ወደ ቅዱሳን መጸለይ ይኖርብናል?
ጭንቀት ያላጋጠመውና የሰው እርዳታ እንደሚያስፈልገው ያልተሰማው ማን አለ? እርግጥ ነው፣ ለእርዳታ የምንመርጠው ሰው እንዳስጨነቀን ሁኔታ ሊለያይ ይችላል፤ ያም ሆኖ የምንሄደው ሁኔታችንን ሊረዳልን ወደሚችልና ስለ ችግሩ ተሞክሮ ወዳለው ወዳጃችን ነው። አንድን ወዳጅ ይበልጥ ተፈላጊ የሚያደርገው የሌላን ሰው ስሜት መረዳት መቻሉና ተሞክሮ ያለው መሆኑ ነው።
ከጸሎት ጋር በተያያዘም አንዳንዶች ተመሳሳይ ስሜት ይሰማቸው ይሆናል። አምላክ እጅግ ከፍ ያለና በጣም የሚያስፈራ መስሎ ስለሚታያቸው በቀጥታ ወደ እሱ ከመጸለይ ይልቅ ልመናቸውን ለቅዱሳን ማቅረብ ይመርጣሉ። ቅዱሳን ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎችና መከራዎች ስለቀመሱ ከአምላክ ይልቅ ሩኅሩኆች እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ውድ ዕቃ የጠፋባቸው ሰዎች የጠፉ ወይም የተሰረቁ ዕቃዎችን ያስመልሳል ብለው ወደሚያምኑበት ወደ ፓጁወው “ቅዱስ” አንቶኒ መጸለይ ይመርጡ ይሆናል። ለታመመ እንስሳ መጸለይ ሲፈልጉ የአሲሲውን “ቅዱስ” ፍራንሲስ ሊመርጡ ይችላሉ፤ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ሲገቡ ደግሞ ወደ “ቅዱስ” ይሁዳ ታዴዎስ ይጸልዩ ይሆናል።
ይሁንና ወደ ቅዱሳን መጸለይ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ተገቢ ስለመሆኑ ወይም ስላለመሆኑ እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ዞሮ ዞሮ ጸሎታችን መድረስ ያለበት ወደ አምላክ ስለሆነ ‘ጸሎታችን በእሱ ዘንድ ተሰሚነት አለው?’ ለሚለው ጥያቄ መልሱን ማወቅ እንደምንፈልግ ጥርጥር የለውም። ደግሞስ ‘ወደ ቅዱሳን ስለ መጸለይ አምላክ ምን ይሰማዋል?’ የሚለውን ጥያቄ መመለስ አይኖርብንም?
ወደ ቅዱሳን ስለ መጸለይ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ወደ ቅዱሳን የመጸለይ ልማድ የተመሠረተው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስለ ቅዱሳን አማላጅነት በምታስተምረው ትምህርት ላይ ነው። ዘ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚገልጸው የዚህ ትምህርት መሠረታዊ ሐሳብ “በአምላክ ፊት ለመቅረብ መብት ያለው ሰው፣ ችግር ላይ ለወደቀ ሰው ምሕረት ለማስገኘት ሲል የሚያቀርበው ልመና” የሚል ነው። በመሆኑም አንድ ሰው ወደ ቅዱሳን የሚጸልየው ቅዱሳኑ በአምላክ ፊት የመቆም ልዩ መብት ስላላቸው በእነሱ አማካኝነት ሞገስ አገኛለሁ ብሎ ተስፋ በማድረግ ነው።
ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱን ትምህርት ያስተምራል? አንዳንዶች፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቅዱሳን ለመጸለይ መሠረት ሆኖ የሚያገለግል ነገር በደብዳቤዎቹ ላይ መግለጹን ይጠቅሳሉ። ለምሳሌ በሮም ለነበሩ ክርስቲያኖች “እንግዲህ ወንድሞች፣ ስለ እኔ ወደ አምላክ በመጸለይ ከእኔ ጋር አብራችሁ እንድትጋደሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና ከመንፈስ በሚገኘው ፍቅር እማጸናችኋለሁ” በማለት ጽፏል። (ሮም 15:30) ታዲያ ጳውሎስ የእምነት አጋሮቹን በአምላክ ፊት አማላጅ እንዲሆኑለት እየጠየቃቸው ነበር? በጭራሽ። እንዲህ ማድረግ ተገቢ ቢሆን ኖሮ ጳውሎስ የክርስቶስ ሐዋርያ በመሆኑ በአምላክ ፊት እንዲያማልዳቸው መጠየቅ ያለባቸው እነሱ ነበሩ። ጳውሎስ ለመግለጽ የፈለገው አንድ የእምነት አጋራችን ወደ አምላክ እንዲጸልይልን መጠየቅ ተገቢ መሆኑን ነው። ይሁን እንጂ ልመናችንን በአምላክ ፊት እንዲያቀርብልን በሰማይ እንደሚኖር ወደሚታመን ሰው መጸለይ ፈጽሞ የተለየ ነገር ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
ሐዋርያው ዮሐንስ በጻፈው ወንጌል ላይ ኢየሱስ “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ። በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:6) በተጨማሪም “አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ [ይሰጣችኋል]” ብሎ ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:16) ኢየሱስ ጸሎታችንን ወደ እሱ እንድናቀርብና ከዚያም እሱ እኛን ወክሎ ለአምላክ እንደሚያቀርብ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ የተናገረው፣ ጸሎታችን እንዲሰማልን ከፈለግን ጸሎታችንን በቀጥታ ወደ አምላክ ማቅረብ እንዳለብንና ይህን ማድረግ ያለብን ደግሞ በሌላ በማንም ሳይሆን በእሱ በኩል መሆን እንዳለበት ነው።
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዴት ብለው መጸለይ እንዳለባቸው እንዲያስተምራቸው በጠየቁት ጊዜ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “በምትጸልዩበት ጊዜ ሁሉ እንዲህ በሉ፦ ‘አባት ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ።’” (ሉቃስ 11:2) አዎን፣ ‘በምንጸልይበት ጊዜ ሁሉ’ ጸሎታችንን ማቅረብ ያለብን ወደ ኢየሱስ ወይም ወደ ሌላ ማንኛውም አካል ሳይሆን ወደ አምላክ ብቻ መሆን አለበት። ምንም ከማያሻሙት ከእነዚህ የኢየሱስ ትምህርቶች አንጻር ጉዳዩን ስንመለከተው ጸሎታችን መቅረብ ያለበት በኢየሱስ በኩል በቀጥታ ወደ አምላክ እንጂ አማላጆች ወይም “ቅዱሳን” ወደሚባሉት አይደለም ከሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳችን ተገቢ አይደለም?
ጸሎት በጣም አስፈላጊ የሆነ የአምልኳችን ክፍል ነው፤ ከአምላክ ውጪ ሌሎች አካላትን ማምለክ ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር እንደማይስማማ ግልጽ ነው። (ዮሐንስ 4:23, 24፤ ራእይ 19:9, 10) ጸሎቶቻችንን ወደ አምላክ ብቻ ማቅረብ የሚኖርብን በዚህ ምክንያት ነው።
አምላክን በጸሎት ለማነጋገር ፍርሃት ሊያድርብህ ይገባል?
ኢየሱስ በዝነኛው የተራራ ስብከቱ ወቅት በጠቀሰው አንድ ምሳሌ ላይ አባቱን የሚበላ ነገር እንዲሰጠው ስለጠየቀ አንድ ልጅ ተናግሮ ነበር። ታዲያ አንድ አባት ለልጁ በዳቦ ፈንታ ድንጋይ ይሰጣል? ወይም ደግሞ በዓሣ ፈንታ እባብ ይሰጣል? (ማቴዎስ 7:9, 10) አፍቃሪ የሆነ አንድ ወላጅ እንዲህ ያደርጋል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው!
እስቲ ምሳሌውን ከወላጅ አንጻር ለማሰብ ሞክር። ልጅህ አንተን መጠየቅ የሚፈልገው አንገብጋቢ ጉዳይ አለው እንበል። ከልጅህ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖር ጥረት ስታደርግ ነበር፤ ደግሞም በቀላሉ የምትቀረብ ዓይነት ሰው ነህ። ያም ሆኖ ልጅህ አንተን በቀጥታ ቢጠይቅህ ስለምትሰጠው ምላሽ መሠረት የሌለው ፍርሃት ስላደረበት ልመናውን ለአንተ እንዲያቀርብለት ሌላ ሰው ይጠይቃል። በዚህ ጊዜ ምን ይሰማሃል? ይባስ ብሎ ከአንተ ጋር የሚያደርገውን የሐሳብ ልውውጥ በሙሉ በዚህ ግለሰብ በኩል ብቻ ማድረጉን ልማድ ቢያደርገውና ለወደፊቱም ቢሆን በዚሁ የመቀጠል ዓላማ እንዳለው ብታውቅ ምን ይሰማሃል? ልጅህ በዚህ መንገድ ከአንተ ጋር የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ በማሰቡ ትደሰታለህ? እንደማትደሰት የተረጋገጠ ነው! አፍቃሪ ወላጆች ልጆቻቸው በቀጥታ ወደ እነሱ በመምጣት የሚፈልጉትን ነገር በነፃነት እንዲጠይቋቸው ይፈልጋሉ።
ኢየሱስ አባቱን የሚበላ ነገር ስለጠየቀው ልጅ የሚናገረውን ምሳሌ ተግባራዊነት በፊቱ ለተሰበሰበው ሕዝብ ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “ታዲያ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት መልካም ነገር አብልጦ አይሰጣቸውም!” (ማቴዎስ 7:11) በእርግጥም አንድ ወላጅ ለልጁ ጥሩ ነገሮችን የመስጠት ከፍተኛ ፍላጎት አለው። የሰማዩ አባታችን የእኛን ጸሎት ሰምቶ ምላሽ ለመስጠት ከዚህ ይበልጥ ፍላጎት እንደሚኖረው ምንም ጥያቄ የለውም።
በሠራነው ስህተት ምክንያት በጭንቀት በምንዋጥበት ጊዜም ጭምር አምላክ በጸሎት በቀጥታ ወደ እሱ እንድንቀርብ ይፈልጋል። ጸሎታችንን እንዲሰሙ ለሌሎች ውክልና አልሰጠም። መጽሐፍ ቅዱስ “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል” በማለት አጥብቆ ይመክረናል። (መዝሙር 55:22) ቅዱሳን ወይም ሌሎች ሰዎች ስለ እኛ ይማልዱልናል ብለን ከምንጠብቅ ስለ ይሖዋ አምላክ አዎንታዊ አመለካከት ማዳበራችን ይበጀናል።
የሰማዩ አባታችን ለእኛ በግለሰብ ደረጃ ያስብልናል። ችግር ሲደርስብን ሊረዳን ይፈልጋል እንዲሁም ወደ እሱ እንድንቀርብ ይጋብዘናል። (ያዕቆብ 4:8) ‘ጸሎት ሰሚ’ ወደሆነው አምላካችንና አባታችን የመቅረብ መብት በማግኘታችን ምንኛ ደስተኞች ነን!—መዝሙር 65:2