በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትርጉም ያለው ሕይወት ለመኖር ቁልፉ ኢየሱስ ነው

ትርጉም ያለው ሕይወት ለመኖር ቁልፉ ኢየሱስ ነው

ኢየሱስ በእርግጥ ትርጉም ያለው ሕይወት ኖሯል? ያደገው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፤ ደግሞም በሕይወት ዘመኑ በሙሉ ይህ ነው የሚባል ንብረት አላፈራም። እንዲያውም “ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ቦታ” አልነበረውም። (ሉቃስ 9:57, 58) በተጨማሪም ሰዎች በጥላቻ ዓይን ይመለከቱት እንዲሁም ስሙን ያጠፉ ነበር፤ በመጨረሻም በጠላቶቹ እጅ ተገድሏል።

‘እንዲህ ያለው ሕይወት ትርጉም አለው ብዬ አላስብም?’ ትል ይሆናል። ሆኖም የኢየሱስ ሕይወት ይህ ብቻ አይደለም፤ ለሌላው የሕይወቱ ገጽታም ትኩረት መስጠታችን የተገባ ነው። እስቲ የኢየሱስን ሕይወት አራት ገጽታዎች እንመርምር።

1. ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ የሕይወቱ ዓላማ ነበር።

“የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው።”ዮሐንስ 4:34

ኢየሱስ በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ በሰማይ የሚኖረውን የአባቱን፣ የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም ጥሯል። * የአምላክን ፈቃድ መፈጸም በእጅጉ ያስደስተው ነበር። እንዲያውም ከላይ የተጠቀሰው ጥቅስ እንደሚያሳየው የአምላክን ፈቃድ መፈጸምን ከምግብ ጋር አመሳስሎታል። ኢየሱስ ይህን የተናገረው በምን ሁኔታ ውስጥ እያለ እንደነበር እንመልከት።

ኢየሱስ ይህን ሐሳብ የተናገረው ስድስት ሰዓት ገደማ ላይ ነበር። (ዮሐንስ 4:6) የጠዋቱን ክፍለ ጊዜ በሙሉ ያሳለፈው ተራራማ የሆነውን የሰማርያ ምድር አቋርጦ በመጓዝ ስለነበር በዚህ ጊዜ ርቦት እንደሚሆን ምንም አያጠያይቅም። በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ “ረቢ፣ ብላ እንጂ” አሉት። (ዮሐንስ 4:31) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ መልስ ሲሰጥ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ እንደ ምግብ እንደሚሆንለትና ብርታት እንደሚሰጠው ጠቆማቸው። ታዲያ ይህ ሕይወቱን ትርጉም ባለው መንገድ እንደመራ አያሳይም?

2. ኢየሱስ አባቱን በጣም ይወድ ነበር።

‘እኔ አብን እወደዋለሁ።’ዮሐንስ 14:31

ኢየሱስ በሰማይ ይኖር በነበረበት ጊዜ ከአባቱ ጋር የጠበቀ ዝምድና ነበረው። ለአምላክ የነበረው ጥልቅ ፍቅር የአባቱን ስም፣ ዓላማና ባሕርያት ለሰዎች እንዲያሳውቅ ገፋፍቶታል። ኢየሱስ በንግግሩ፣ በድርጊቱና በአመለካከቱ አባቱን ፍጹም በሆነ መንገድ በማንጸባረቁ ኢየሱስን በማየት አባቱን ማየት እንችላለን። በመሆኑም ፊልጶስ ኢየሱስን “አብን አሳየን” ባለው ጊዜ “እኔን ያየ አብንም አይቷል” ሲል መልሶለታል።—ዮሐንስ 14:8, 9

ኢየሱስ አባቱን እጅግ ይወድ ስለነበረ እስከሞት ድረስ ለእሱ ለመታዘዝ ፈቃደኛ ሆኗል። (ፊልጵስዩስ 2:7, 8፤ 1 ዮሐንስ 5:3) ኢየሱስ ለአምላክ የነበረው እንዲህ ያለ ጥልቅ ፍቅር ሕይወቱ ትርጉም ያለው እንዲሆን አድርጓል።

 3. ኢየሱስ ሰዎችን ይወድ ነበር።

“ነፍሱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም።”ዮሐንስ 15:13

ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ከፊታችን አስከፊ ነገር እንደሚጠብቀን ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” (ሮም 5:12) ኃጢአት ካስከተለብን መዘዝ ይኸውም ከሞት በራሳችን አቅም ማምለጥ አንችልም።—ሮም 6:23

ደስ የሚለው ነገር፣ ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ የሰው ዘር ላጋጠመው ችግር መፍትሔ አዘጋጅቷል። ይሖዋ፣ ፍጹም የሆነውና ምንም ኃጢአት የሌለበት ልጁ ማለትም ኢየሱስ ተሠቃይቶ እንዲሞት ፈቅዷል፤ ይህን ያደረገው የሰው ልጆች ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ የሚወጡበትን ቤዛ ለመክፈል ነው። ኢየሱስ ለአባቱ እና ለሰው ልጆች ባለው ፍቅር ተገፋፍቶ የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም ራሱን በፈቃደኝነት ያቀረበ ከመሆኑም ሌላ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ለእኛ ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኗል። (ሮም 5:6-8) እንዲህ ያለው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ሕይወቱ ትርጉም እንዲኖረው አድርጓል። *

4. ኢየሱስ አባቱ እንደሚወደውና በእሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው ያውቅ ነበር።

“በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው።”ማቴዎስ 3:17

ይሖዋ በሰማይ ሆኖ ይህን የተናገረው ኢየሱስ በተጠመቀበት ጊዜ ነበር። በዚህ መንገድ ይሖዋ ልጁን ኢየሱስን እንደሚወደውና በእሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው በግልጽ ተናግሯል። በመሆኑም ኢየሱስ ‘አብ ይወደኛል’ ብሎ በእርግጠኝነት መናገሩ ምንም አያስደንቅም! (ዮሐንስ 10፡17) ኢየሱስ አባቱ እንደሚወደውና ሞገስ እንደሚያሳየው ስለሚያውቅ የደረሰበትን ተቃውሞና ነቀፋ በልበ ሙሉነት ተጋፍጧል። ከሞት ጋር ፊት ለፊት በተፋጠጠበት ጊዜ እንኳ ሚዛኑን የጠበቀ ከመሆኑም ሌላ የተረጋጋ ስሜት ነበረው። (ዮሐንስ 10:18) ኢየሱስ አባቱ እንደሚወደውና በእሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው ማወቁ ሕይወቱ ይበልጥ ትርጉም እንዲኖረው አስችሎታል።

በእርግጥም ኢየሱስ ትርጉም ያለው ሕይወት ኖሯል። እኛም ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት ምን ማድረግ እንደሚኖርብን ከእሱ ብዙ ነገር መማር እንችላለን። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ኢየሱስ ለተከታዮቹ እንዴት መኖር እንደሚገባቸው ከሰጣቸው ግልጽ የሆኑ ምክሮች መካከል አንዳንዶቹን እንመለከታለን።

^ စာပိုဒ်၊ 6 የአምላክ የግል ስም ይሖዋ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል።

^ စာပိုဒ်၊ 15 የኢየሱስ ሞት ስላስገኘው ቤዛ ይበልጥ ለማወቅ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 5 ተመልከት።