በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጦርነት—ሃይማኖቶችን ልትተማመንባቸው ትችላለህ?

ጦርነት—ሃይማኖቶችን ልትተማመንባቸው ትችላለህ?

አልቤርቶ በጦር ሠራዊት ውስጥ ለአሥር ዓመታት ያህል አገልግሏል። እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “ቄሳችን ‘አምላክ ከእናንተ ጋር ነው’ በማለት ባረኩን። ቄሱ እንዲህ ሲያደርጉ ‘መጽሐፍ ቅዱስ “አትግደል” ይላል፤ እኔ ግን ለመግደል እየሄድኩ ነው’ የሚለው ሐሳብ በአእምሮዬ ይመላለስ ነበር።”

ሬይ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በባሕር ኃይል ውስጥ አገልግሏል። በአንድ ወቅት ሬይ፣ የወታደሮቹን ቄስ “እርስዎ ወደ መርከቡ መጥተው ሠራዊታችን ድል እንዲያገኝ ይጸልዩልናል። ጠላቶቻችንስ እንዲህ ያደርጉ የለ?” በማለት ጠየቃቸው። ቄሱም የጌታ አሠራር ሚስጥራዊ እንደሆነ ነገሩት።

እንዲህ ዓይነቱ መልስ አጥጋቢ እንዳልሆነ ይሰማሃል? ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል?

ኢየሱስ ከታላላቆቹ የአምላክ ትእዛዛት መካከል አንዱ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል እንደሆነ ተናግሯል። (ማርቆስ 12:31) ይሁንና ኢየሱስ፣ ባልንጀራችንን እንድንወድ የተሰጠው ትእዛዝ ባልንጀራ የተባለው ሰው በሚኖርበት ቦታ ወይም በዜግነቱ ላይ የተመካ እንደሆነ ገልጿል? በፍጹም። ለደቀ መዛሙርቱ “በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 13:34, 35) በመካከላቸው ያለው ፍቅር በጣም አስደናቂ ከመሆኑ የተነሳ በፍቅራቸው ተለይተው ይታወቃሉ። ክርስቲያኖች ፈጽሞ የሰዎችን ሕይወት አያጠፉም፤ እንዲያውም አንዳቸው ለሌላው ሕይወታቸውን አሳልፈው ለመስጠት ፈቃደኞች ናቸው።

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ከተናገረው ሐሳብ ጋር በሚስማማ መንገድ ተመላልሰዋል። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን እንደሚከተለው ይላል፦ “ተርቱሊያንንና ኦሪጀንን ጨምሮ የቀድሞዎቹ የቤተ ክርስቲያን አባቶች እንዳረጋገጡት ክርስቲያኖች ሰው አይገድሉም፤ በሮማውያን የጦር ሠራዊት ውስጥ የማይካተቱትም በዚህ ምክንያት ነበር።”

ስለ ይሖዋ ምሥክሮችስ ምን ማለት ይቻላል?

የይሖዋ ምሥክሮች በሁሉም አገሮች ይኖራሉ ማለት ይቻላል፤ በመሆኑም በሁለት አገሮች መካከል ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ በሁለቱም ቦታዎች የይሖዋ ምሥክሮች መኖራቸው አይቀርም። ያም ቢሆን እነዚህ ክርስቲያኖች መለያቸው የሆነውን ፍቅር ለማሳየት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።

የሃይማኖት መሪዎች፣ ሰዎች እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅር እንዲያሳዩ አስተምረዋል?

ለምሳሌ ያህል፣ በ1994 በሩዋንዳ በሁቱና በቱትሲ ጎሣዎች መካከል በነበረው ግጭት ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ፈጽሞ አልተካፈሉም። የአንደኛው ጎሣ አባላት የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የሌላው ጎሣ አባላት የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮችን ይደብቁ ነበር፤ ብዙውን ጊዜ ይህን የሚያደርጉት ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ነው። በአንድ ወቅት፣ ቱትሲ ወንድሞቻቸውን አስጠግተው የነበሩ ሁለት ሁቱ የይሖዋ ምሥክሮች ኢንተራሃምዌ በተባሉት የሁቱ ወታደሮች ተያዙ፤ ወታደሮቹ “ቱትሲዎች እንዲያመልጡ ስለረዳችሁ መሞት አለባችሁ” አሏቸው። የሚያሳዝነው ነገር፣ ሁለቱም ሁቱ የይሖዋ ምሥክሮች ተገደሉ።—ዮሐንስ 15:13

ታዲያ ምን ይመስልሃል? የይሖዋ ምሥክሮች፣ ኢየሱስ የጠቀሰውን የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን የሚጠይቀውን ፍቅር እያሳዩ እንደሆነ ይሰማሃል?