የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
ለዘላለም መኖር ይቻላል?
የመጀመሪያው ሰው አዳም ብዙ መቶ ዓመታት ኖሯል። ውሎ አድሮ ግን አርጅቶ መሞቱ አልቀረም። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ሰዎች እርጅናን ለማስቀረት የተለያዩ ዘዴዎችን ሲሞክሩ ቆይተዋል። ሆኖም ከሞት ማምለጥ የቻለ ማንም የለም። ለምን? ምክንያቱም አዳም አርጅቶ የሞተው የአምላክን ትእዛዝ ጥሶ ኃጢአት በመሥራቱ ነው። እኛም ከአዳም ኃጢአትንና የኃጢአት ቅጣት የሆነውን ሞትን ስለወረስን እናረጃለን።—ዘፍጥረት 5:5ን እና ሮም 5:12ን አንብብ።
የሰው ዘሮች ለዘላለም መኖር እንዲችሉ ቤዛ የሚከፍልላቸው ሰው ያስፈልጋቸዋል። (ኢዮብ 33:24, 25) ቤዛ ማለት አንድን ሰው ነፃ ለማውጣት የሚከፈል ካሳ ነው፤ እኛም ከሞት ነፃ መውጣት ያስፈልገናል። (ዘፀአት 21:29, 30) ኢየሱስ ስለ እኛ በመሞት ቤዛውን ከፍሎልናል።—ዮሐንስ 3:16ን አንብብ።
የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
ከበሽታና ከእርጅና ነፃ የሚወጣው ሁሉም ሰው አይደለም። እንዲያውም እንደ አዳም አምላክን የማይታዘዙ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ማግኘት አይችሉም። የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት ኃጢአታቸው ይቅር የተባለላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው።—ኢሳይያስ 33:24ን እና 35:3-6ን አንብብ።
ይቅርታ ለማግኘት ደግሞ ልንወስደው የሚገባ እርምጃ አለ። የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት አምላክን ማወቅ ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከሁሉ የተሻለ ሕይወት መምራት እንዲሁም የአምላክን ሞገስና የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል።—ዮሐንስ 17:3ን እና የሐዋርያት ሥራ 3:19ን አንብብ።