?

ሐና፦ ጥቅሱ ይህን የሚያሳይ ይመስላል።

ዮሐና፦ እንደ እውነቱ ከሆነ አምላክ ስለ እኛ በጣም ያስባል፤ እንዲሁም ስንሠቃይ ማየት ያሳዝነዋል። እኛ ስንሠቃይ እሱም ከእኛ ጋር ይሠቃያል።

ታዲያ አምላክ እስከ አሁን መከራን ያላስወገደው ለምንድን ነው?

ዮሐና፦ ላካፍልሽ የምፈልገው ሌላም ሐሳብ አለ።

ሐና፦ እሺ።

ዮሐና፦ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ኃይል ምን እንደሚል እንመልከት። እንድናነበው የምፈልገው ጥቅስ ኤርምያስ 10:12 ነው። ልታነቢው ትችያለሽ?

ሐና፦ እሺ፣ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር ግን ምድርን በኀይሉ ፈጠረ፤ ዓለምን በጥበቡ መሠረተ፤ ሰማያትንም በማስተዋሉ ዘረጋ።”

ዮሐና፦ አመሰግናለሁ። እስቲ ይህ ጥቅስ ምን ትርጉም እንዳለው አስቢ። አምላክ ግዙፉን አጽናፈ ዓለምና በውስጡ ያለውን ሁሉ ለመፍጠር ታላቅ ኃይል አስፈልጎታል ቢባል አትስማሚም?

ሐና፦ ምን ጥያቄ አለው!

ዮሐና፦ ታዲያ አምላክ በዙሪያችን ያለውን ነገር ሁሉ ለመፍጠር የሚያስችል ኃይል ካለው የፈጠራቸውን ነገሮች ሁሉ ለመቆጣጠር የሚያስችል ኃይል የሚኖረው አይመስልሽም?

ሐና፦ አዎ፣ ይኖረዋል።

ዮሐና፦ እስቲ መለስ ብለሽ ስለ እናትሽ አስቢ። እናትሽ ስትሠቃይ ማየት የሚረብሽሽ ለምንድን ነው?

ሐና፦ ስለምወዳት ነዋ! እናቴ አይደለች እንዴ?

ዮሐና፦ እናትሽ እንድትድን ማድረግ ብትችዪ ምን ታደርጊ ነበር?

ሐና፦ ወዲያውኑ አድናት ነበር!

ዮሐና፦ እስቲ ይህን ጉዳይ ከአምላክ አንጻር እንመልከተው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ሥቃያችንን እንደሚመለከት፣ እኛ ስንሠቃይ እሱም እንደሚሠቃይ እንዲሁም ከፍተኛ ኃይል እንዳለው ያስተምራል። ይሁንና አምላክ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን መከራ ወዲያውኑ ለማስወገድ ጣልቃ አልገባም፤ ይህ ታዲያ ምን ያህል ራሱን መቆጣጠር እንደጠየቀበት መገመት ትችያለሽ?

ሐና፦ ከዚህ በፊት እንደዚህ አስቤ አላውቅም።

ዮሐና፦ አምላክ ጣልቃ ገብቶ ችግሮቻችንን ያላስቆመው በቂ ምክንያት ስላለው ይሆን? *

ሐና፦ እህም፣ እውነትም በቂ ምክንያት ቢኖረው ይመስለኛል።

ዮሐና፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይህን በተመለከተ ምን እንደሚል ሌላ ጊዜ ተመልሼ ላወያይሽ እችላለሁ። በሚቀጥለው ሳምንት በዚሁ ሰዓት ብመጣ ይመችሻል?

ሐና፦ አዎ፣ ታገኚኛለሽ።

ዮሐና፦ ጥሩ፣ በነገራችን ላይ እኔ ዮሐና እባላለሁ።

ሐና፦ እኔ ደግሞ ሐና እባላለሁ።

ዮሐና፦ እሺ ሐና፣ በሚቀጥለው ሳምንት እንገናኝ። *

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የተያያዘ ግራ የሚያጋባህ ነገር አለ? የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያምኑባቸው ነገሮች ወይም ስለ ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው ለማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ስትገናኝ ጥያቄህን ከማቅረብ ወደኋላ አትበል። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከአንተ ጋር መወያየት ያስደስታቸዋል።

^ አን.57 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ተመልከት።

^ አን.63 አምላክ መከራን የፈቀደው ለምን እንደሆነ ወደፊት በዚህ ዓምድ ሥር በሚወጣ ርዕስ ላይ ይብራራል።