በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተፈጥሮ አደጋዎች አምላክ ጨካኝ እንደሆነ ያረጋግጣሉ?

የተፈጥሮ አደጋዎች አምላክ ጨካኝ እንደሆነ ያረጋግጣሉ?

ሰዎች ምን ይላሉ? “አምላክ ዓለምን ስለሚገዛ የተፈጥሮ አደጋዎችን የሚያደርሰው እሱ ነው፤ እንዲህ ማድረጉ ደግሞ ጨካኝ እንደሆነ ያሳያል።”

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “መላው ዓለም ግን በክፉው ኃይል ሥር ነው።” (1 ዮሐንስ 5:19) “ክፉው” የተባለው ማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን እንደሆነ ይገልጻል። (ማቴዎስ 13:19፤ ማርቆስ 4:15) ይህ ሐሳብ ከእውነታው የራቀ ነው? እስቲ የሚከተለውን ለማሰብ ሞክር፦ ዓለም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ከሆነ ሰዎች ልክ እንደ እሱ ራስ ወዳድ፣ ስግብግብ እንዲሁም አርቀው የማያስቡ እንዲሆኑ ተጽዕኖ እንደሚያደርግባቸው የታወቀ ነው። ይህ ደግሞ የሰው ልጆች መኖሪያቸው የሆነችውን ምድር በከፍተኛ ሁኔታ እያበላሿት ያለው ለምን እንደሆነ ግልጽ ያደርግልናል። ሰዎች ምድርን አላግባብ መያዛቸው የተፈጥሮ አደጋዎች እንዲከሰቱ፣ እንዲባባሱ አሊያም በሰዎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዲያደርሱ ዋነኛ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ በርካታ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

ታዲያ ሰይጣን ይህን ያህል ኃይል እንዲኖረው አምላክ የፈቀደው ለምንድን ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት በሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ ላይ የተፈጸመን አንድ ሁኔታ እንመልከት፤ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በአምላክ አገዛዝ ላይ ዓምፀው ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አብዛኛው የሰው ዘር የእነሱን የዓመፀኝነት ጎዳና ተከትሏል። ሰዎች በአምላክ መገዛት አለመፈለጋቸው መላው ዓለም የአምላክ ጠላት በሆነው በዲያብሎስ እጅ እንዲወድቅ አድርጓል። በመሆኑም ኢየሱስ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” በማለት ጠርቶታል። (ዮሐንስ 14:30) ታዲያ ሰይጣን ዓለምን የሚገዛው ለዘላለም ነው? በፍጹም!

ይሖዋ፣ * ሰይጣን በሰው ልጆች ላይ ስለሚያደርሰው መከራ ደንታ የለውም ማለት አይደለም። እንዲያውም አምላክ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው ሥቃይ በጣም ያሳዝነዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በእስራኤል ብሔር ላይ መከራ በመጣበት ወቅት አምላክ “በጭንቃቸው ሁሉ [እንደተጨነቀ]” መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢሳይያስ 63:9) አምላክ በምሕረቱ ተገፋፍቶ የሰይጣንን የጭካኔ አገዛዝ በቅርቡ ወደ ፍጻሜው ለማምጣት ዝግጅት አድርጓል! ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በፍትሕና በጽድቅ የሚያስተዳድር ንጉሥ እንዲሆን ለዘላለም ሾሞታል።

ይህ ለአንተ ምን ትርጉም አለው? የሰይጣን አገዛዝ ሰዎችን ከተፈጥሮ አደጋዎች መጠበቅ ሳይችል ቢቀርም የኢየሱስ አገዛዝ ግን ይህን ማድረግ ይችላል። በአንድ ወቅት ኃይለኛ ማዕበል በተነሳ ጊዜ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለማዳን እርምጃ ወስዶ ነበር። “ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም ‘ጸጥ በል! ረጭ በል!’ አለው። ነፋሱም ቆመ፤ ታላቅ ጸጥታም ሰፈነ” በማለት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይናገራል። ደቀ መዛሙርቱም “‘ለመሆኑ፣ ነፋስና ባሕር እንኳ የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?’ ተባባሉ።” (ማርቆስ 4:37-41) ይህ አጋጣሚ ኢየሱስ እሱ ንጉሥ ሆኖ በሚገዛበት ጊዜ፣ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል።—ዳንኤል 7:13, 14

^ አን.5 የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል።