ገንዘብ—ሃይማኖቶችን ልትተማመንባቸው ትችላለህ?
ኤስቴል * ከልጆቿ ጋር አዘውትራ ወደ ቤተ ክርስቲያን ትሄድ ነበር። “መጽሐፍ ቅዱስን መማር እንደምፈልግ ለቄሱ ነገርኩት” ትላለች። እሱ ግን ምንም ምላሽ አልሰጣትም። በመጨረሻም ኤስቴል ቤተ ክርስቲያን መሄዷን አቆመች። እንዲህ ብላለች፦ “የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለሥልጣናት ደብዳቤ የጻፉልኝ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን መምጣት ባልችል እንኳ ገንዘብ እንድልክ ጠየቁኝ። እኔም ‘ቤተ ክርስቲያን ብሄድ ባልሄድ ግድ የላቸውም፤ የሚፈልጉት ገንዘቤን ብቻ ነው’ ብዬ አሰብኩ።”
ሃይማኖተኛ የሆነችው አንጌሊና ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “በምሄድበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በእያንዳንዱ የአምልኮ ሥርዓት ወቅት ገንዘብ መሰብሰቢያው ሦስት ጊዜ ይዞር ነበር፤ እኛም በእያንዳንዱ ዙር እንድንሰጥ ይጠበቅብናል። ገንዘብ እንድንሰጥ ሁልጊዜ እንደወተወቱን ነው። በመሆኑም ‘እነዚህ ሰዎች የአምላክ መንፈስ የላቸውም’ ብዬ አሰብኩ።”
በአካባቢህ ያሉት ሃይማኖቶች ሰዎች ገንዘብ እንዲሰጡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጫና ያሳድራሉ? ይህስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል?
የክርስትና መሥራች የሆነው ኢየሱስ “በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ” ብሏል። (ማቴዎስ 10:8) የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በዋጋ ሊተመን የማይችል ሲሆን የሚፈልግ ሁሉ በነፃ ሊያገኘው ይገባል።
የጥንቶቹ ክርስቲያኖች፣ ጉባኤው የሚያወጣቸውን ወጪዎች የሚሸፍኑት እንዴት ነበር?
ሁሉም ሰው “ቅር እያለው ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን” ይሰጥ ነበር፤ ምክንያቱም አምላክ የሚወደው “በደስታ የሚሰጠውን ሰው” ነው። (2 ቆሮንቶስ 9:7) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “የአምላክን ምሥራች የሰበክንላችሁ፣ ማናችሁንም ብዙ ወጪ በማስወጣት ሸክም እንዳንሆንባችሁ ብለን ሌት ተቀን እየሠራን ነው።” (1 ተሰሎንቄ 2:9) ጳውሎስ፣ አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ወቅት ለራሱ የሚያስፈልገውን የሚያሟላው ድንኳን በመስፋት ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 18:2, 3
ስለ ይሖዋ ምሥክሮችስ ምን ማለት ይቻላል?
የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባቸውን የሚያደርጉባቸው ቦታዎች የመንግሥት አዳራሾች ተብለው የሚጠሩ ሲሆን እነዚህ አዳራሾች የተንቆጠቆጡ አይደሉም። የይሖዋ ምሥክሮች ወጪዎቻቸውን የሚሸፍኑት እንዴት ነው? ሙዳየ ምፅዋት ፈጽሞ አያዞሩም፤ ወይም ደግሞ ፖስታ በመላክ ሰዎች ገንዘብ እንዲያዋጡ አይጠይቁም። ከዚህ ይልቅ ለሚቀርበው መንፈሳዊ ፕሮግራም አድናቆት ያለው ማንኛውም ሰው በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ በሚገኝ የመዋጮ ሣጥን ውስጥ ገንዘብ መክተት ይችላል።
ሃይማኖቶች ወጪያቸውን መሸፈን የሚኖርባቸው እንዴት ነው?
ይህን መጽሔት ለማተምና ወደተለያዩ ቦታዎች ለማጓጓዝ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው። ያም ቢሆን በመጽሔቱ ላይ የንግድ ማስታወቂያ ወይም ሰዎች መዋጮ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ሐሳብ ፈጽሞ አይወጣም። የይሖዋ ምሥክሮች ዋነኛ ትኩረታቸው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማሰራጨት ነው።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ይህ ዓይነቱ አሠራር ኢየሱስ ከተናገረው እንዲሁም የቀድሞ ክርስቲያኖች ከተዉት ምሳሌ ጋር ይስማማል?
^ አን.2 በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።