በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው

ዓለም አቀፍ ሰላም የሕልም እንጀራ ሆኖ የቀረው ለምንድን ነው?

ዓለም አቀፍ ሰላም ማምጣት የሚችለው የሰዎችን ልብ መለወጥ የሚችል መንግሥት ብቻ ነው

መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት መሠረታዊ ምክንያቶችን ይጠቅሳል። አንደኛው፣ የሰው ልጆች ድንቅ ነገሮችን ያከናወኑ ቢሆንም ራሳቸውን የመምራት ችሎታ አልተሰጣቸውም። ሁለተኛው፣ “መላው ዓለም በክፉው ኃይል” ማለትም በሰይጣን ዲያብሎስ ሥር ስለሆነ ሰዎች የሚያቅዱት ነገር አይሳካም። በመሆኑም የሰዎች ጥረት ዓለም አቀፍ ሰላም ማስገኘት አልቻለም።—ኤርምያስ 10:23ን እና 1 ዮሐንስ 5:19ን አንብብ።

በተጨማሪም ሰዎች ራስ ወዳድና የሥልጣን ጥም የተጠናወታቸው በመሆናቸው ዓለም አቀፍ ሰላም የሕልም እንጀራ እንደሆነ ቀርቷል። በዓለም ላይ ሰላም ሊሰፍን የሚችለው ሰዎች መልካም የሆነውን እንዲወዱና ለሌላው አሳቢነት እንዲያሳዩ የሚያስተምር ዓለም አቀፍ መንግሥት ከተቋቋመ ብቻ ነው።—ኢሳይያስ 32:17ን እና 48:18, 22ን አንብብ።

በምድር ላይ ሰላምን የሚያሰፍነው ማን ነው?

ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ መላውን የሰው ዘር የሚገዛ አንድ መንግሥት እንደሚያቋቁም ቃል ገብቷል። ይህ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን ይተካል። (ዳንኤል 2:44) የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ የሰላም ልዑል በመሆን ይገዛል። ከምድር ላይ ክፋትን ጠራርጎ የሚያስወግድ ከመሆኑም ሌላ ለሰዎች የሰላምን መንገድ ያስተምራል።—ኢሳይያስ 9:6, 7ን እና 11:4, 9ን አንብብ።

ዛሬም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በኢየሱስ አመራር ሥር ሆነው፣ ከሌሎች ጋር እንዴት በሰላም መኖር እንደሚቻል የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም ለሰዎች እያስተማሩ ነው። በቅርቡ ደግሞ ዓለም አቀፍ ሰላም እውን ይሆናል።—ኢሳይያስ 2:3, 4ን እና 54:13ን አንብብ።